የአሜሪካ ጦር ምንነቱ ያልተገለጸ በራሪ አካል ለአራተኛ ጊዜ መትቶ ጣለ

ጦር ጄት

የፎቶው ባለመብት, AFP

የአሜሪካ ጦር በዚህ ወር ለአራተኛ ጊዜ ምንነቱ ያልታወቀ በራሪ አካል በሰሜናዊ የአገሪቱ ግዛት ሰማይ ላይ መትቶ ጣለ።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ካናዳ ድንበር አቅራቢያ ይህ በራሪ አካል ተመትቶ እንዲወድቅ ትናንት እሁድ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

ፔንታገን በመግለጫው ይህ በራሪ አካል ሲንሳፈፍ የነበረው በ20 ሺህ ጫማ ከፍታ ላይ ስለነበረ፣ በመንገደኞች የአውሮፕላን የበረራ መስመር ላይ ጣልቃ ሳይገባ አይቀርም ብሏል።

የአሜሪካ ጦር ይህ በራሪ አካል ቅዳሜ ዕለት ሞንታና በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ ሲንሳፈፍ ነው ያገኘው።

ሰው አልባው በራሪ አካል ኤፍ-16 በተሰኘ ጄት በሚሳኤል ተመትቶ መውደቁን ጦሩ ጨምሮ አስታውቋል።

ይህ ክስተት በሰሜን አሜሪካ እጅግ በራቀ ከፍታ ላይ እየበረሩ የሚገኙ በራሪ አካላት ጉዳይ ተጨማሪ ጥያቄዎችን ያጫረ ሆኗል።

የቻይና የስለላ በራሪ አካል ነው የተባለ ፊኛ በአሜሪካ ሰማይ ላይ ለቀናት ሲበር ቆይቶ ከ10 ቀናት በፊት ተመትቶ መውደቁ ይታወሳል።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት ይህ ፊኛ መነሻው ከቻይና መሆኑን ገልጸው፣ ተግባሩም ጥብቅ መረጃ የሚገኝባቸው ተቋማትን መሰለል ነው ብለዋል።

ቻይና በበኩሏ ፊኛው የአየር ሁኔታ መከታታየ እንጂ ለስለላ ተግባር የሚውል አለመሆኑን የገለጸች ሲሆን፣ ወደ አሜሪካ የአየር ክልል የገባችውም በነፋስ ተገፍታ መሆኑን ስትገልጽ ቆይታለች።

ቻይና ይህን ትበል እንጂ የፊኛዋ ተመትቶ መውደቅ በሁለቱ ኃያላን አገራት መካከል ባለው ግንኙነት ላይ ከፍተኛ ውጥረትን አስከትሏል።

ይህ ፊኛ ተመትቶ ከወደቀች በኋላ የአሜሪካ ተዋጊ ጀቶች ሦስት በአገሪቱ እጅግ ከፍ ብሎ በሚገኝ የአየር ክልል ውስጥ ሲበሩ የነበሩ በራሪ አካላትን መትተው ጥለዋል።

አርብ ዕለት በአላስካ ግዛት አንድ በራሪ አካል ተመትቶ የወደቀ ሲሆን፣ ተመሳሳይ በራሪ አካል ደግሞ ቅዳሜ ዕለት በሰሜን ምዕራብ ካናዳ ተመትቶ ወድቋል።

አሜሪካ እና ካናዳ ተመትተው የወደቁ በራሪ አካላት ስብርባሪዎችን እየፈለጉ ይገኛሉ።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት ስለእነዚህ ሦስት የበራሪ አካላት ምንነት እና ዓላማ እስካሁን ያሉት ነገር የለም። ይሁን እንጂ የዋይት ሐውስ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ቃል አቀባይ ሦስቱ በራሪ አካላት፣ መጀመሪያ ላይ ተመትቶ ከወደቀው ፊኛ በመጠን በጣም ያነሱ እና በቅርጽም ተመሳሳይ አለመሆናቸው ተናግረዋል።