በቱርክና ሶሪያ አስከፊ ርዕደ መሬቶች የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ28 ሺህ በላይ ደረሰ

በደቡብ ቱርክ የተከሰተው አለመረጋጋት በርዕደ መሬቱ የተጎዱ ዜጎችን ህይወት የማትረፍ ተግባሩን ማስተጓጎሉን ሶስት የነፍስ አድን ድርጅቶች አስታወቁ።
ከሰሞኑ በቱርክ እና በሶሪያ በተከሰተው ርዕደ መሬቶች የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ28 ሺህ በላይ ሆኗል።
በአንዳንድ አካባቢዎች ተአምራዊ በሆነ መልኩ ከፍርስራሹ ውስጥ በህይወት የተረፉ ሰዎች ተገኝተዋል።
ነገር ግን ሰባተኛ ቀኑን ባስቆጠረው በዚህ ርዕደ መሬት ከፍርስራሹ ውስጥ ከዚህ በኋላ በሕይወት የሚወጡ ሰዎች ይኖራሉ ወይ የሚለው ተስፋም እየከሰመ መጥቷል።
የጀርመን እና የኦስትሪያ የነፍስ አድን ቡድኖች ርዕደ መሬቱ በተከሰተባቸው በቱርክ ግዛቶች በታጣቂዎች መካከል የተከተሰውን ግጭትም በመጥቀስ የፍለጋ ስራውን ቅዳሜ እለት ማቆማቸውን አስታውቀዋል።
የምግብ አቅርቦቱ በመናመኑ የአካባቢው የጸጥታው ሁኔታ እየከፋ እንደሚመጣም አንድ የነፍስ አድን ሰራተኛ ተናግረዋል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ 50 የሚሆኑ ግለሰቦች በዘረፋ ተሰማርተዋል በሚል በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን በርካታ የጦር መሳሪያዎች መያዛቸውን የኃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የቱርክ ፕሬዚዳንት በበኩላቸው በማንኛውም ህግ በሚጥስ ሰው የአስቸኳይ ጊዜ ኃይልን እጠቀማለሁ ሲሉ ማስጠንቀቂያ አስተላልፈዋል።
የኦስትሪያ ጦር ቃለ አቀባይ ቅዳሜ ማለዳ ላይ እንደተናገሩት በሃታይ ግዛት ማንነታቸው ባልተወቁ ታጣቂዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት በርካታ የኦስትሪያ የአደጋ መረዳጃ ሰራተኞች ስራቸው እንደተገታና በመጠለያ ውስጥ እንደተጠለሉ አስታውቀዋል።
ከኦስትሪያ በተጨማሪ ሌሎች የዓለም አቀፍ ድርጅቶች የነፍስ አድን ሰራተኞች በዚሁ መጠለያ እንዳሉም ተገልጿል።
“በቱርክ ውስጥ ባሉ አንጃዎች መካከል ግጭቶች እየጨመረ መጥቷል” ሲሉም ሌተናል ኮሌኔል ፒየር ኩገልዌይስ ገልጸዋል።
ኦስትሪያ የነፍስ አድን ስራዋን ከገታች ከሰዓታት በኋላ የቱርክ ጦር ለሰራተኞቹ የደህንነት ከለላ ለመስጠት ወደ ተግባር መግባቱን የኃገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ገልጿል።
የጀርመኑ የፍለጋ እና የነፍስ አድን ቡድን አይሳር እና የጀርመን ፌደራል የቴክኒክ ድጋፍ ኤጀንሲ ቲኤስ ደብልዩ የጸጥታ ስጋቶችን በመጥቀስ ስራዎችን አቁመዋል።
በሺህ የሚቆጠሩ ከርዕደ መሬቱ አደጋ የተረፉ ዜጎች ለሳምንት ያህል ከባድ ቅዝቃዛ ባለበት ሁኔታ ጎዳና ላይ እያደሩ ነው።
የዓለም ጤና ድርጅት በከፍተኛ ቅዝቃዜ የተነሳ የጤና ችግር የሚያጋጥማቸው በርካታ ከአደጋው የተረፉ ሰዎች እንደሚኖረ ያስጠነቀቀ ሲሆን፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፉን እንዲቀጥል ተማጽኗል።
ሕይወታቸውን ካጡት ባሻገር በአደጋው ከ23 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለተለያዩ ችግሮች ተዳርገዋል ወይም ተጋልጠዋል ተብሏል።












