ትራምፕና ፑቲን አላሳካ ተገናኝተው ስለ ዩክሬን ጦርነት ሊመክሩ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የፊታችን አርብ በአላስካ ተገናኝተው ስለ ዩክሬን ጦርነት እንደሚወያዩ ተገለጸ።
ነሐሴ 9/2017 ዓ. ም. መሪዎቹ እንደሚገናኙ ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያቸው ገልጸዋል። የክሬምሊን ቃል አቀባይም ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
አላስካ ለሩሲያ ቅርብ ስለሆነች ምቹ ቦታ እንደሆነም ተገልጿል። በዩክሬን በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም።
ዩክሬን ጦርነቱን ለመግታት ግዛቶች መስጠት ይኖርባታል የሚል ሐሳብ ከትራምፕ ከተደመጠ በኋላ ነው ስለ ውይይቱ የተሰማው።
"በሦስት ዓመት ተኩል ውስጥ ለዚህ ግዛት ብዙ ሩሲያውያንና ዩክሬናውያን ሞተዋል። ውስብስብ ጉዳይ ነው። የተወሰኑትን እናስመልሳለን። የምንለዋወጣቸው ግዛቶችም ይኖራሉ። ለሁለቱም ወገን የሚበጀው ይሄ ነው" ብለዋል ትራምፕ።
የሚቀርበውን የውይይት ሐሳብ ዝርዝር ትራምፕ አልገለጹም።
የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው አካላት ባገኘው መረጃ መሠረት፤ ሩሲያ አጠቃላይ ዶንባስን የምትወስድበትና ክሬምያን ይዛ የምትቀጥልበት የሰላም ስምምነትን የአውሮፓ መሪዎች እንዲቀበሉ የማድረግ ዕቅድን አሜሪካ ይዛለች።
ሩሲያ በከፊል የያዘቻቸውን ኬርሶን እና ዛፖሪዚያ ግዛቶችን የምትመልስም ይሆናል።
ዋል ስትሪት ጆርናል እንደዘገበው፤ የአሜሪካ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ በቅርቡ በሞስኮ ከፑቲን ጋር ሲገናኙ ተመሳሳይ ሐሳብ አቅርበዋል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ እና ፑቲን ከሰላም ስምምነት የራቁ ይመስላል። የአሜሪካን ሐሳብ ዩክሬን እንዲሁም የአውሮፓ መሪዎች ስለመቀበላቸውም አልታወቀም።
አንድ ከፍተኛ የዋይት ሀውስ አመራር ለሲቢኤስ እንዳሉት በቀጣይ አርብ በፑቲንና ትራምፕ መካከል የሚካሄደው ውይይት ላይ ዘለንስኪ ሊገኙ የሚችሉበት ዕድል ይኖራል።
ከዚህ ቀደም በኢስታንቡል ሦስት ውይይቶች ቢካሄዱም ጦርነቱን ማስቆም አልተቻለም። ሩሲያ ያቀረበችውን የድርድር ነጥቦች ዩክሬንና አጋሮቿ ዩክሬንን ለመቆጣጠር የቀረቡ ሐሳቦች በሚል ውድቅ አድርገዋል።
ሩሲያ ወደ 20% የዩክሬንን ግዛት የያዘች ሲሆን የዩክሬን ጦር ወደ ሩሲያ ዘልቆ ለመግባት አልቻለም።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) እንዳትገባና ሩሲያ ላይ በምዕራባውያን የተጣሉ ማዕቀቦች እንዲነሱ ሩሲያ ትሻለች።
የዩክሬን ወታደሮች ሩሲያ በከፊል ከተቆጣጠረቻቸው የደቡብ ምሥራቅ ዩክሬን አራት ግዛቶች እንዲወጡ የሚል ሐሳብም ቀርቧል።
ትራምፕ እንደሚሉት አሜሪካ ሁለቱን አገራት "የማስታረቅ ዕድል" አላት።
"የአውሮፓ መሪዎች ሰላም እንዲሰፍን ይፈልጋሉ። ፑቲንም ሰላም ይፈልጋል ብዬ አስባለሁ። ዘለንስኪም ሰላም እንዲወርድ ነው የሚሻው። ዘለንስኪ መፈረም ያለበት ሰነድ ስላለ የሚፈልገውን ማግኘት አለበት" ብለዋል።
ትራምፕ ፑቲንን አራት ጊዜ ቢጠይቁም አዎንታዊ ምላሽ እንዳላገኙ ጠቅሰው "በጣም አበሳጭቶኛል። የሱ ነገር በቅቶኛል" ሲሉ ለቢቢሲ ባለፈው ወር ተናግረዋል።
ነሐሴ 2 ላይ የተኩስ አቁም እንዲደረስ ቀነ ገደብ አስቀምጠውም ነበር። ቀነ ገደቡ ሲቃረብ ግን ትራምፕና ፑቲን በአካል ተገናኝተው እንደሚወያዩ መረጃዎች መውጣት ጀምረዋል።
አሜሪካ የሩሲያን ምጣኔ ሃብት የሚጎዱ የማዕቀብ ዛቻዎችን ስትሰነዝርም ቆይታለች።















