የቱርክ ርዕደ መሬት፡ ከሕንጻ ግንባታ ጋር በያያዘ 113 ሰዎች ላይ የእስር ትዕዛዝ ወጣ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ከሳምንት በፊት ባጋጠው የመሬት መንቀጥቀጥ ከፈረሱ ሕንጻዎች ግንባታ ጋር በተያያዘ በ113 ሰዎች ላይ የእስር ትዕዛዝ መውጣቱን የቱርክ ባለስልጣናት አስታወቁ።
የቱርክ ፖሊስ በበኩሉ የግንባታ ኮንትራክተሮችን ጨምሮ 12 ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።
በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ሊታሰሩ እንደሚችሉ የሚጠበቅ ሲሆን ይህ የመንግሥት እርምጃ ለደረሰው ጉዳት ሌሎችን ተጠያቂ ለማድረግ ያለመ ስለመሆኑ ብዙዎች የተስማሙበት ሆኗል።
በቱርክ እና ሶሪያ የድንበር ከተሞች ባጋጠመው የመሬት መንቀጥቀጥ ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር ከ33ሺህ በላይ ሆኗል። በርዕደ መሬቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሕንጻዎችም ወድመዋል።
ለዓመታት ባለሙያዎች ርዕደ መሬት ሊከሰት በሚችልባቸው አካባቢዎች የሚገነቡት ሕንጻዎች በሙስና እና በመንግሥት ፖሊስ ምክንያት ደኅንነታቸው የተረጋገጡ አይደለም ሲሉ ቆይታዋል።
የመንግሥት ፖሊሲ የግንባታ ዕድገትን ለማምጣት ሲል የዘረጋው ልል የደረጃ ቁጥጥር በርዕደ መሬቱ በርካታ ሕንጻዎች ወድመው ከፍተኛ አደጋ እንዲደርስ ምክንያት ሆኗል እየተባለ ነው።
የቱርክ ምርጫ እየታቀረበ ሲሆን ክስተቱ በፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶሃን ላይ ከፍተኛ ፈተናን ሊጋርጥ ይችላል ተብሎ ተገምቷል።
ፕሬዝዳንት ኤርዶሃን ከአደጋው በኋላ የነፍስ አድን ስራው እና ለተጎጂዎች እርዳታ የማቅረብ ስራ ላይ ክፍተት እንዳለ ቢያምኑም በአንድ ንግግራቸው ግን ርዕደ መሬቱን ከዕጣ ፈንታ ጋር አያይዘውታል። “እነደዚህ አይነት ነገሮች ሁሌም ያጋጥማሉ፤ የዕጣ ፈንታ አካል ነው” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በደቡባዊ ቱርክ የነፍስ አድን ስራው በጸጥታ ምክያት ተስተጓጉሏል። ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ በስም ባልተጠቀሱ ሁለት ቡድኖች መካከል ግጭት ተፈጥሮ ከጀርመን እና ኦስትሪያ የመጡ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ስራቸውን ለማቆም ተገደዋል።
ከፍተኛ ቅዝቃዜ ባለባቸው በደቡብ ቱርክ እና በሰሜን ሶሪያ አካባቢዎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ቤተ አልባ ሆነዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ከ800ሺህ በላይ ሰዎች በቂ ምግብ እያገኙ አለመሆናቸውን የገለጸ ሲሆን በአካባቢው ተሰማርተው የሚገኙ የእርዳታ ድርጅቶች ደግሞ የሟቾች ቁጥር አሁን ካለበት በእጥፍ ሊጨምር ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በሶሪያ እስከ አርብ ያለው የሟቾች ቁጥር 3ሺህ 500 ሲሆን በቱርክ ደግሞ እስከ ትናንት ዕሁድ የተመዘገበው የሟቾች ቁጥር ከ29ሺህ ተሻግሯል።
አሁን ላይ ሰዎችን በሕይወት የማግኘቱ ተስፋ እየጨለመ ቢሆንም አሁንም ግን በአስደናቂ ሁኔታ ሰዎች በሕይወት እየተገኙ ነው። ከእነዚህም መካከል በጋዚያንቴፕ ግዛት አምስት የቤተሰብ አባላት በሕይወት ተገኝተዋል። የ7 ዓመት ሴት ልጅ ደግሞ 132 ሰዓታትን በፍርስራሽ ስር ካሳለፈች በኋላ በሕይወት ተገኝታለች።












