በአሜሪካ በህጻናት የዱቄት ወተት አምራች ፋብሪካ ላይ የወንጀል ምርመራ ተጀመረ

የአሜሪካ መንግሥት ባለፈው ዓመት በአገሪቱ ውስጥ ከተከሰተው የህጻንት የዱቄት ወተት እጥረት ጋር በተያያዘ ለችግሩ ዋነኛ ተጠያቂ ነው በተባለ ፋብሪካ ላይ የወንጀል ምርመራ ማድረግ ጀመረ።
ምርመራ የሚደረግበት በሚችጋን ግዛት ውስጥ የሚገኘው እና በአሜሪካ ካሉት ትልልቅ ፋብሪካዎች መካከል አንዱ የሆነውና ከምርት ብክለት ጋር በተያያዘ ባለፈው ዓመት የካቲት ላይ በተዘጋው ፋብሪካ ላይ ነው።
በዓለም ደረጃ ከተፈጠረው የአቅርቦት ችግር ጋር ተደርቦ፣ የፋብሪካው መዘጋት በአሜሪካ ውስጥ በአስርታት ውስጥ እጅግ የከፋ ነው የተባለ የህጻንት ዱቄት ወተት እጥረትን አስከትሏል።
ፋብሪካውን የሚያንቀሳቅሰው አቦት ላቦራቶሪስ የተባለው ኩባንያም ምርመራ እየተደረገበት መሆኑን አረጋግጧል።
“የአሜሪካ የፍትህ መሥሪያ ቤት ምርመራው እየተካሄደ መሆኑን ያሳወቀን ሲሆን፣ እኛም ሙሉ ትብብር እያደረግን ነው” ሲል ቃል አቀባዩ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
በአሜሪካ የህጻንት የዱቄት ወተትን በማምረት ትልቁ የሆነው ኩባንያው በጤና ባለሥልጣናት በፋብሪካው ውስጥ በህጻንት ላይ ሞትን ሊያስከትል የሚችል ችግርን የሚፈጥር ባክቴሪያ ማግኘቱን ገልጾ ነበር። በዚህም ሳቢያ ለገበያ የቀረቡትን የጨቅላ ህጻንት የወተት ምርቶች እንዲሰበሰቡ እና ምርት እንዲያቆም ተደርጓል።
የአገሪቱ የምግብ እና መድኃኒት አስተዳደር መሥሪያ ቤትም በፋብሪካው ውስጥ ንጽህናው ያልተጠበቀ ሁኔታ ማግኘቱንም አመልክቷል።
የምርቶቹ ከገበያ መውጣት እና የፋብሪካው መዘጋት በኮሮናቫይረስ ወረርሽን ምክንያት በዓለም አቀፍ የአቅርቦት ችግር ምክንያት ከተፈጠረው የምርት መስተጓጎል ጋር ተዳምሮ በመላዋ አሜሪካ የህጻንት የዱቄት ወተት እጥረትን በእጅጉ አባብሶት ነበር።
አምራቹ የማስተካከያ እርምጃ የሚወስድበትን ዕቅድ ባለፈው ሚያዝያ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል አቅርቦ፣ በተከታይነትም ገለልተኛ ባለሙያዎች የምርት ሂደቱን እንዲፈትሹ መቅጠርን ጨምሮ ያጋጠመውን ችግር የሚፈቱ በርካታ እርምጃዎችን ለመውሰድ ተስማምቶ ነበር።
ፋብሪካው በሰኔ ወር መልሶ ቢከፈትም ግዛቲቱን በመታት ወደጀብ እና ጎርፍ ምክንያት ለበርካታ ሳምንታት ዝግ ሆኖ ቆይቶ ምርቱን በሐምሌ ወር እንደገና ጀምሯል።
የአሜሪካ ምግብ እና መድኃኒት አስተዳደር ያደረገው ምርመራ ምንም እንኳን ከፋብሪካው ጋር ግንኙነት እንዳለው በትክክል ማረጋገጥ ባይችልም፣ ዘጠኝ የሚደርሱ ህጻናት የፋብሪካውን የዱቄት ወተት ከወሰዱ በኋላ ለሞት መዳረጋቸውን አመልክቷል።
የዱቄት ወተት አምራች ኩባንያው ግን ህጻናቱን ለሞት የዳረገው ባክቴሪያ እና ምርቱን በቀጥታ የሚያገናኛቸው ነገር የለም ሲል አስተባብሏል።
በወቅቱ መንግሥት ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ፍቃድ ያልሰጣቸውን የዱቄት ወተት ምርቶችን እንዳይጠቀሙ ቢያስጠነቅቅም ችግር የገጠማቸው ወላጆችም ወተቱን ከጥቁር ገበያ ለመግዛት ተገደው ነበር።
አንዳንዶችም የልጆቻቸውን የዱቄት ወተት ፍላጎት ለማሟላት በቤት ውስጥ ለማዘጋጀት አስከመሞከር ደርሰው የነበረ ሲሆን፣ ባለሙያዎችም ወላጆች ይህንን ከመሞከር እንዲቆጠቡ ሲመክሩ ነበር።
ይህንንም ተከትሎ በአሜሪካ ውስጥ የህጻናት የዱቄት ወተት እጥረት በመከሰቱ ወላጆች ችግር ላይ ወድቀው ነበር። መንግሥትም የአስቸኳይ ጊዜ ውሳኔ ሕግን በመተግበር በሚሊዮን የሚቆጠሩ የዱቄት ወተት ምርቶችን ከሌሎች አገራት እንዲገባ ማድረጉ ይታወሳል።












