ትራምፕ ቤት አልባ ሰዎች ከዋሽንግተን "በፍጥነት" ለቅቀው እንዲወጡ ጠየቁ

በዋሺንግተን ዲሲ መናፈሻ ውስጥ ቤት አልባዎች የዘረጉት ድንኳን ሲፈራርስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, እአአ በ2023 በዋና ከተማዋ ዋሽንግተን ዲሲ ድንኳን ዘርግተው ይኖሩ የነበሩ ሰዎች እንዲነሱ ተደርገዋል

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዋሺንግተን ዲሲ የሚታዩ ወንጀሎችን ለመከላከል ቃል ገብተው በከተማዋ የሚገኙ ቤት የሌላቸው ሰዎች "መውጣት አለባቸው" አሉ።

የከተማዋ ከንቲባው ግን ዋይት ሐውስ ዋና ከተማዋን ከባግዳድ ጋር በማነጻጸሩ ተችተዋል።

እሁድ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ "የምትቆዩበት ቦታ እንሰጣችኋለን፤ ነገር ግን ከዋና ከተማው የራቀ ነው" በማለት ለጥፈዋል።

የሪፐብሊካኑ ፕሬዚዳንት ከተማዋን "ከዚህ በፊት ከነበረችው የበለጠ አስተማማኝ እና የበለጠ ውብ" ለማድረግ ስለወጠኑት ዕቅድ ሰኞ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ቀጠሮ ይዘዋል።

የከተማዋ ከንቲባ ዲሞክራቷ ሙሪየል ቦውሰር "የወንጀል መጨመር እያጋጠመን አይደለም" ሲሉ አስተባብለዋል።

ትራምፕ ባለፈው ወር ቤት የሌላቸውን ሰዎች በቀላሉ በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚያስችል ትዕዛዝ የፈረሙ ሲሆን ባለፈው ሳምንት ደግሞ የፌደራል ሕግ አስከባሪ አካላት በዋሽንግተን ዲሲ ጎዳናዎች እንዲሰማሩ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

ትራምፕ እሁድ ዕለት በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ "ቤት አልባዎች መውጣት አለባቸው፤ ወድያውኑ" ሲሉ ጽፈዋል።

"የምትቆዩበት ቦታዎችን እንሰጣችኋለን፤ ነገር ግን ከዋና ከተማው ርቆ በሚገኝ ስፍራ ነው። ወንጀለኞች፣ እናንተ መውጣት አይጠበቅባችሁም። የሚገባችሁ ቦታ እስር ቤት እናስቀምጣችኋለን።"

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ድንኳኖች እና ቆሻሻዎችን ከሚያሳዩ ምስሎች አያይዘው በለጠፉት ፅሁፍ " 'ደጉ ሰው' ብሎ ነገር አይኖርም። ዋና ከተማችን እንዲመለስ እንፈልጋለን። በጉዳዩ ላይ ለሰጣችሁት ትኩረት እናመሰግናለን!" ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ ስላቀዱት ዝርዝር ሁኔታ በይፋ የሚታወቅ ነገር የለም። ነገር ግን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ 2022 ባደረጉት ንግግር ቤት የሌላቸውን ሰዎች ከከተማ ውጭ ርካሽ በሆነ አካባቢ ላይ "ከፍተኛ ጥራት" ወዳላቸው የመታጠቢያ ቤቶች እና የሕክምና ባለሙያዎች ተደራሽ ወደሚሆኑባቸው ድንኳኖች እንዲዘዋወሩ ሀሳብ አቅርበው ነበር።

አርብ ዕለት ትራምፕ የፌደራል አካላት በዋሽንግተን ዲሲ "ከቁጥጥር ውጪ" የሆነውን ወንጀል ለመግታት እንዲሰማሩ አዝዘዋል።

የፌደራል የፀጥታ አካላቱ ከዩኤስ ፓርክ ፖሊስ፣ ከመድሃኒት ቁጥጥር አስተዳደር፣ ከኤፍቢአይ እና ከዩኤስ ማርሻል የተውጣጡ ይሆናሉ ተብሏል።

ቅዳሜ ምሽት እስከ 450 የሚደርሱ የፌደራል የፀጥታ አካላት መሰማራታቸውን የዋይት ሐውስ ባለስልጣን ለናሽናል ፐብሊክ ሬዲዮ ተናግረዋል።

እርምጃው የመጣው የ19 ዓመቱ የቀድሞ የመንግሥት ቅልጥፍና ቢሮ ሠራተኛ (ዶጅ) በዋሽንግተን ዲሲ የመኪና ስርቆት ሙከራ ከተፈፀመበት በኋላ ነው።

ትራምፕ ስለዚያ ክስተት በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ ደም እየፈሰሰው የሚታየውን ተጎጂ ፎቶ ለጥፈዋል።

ከንቲባ ቦውሰር እሁድ ዕለት ለኤምኤስኤንቢሲ እንደተናገሩት "እአአ በ2023 የወንጀል መጠኑ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ እውነት ነው። ይህ ግን 2023 አይደለም።

"ባለፉት ሁለት ዓመታት በዚህ ከተማ ውስጥ የሚፈጸሙ ጥቃት የተቀላቀለባቸውን ወንጀሎች በመቀነስ በ30 ዓመታት ውስጥ ዝቅተኛው ደረጃ ላይ እንዲደርስ ማድረግ ችለናል።"

የዋይት ሐውስ ምክትል ኃላፊ ስቴፈን ሚለር የዩኤስ ዋና ከተማን "ከባግዳድ የበለጠ አደገኛ" ማለታቸውን በመጥቀስ ወቅሰዋል።

ቦውሰር "በጦርነት ከታመሰች አገር ጋር የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት ንጽጽር የተጋነነ እና ሐሰት ነው" ብለዋል።

ዋሺንግተን ዲሲ ከሌሎች የአሜሪካ ከተሞች ጋር ስትነጻጸር ከፍ ያሉ ግድያ ወንጀሎች የሚፈፀምባት ሲሆን ባለፉት ሰባት ወራት በድምሩ 98 ግድያዎች ተመዝግበዋል።

ይሀም በዋና ከተማዋ የግድያ ወንጀሎች ከአስር ዓመታት በፊት ከነበሩት እየጨመሩ መምጣታቸውን ያሳያል።

ነገር ግን በጥር ወር የወጣው የፌደራል መረጃ እንደሚያመለክተው ዋሽንግተን ዲሲ ባለፈው ዓመት ዝቅተኛ ኃይል የተቀላቀለባቸው ወንጀሎችን አስመዝግባለች።

ትራምፕ ሰኞ ዕለት በዋይት ሐውስ በአሜሪካ መዲና የሚካሄደውን የኃይል ጥቃት ለማስቆም ያላቸውን ዕቅድ ይፋ ለማድረግ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

እሁድ ዕለት ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በሚኖረው ዝግጅት በከተማው ውስጥ "ወንጀልን፣ግድያ እና ሞትን" ማስቆምን እንዲሁም "የከተማዋን እድሳት" በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ እንደሚናገሩ አስታውቀዋል።

ቦውሰርን "ሙከራ ያደረገች መልካም ሰው" ሲሉ የገለጿቸው ሲሆን፣ ምንም እንኳን ጥረት ብታደርግም ወንጀሎች "እየከፉ" መቀጠላቸውን እና ከተማዋ "ቆሻሻ እና አስቀያሚ እየሆነች ነው" መጥታለች ብለዋል።

በዋሽንግተን ዲሲ የመኖሪያ ቤት እጦትን ለመቀነስ የሚሰራው ኮሚኒቲ ፓርትነርሺፕ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደገለጸው 700,000 ነዋሪዎች ያሉት ከተማ በየትኛውም ምሽት 3,782 ሰዎች ቤት አልባ ናቸው።

አብዛኛዎቹ በሕዝብ መኖሪያ ቤቶች ወይም በድንገተኛ መጠለያዎች ውስጥ የነበሩ ሲሆን 800 ያህሉ ግን "ጎዳና ላይ" እንደሚኖሩ ተደርገው ይቆጠራሉ።

ዋሽንግተን ዲሲ እንደ ዲስትሪክት በፌዴራል መንግሥት ቁጥጥር የሚደረግባት ሲሆን ይህም አንዳንድ የአካባቢ ሕጎችን የመሻር አቅም ይሰጠዋል።

ፕሬዚዳንቱ ምንም እንኳን ዲስትሪክቱን በፌዴራል ቁጥጥር ስር ለማድረግ የኮንግረስ ይሁንታ ቢያስፈልጋቸውም፣ በከተማው ውስጥ የፌዴራል መሬቶችን እና ሕንፃዎችን ይቆጣጠራሉ።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ፖሊስ እንደሚቆጣጠሩ የዛቱ ሲሆን ከንቲባዋ ቦውሰር ግን አይቻልም ሲሉ ተከራክረዋል።

ቦውሰር "በሕጋችን ውስጥ ፕሬዝዳንቱ በፖሊስ ቢሯችን ላይ የበለጠ ቁጥጥር እንዲኖራቸው የሚፈቅዱ በጣም ውስን ነገሮች አሉ። ከእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ አንዳቸውም በከተማችን በአሁኑ ጊዜ የሉም" ብለዋል።