የትራምፕ የረጅም ጊዜ ምኞት የሆነው የዋይት ሀውስ አዳራሽ በ200 ሚሊዮን ዶላር ሊገነባ ነው

የሚገነባውን ሰፊ እና ብዙ ወንበሮች የሚይዝ አዳራሽ የሚያሳይ ምስል

የፎቶው ባለመብት, White House

ዋይት ሀውስ፤ በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተደጋጋሚ ይጠቀስ የነበረን አዲስ የድግስ በአዳራሽ ለመገንባት የሚያስችል የ200 ሚሊዮን ዶላር እቅድ ይፋ አደረገ።

አዲሱ የድግስ አዳራሽ የሚገነባው በአሁኑ ወቅት የቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ ቢሮዎች እና ሌሎች ቁልፍ የዋይት ሀውስ የስራ ክፍሎች ከሚገኙበት እና "ዘመናዊ" ተደርጎ ከሚታደሰው የቤተ መንግስቱ የምስራቅ ክንፍ ጎን ነው ተብሏል።

ለግንባታው የሚውለው ገንዘብ በቀጥታ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ እና እስከአሁን ማንነታቸው ይፋ ካልተደረገ ሌሎች ለጋሾች እንደሚሰበሰብ እንዲሁም ስራው በመስከረም ላይ እንደሚጀምር የዋይት ሀውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮሊን ሌቪት ተናግረዋል።

ትራምፕ ከዚህ ቀደም ኋይት ሀውስ ውስጥ "ውብ" የድግስ አዳራሽ ለመገንባት በተደጋጋሚ ቃል የገቡ ሲሆን እ.አ.አ በ2016 በባራክ ኦባማ አስተዳደር ወቅት ለዚሁ ግንባታ የሚውል 100 ሚሊየን ዶላር ለመክፈል ቃል ገብተውም ጭምር ነበር። የወቅቱ ፕሬዝዳንት ኦባማ ግን ይህንን ልገሳ ውድቅ አድርገውታል።

ቃል አቀባይዋ ሌቪት ሀሙስ ዕለት በዋይት ሀውስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ላይ ሌቪት ግንባታው "በጣም አስፈላጊ እና ግሩም" የቤተ መንግስቱ ተጨማሪ አካል እንደሚሆን ገልጸዋል። አዳራሹ፤ 8,360 ስኩዌር ሜትር ስፋት ይኖረዋል እንዲሁም 650 የሚጠጉ መቀመጫዎችን ይይዛል ተብሎ እንደሚገመትም አክለዋል።

በአሁኑ ወቅት በርካታዎቹ የዋይት ሀውስ መደበኛ ተግባራት የሚከናወኑት 200 ገደማ ሰዎችም መያዝ በሚችለው የቤተ መንግስቱ ምስራቃዊ ክፍል ውስጥ ነው።

እንደ ሌቪት ገለጻ አዲሱ የድግስ አዳራሽ፤ ከዚህ ቀደም የዓለም መሪዎች ጭምር በሚታደሙባቸው አንዳንድ ትልልቅ ዝግጅቶችን ለማከናወን የሚጣለውን "ትልቅ እና የማያምር ድንኳን" ያስቀራል።

የአዳራሹ ግንባታ፤ በጥር 2029 ከሚጠናቀቀው የትራምፕ የስልጣን ዘመን "ረጅም ጊዜ በፊት" እንደሚያልቅም አክለዋል።

የዋይት ሀውስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሱዚ ዋይልስ በበኩላቸው፤ "ፕሬዝዳንቱ እና የትራምፕ ኋይት ሀውስ፤ ቀጣይ አስተዳደሮች እና የአሜሪካ ትውልዶች ጭምር የሚደሰቱበት ውብ የድግስ አዳራሽ በሚገነባበት ጊዜ የቤተ መንግሥቱን ልዩ ታሪክ ለመጠበቅ ከሚመለከታቸው ድርጅቶች ጋር ለመስራት ሙሉ በሙሉ ቁርጠኛ ናቸው" ሲሉ ተናግረዋል።

ከእድሳቱ በኋላ የዋይት ሀውስ ምስራቃዊ ክንፍ ከውጭ ምን እንደሚመስል የሚያሳይ ምስል

የፎቶው ባለመብት, White House

የምስሉ መግለጫ, ከእድሳቱ በኋላ የዋይት ሀውስ ምስራቃዊ ክንፍ (በቀኝ በኩል የሚገኘው የህንጻው ክፍል) ከውጭ ምን እንደሚመስል የሚያሳይ ምስል

በዋይት ሀውስ የቀረቡት የንድፍ ምስሎች እንደሚያሳዩት፤ አዳራሹ ከቀሪው የኋይት ሀውስ ጋር ተመሳሳይ በሆነ ሥነ ህንፃ ቅርፅ የሚኖረው ሲሆን ቅንጡ ሆኖ በሚዘጋጀው ውስጣዊ ክፍሉ ውስጥም ትላልቅ የሚንጠለጠሉ መብራቶችን እና ያጌጡ አምዶች ይኖሩታል።

የቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕን ቢሮን ጨምሮ ከግንባታው አጠገብ በሚገኘው የዋይት ሀውስ ምስራቃዊ ክንፍ ውስጥ ያሉ የስራ ክፍሎች በጊዜያዊነት ይዛወራሉ።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ዋይት ሀውስ እንዲታደስ እና በዚያውም አዲስ የድግስ አዳራሽ እንዲገነባ ያላቸውን ምኞት በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል።

ቤተ መንግሥቱ ከዚህ ቀደም ሁለት ትላልቅ የሰንደቅ ዓላማ ፖሎች የተተከሉበት እና የኦቫል ቢሮው አዲስ የወርቅ ጌጦች እንዲጨመሩበት የተደረገ ሲሆን ታዋቂው የሮዝ ጋርደንም በቡልዶዘር ተጠርጓል።

ትራምፕ ሐሙስ ዕለት በዋይት ሀውስ በተካሄደ ዝግጅት ላይ "የድግስ አዳራሾች ላይ ጥሩ የሆነ ፕሬዝዳንት የለም" እንዲሁም "ነገሮችን መገንባት ጥሩ ነኝ" ሲሉ ተደምጠዋል።

ትራምፕ አክለውም፤ በዋይት ሀውስ ለሚካሄዱ ትላልቅ ዝግጅቶች "ሁልጊዜ ድንኳኖችን ማግኘት ነበረባቸው" ያሉ ሲሆን ይህንን ልምድም "ለእይታ ቆንጆ አይደለም" ሲሉ አጣጥለዋል።