ከአሜሪካ እና ሩሲያ ጉባዔ አስቀድሞ የደህንነት ኃላፊዎች በዩክሬን ጉዳይ ላይ ለመነጋገር ተሰበሰቡ

የፎቶው ባለመብት, FCDO
የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ እና የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ በዩክሬን ስላለው ጦርነት ለመወያየት በለንደን ከአውሮፓ እና ዩክሬን ደህንነት ኃላፊዎችን ጋር ተገናኙ።
ስብሰባው የተጠራው በአሜሪካ ጥያቄ መሠረት ነው ተብሏል።
በስብሰባው ላይ የዩክሬን ባለስልጣናት እና የአውሮፓ ብሔራዊ ደህንነት አማካሪዎች የተሳተፉ ሲሆን ላሚ በበኩላቸው "ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እየሰራን ባለንበት በዚህ ሰዓት ዩናይትድ ኪንግደም ለዩክሬን የምትሰጠው ድጋፍ እንደተጠበቀ ነው" ብለዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ በሚቀጥለው ሳምንት በአላስካ ከሚካሄደው የዶናልድ ትራምፕ እና የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ስብሰባ አስቀድመው ምንም ዓይነት ግዛት ለሩሲያ እንደማይሰጡ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
የዩክሬን ብሔራዊ ደህንነት እና መከላከያ ምክር ቤት ኃላፊ ረስተም ኡሜሮቭ እና የዜሌንስኪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አንድሪይ ይርማክ ከእንግሊዝ፣ ከዩኤስ፣ ከአውሮፓ ኅብረት፣ ከፈረንሳይ፣ ከጀርመን፣ ከጣሊያን፣ ከፊንላንድ እና ከኔቶ ተወካዮች ጋር በመሆን በውይይቱ ላይ ተገኝተዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ከስብሰባው በፊት ከዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ጋር በስልክ የተነጋገሩ ሲሆን፣ ወደ ሰላም የሚደረገው ጉዞ ላይ ለመወያየት "ወሳኝ መድረክ" እንደሚሆን ተግባብተናል ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, UK government handout
ትራምፕ እና ፑቲን ነሐሴ 9/2017 ዓ.ም. ተገናኝተው ስለ ጦርነቱ የወደፊት ሁኔታ ለመወያየት ቀጠሮ ይዘዋል።
ሩሲያ እአአ በ2022 የካቲት ወር ዩክሬን ላይ ወረራ ከፈፀመች በኋላ የተጀመረውን የሁለቱን አገራት ጦርነት ለማስቆም፣ኪዬቭ ግዛቷን ልትሰጥ እንደምትችል ትራምፕ ፍንጭ ሰጥተዋል።
አርብ ዕለት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሊኖር ስለሚችል የሰላም ስምምነት ሲናገሩ "ለሁለቱም የተሻለ እንዲሆን አንዳንድ ግዛቶችን መለዋወጥ ሊኖር ይችላል" ብለዋል።
"ለሦስት ዓመት ተኩል ውጊያ ስለተካሄደበት ግዛት ነው እያወራን ያለነው። ብዙ ሩሲያውያን ሞተዋል፤ ብዙ ዩክሬናውያን ተሰውተዋል" ብለዋል።
ቅዳሜ ምሽት በርካታ የአውሮፓ መሪዎች ዩክሬንን እንደሚደግፉ እና በማንኛውም የሰላም ድርድር ላይ ኪዬቭ መሳተፍ እንዳለባት የሚገልጽ የጋራ መግለጫ አውጥተዋል።
የብሪታንያ፣የፈረንሳይ፣የጀርመን፣የኢጣሊያ፣የፖላንድ፣የፊንላንድ እና የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ፎን ደር ሌየን መሪዎች "በዩክሬን ውስጥ ለሚኖረው የሰላም መንገድ ያለ ዩክሬን ተሳትፎ መወሰን አይቻልም" ብለዋል።
"ዩክሬን የራሷን እጣ ፈንታ የመምረጥ ነፃነት አላት።"
አክለውም "ዓለም አቀፍ ድንበሮች በኃይል መለወጥ የለባቸውም" እና አገሮቻቸው ለዩክሬን በዲፕሎማሲ፣ በወታደራዊ እና በገንዘብ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
ሩሲያ በተደጋጋሚ በኃይል በያዘቻቸው የዩክሬን በርካታ ክልሎች ላይ የሩሲያ ሉዓላዊነትን እውቅና እንድትሰጥ እንዲሁም ወታደራዊ ትጥቆቿን እንድትፈታ እና ኔቶን ለመቀላቀል ያላትን ፍላጎት እርግፍ አድርጋ እንድትተው ትጠይቃለች።
ትራምፕም በተደጋጋሚ ዩክሬን የተወሰነ ግዛቶቿን ለሰላም ስትል ለሩሲያ እንድትተው በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
ዜሌንስኪ ትራምፕን ላለመተቸት ተጠንቅቀው፣በማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ ይህንን ሀሳብ እንደማይቀበሉት ግልጽ አድርገዋል።
ቅዳሜ ጠዋት በቴሌግራም ገጻቸው ላይ "ዩክሬናውያን መሬታቸውን ለወራሪ አሳልፈው አይሰጡም" ብለዋል። አክለውም ዩክሬን በማንኛውም የሰላም መፍትሄ ውስጥ መሳተፍ አለባት ሲሉ ጠይቀዋል።
"ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር፣ ከሁሉም አጋሮቻችን ጋር፣ ለእውነተኛ እና ከሁሉም በላይ ደግሞ ለዘላቂ ሰላም ሞስኮ ስለፈለገች ለማታፈርሰው ሰላም ለመስራት ዝግጁ ነን።"
ቅዳሜ ምሽት ባደረጉት ንግግር ላይ ደግሞ ዜሌንስኪ በዩኬ የተደረገው ስብሰባ ገንቢ ነበር ብለዋል።
"የዩክሬን ሰላም በጋራ እና ከዩክሬን ጋር በጋራ ብቻ ነው መወሰን ያለበት። ይህ ቁልፍ መርኅ ነው" ብለዋል።
ዩክሬን እና ብዙ የአውሮፓ አጋሮቿ ትራምፕ እና ፑቲን ኪዬቭን አግልለው ስምምነት ሊያደርጉ ይችላሉ የሚል ስጋት አላቸው።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ቅዳሜ ዕለት በኤክስ ገጻቸው ላይ የዩክሬን የወደፊት ዕጣ ፈንታ "ከዩክሬናውያን ውጭ ሊወሰን አይችልም" ሲሉ አስጠንቅቀው "አውሮፓውያንም የራሳቸው ደህንነት አደጋ ላይ ስለሆነ የመፍትሄው አካል ይሆናሉ" ብለዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሩሲያ ላይ ጠንከር ያሉ አስተያየቶችን ቢሰጡም እስካሁን ግን ለዩክሬን ተጨባጭ እርምጃዎችን አላስገኙም።
አርብ ዕለት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ሩሲያ በፍጥነት የተኩስ አቁም ስምምነት እንድታደርግ ወይም ተጨማሪ ማዕቀቦች እንደሚጠብቃት ገልጸው ቀነ ገደብ አስቀምጠዋል።
የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ የዋይት ሐውስ ከፍተኛ ባለስልጣንን ጠቅሶ እንደዘገበው ዜሌንስኪ በፑቲን እና በትራምፕ መካከል በሚደረገው ስብሰባ ላይ በተወሰነ መልኩ ሊሳተፉ ይችላሉ።
ዩክሬን ያልተሳተፈችበት ማንኛውም የሰላም ድርድር በቀላሉ ሊፈርስ ይችላል የሚል ፍርሃት አለ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ወታደሮች እና ሰላማዊ ሰዎች ለሰላም ያላቸውን ከፍተኛ ፍላጎት ገልጸዋል። ያለማቋረጥ በቀጠለው ውጊያ እና ሩሲያ በምትፈጽማቸው የሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ሚሳኤል ጥቃቶች መሰላቸት ተፈጥሯል።
ነገር ግን ዩክሬን በማንኛውም ዋጋ ሰላምን ለመቀበል ፈቃደኛ መሆኗን የሚያሳይ ፍንጭ የለም።















