ሶሪያ፡ ፍርስራሽ ውስጥ የተወለደችውን ተአምረኛ ጨቅላ በጉዲፈቻነት ለመውሰድ ሺዎች ጥያቄ አቀረቡ

በቱርክና ሶሪያ የተከሰቱትን ርዕደ መሬቶች ተከትሎ ተአምር የሚመስሉ ዜናዎች እየተሰሙ ነው።
በሰሜን ምዕራብ ሶሪያ ባለፈው ሰኞ ከፍርስራሽ መሬት ውስጥ ገና በተወለደችበት ቅጽበት የተገኘችውንና በተአምር የተረፈችው ጨቅላ በጉዲፈቻነት ለማሳደግ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ጥያቄ እያቀረቡ ነው።
ጥያቄው እየቀረበ ያለው ከሶሪያ ብቻ ሳይሆን ከመላው ዓለም ነው ተብሏል።
አያ የሚል የአረብኛ ስም የተሰጣት ይህቺ ጨቅላ ዕትብቷ ከእናቷ ጋር ገና ሳይቆረጥ ነበር በሞትና ሕይወት መሀል ሆና ከፍርስራሽ ውስጥ የወጣችው።
አያ የሚለው ስም ትንግርት እንደማለት ነው በአገሬው ቋንቋ።
አያ ወዲያውኑ ወደ ሆስፒታል ብትደርስም በቅጡ እንኳ መተንፈስ የማትችል፥ የቆሳሰለችና እብጠቶች የነበሩባት እንቦቀቅላ ነበረች ብለዋል አሁን ባለችበት ሆስፒታል የሕጻናት ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሐኒ ማሩፍ።
ዶ/ር ማሩፍ እንደሚሉት አሁን ጨቅላዋ አያ ጤንነቷ ጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል ብለዋል።
የጨቅላዋ አያ ከፍርስራሽ አፈር ለብሳ ስትወጣ የሚያሳየው ተአምራዊ ቪዲዮ በማኀበራዊ ትስስር መድረክ ከተዛመተ በኋላ ነበር ወዲያውኑ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች እኛ እናሳድጋት ማለት የጀመሩት።
የጨቅላዋ እናትን ጨምሮ አባቷ እንዲሁም አራት ወንድም እህቶቿ በሙሉ በርዕደ መሬቱ ሕይወታቸው አልፏል።
ካሊል አልሱዋዲ የሚባል የጨቅላዋ የሩቅ ዘመድ ነው አሁን ለጊዜው አብሯት ያለው።
እሱም በርካታ የስልክ ጥሪዎች እየደረሱት እንደሆነና የብዙዎች ጥያቄም በጉዲፈቻነት ለመወሰድ እንደሆነ ተናግሯል።
አንዲት የኩዌት የቴሌቭዥን እውቅ ዜና አንባቢ ጨቅላዋን እኔ በተደላደለ ሁኔታ ላሳድጋት ይፈቀድልኝ ስትል ጠይቃለች።
አያ አሁን ያለችበት ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ካሊድ አቲያህ በበኩላቸው በቀን ውስጥ በርካታ ጥሪዎች ከመላው ዓለም እንደሚደርሷቸውና የሁሉም ጥያቄ እኛ እናሳድጋት የሚል እንደሆነ ተናግረዋል።
ዶ/ር ካሊድ ግን ለማንም ምላሽ አልሰጡም።
"የቅርብ ዘመዶቿ እስኪመጡና እስኪወስኑ ድረስ እኔ እንደ ልጄ አሳድጋታለሁ" ብለው የራሳቸው ቤተሰብ ውስጥ ቀላቅለዋታል።
ዶ/ር ካሊድ ከአያ በአራት ወር ብቻ የምትበልጥ ልጅ አለቻቸው።
በዚህ የተነሳ ጨቅላዋን ለሚስታቸው ሰጥተው ሚስታቸው ጡት እያጠባቻት እንደሆነም ተናግረዋል።
በዚህ በሰሜን ምዕራብ ሶሪያ፣ ጂንዳይሪስ ከተማ በደረሰው ርዕደ መሬት አሁንም በርካታ ሕንጻዎች ፈራርሰው ሰዎችን ለማዳን ጥረቱ ቀጥሏል።
መሐመድ አልአድናን የተባለ ጋዜጠኛ ለቢቢሲ እንደተናገረው አሁንም በሕይወት የሚኖሩ በርካታ ቤተሰቦች ከፍርስራሹ ሥር እንዳሉ ስለታወቀ እነሱን ለማዳን ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው።
እሱ እንደሚለው በዚህ ርዕደ መሬት ከተማዋ 90 ከመቶ ወድማለች።
"ዋይት ሄልሜትስ" የሚባሉትና በሶሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት ጊዜ ከፍተኛ ሰብአዊ ድጋፍ በመስጠት የሚታወቁት ቡድኖች ጂንዳይሪስ ከተማ አደጋው ከደረሰ ጀምሮ እገዛ እየሰጡ ነው።
ይሁንና ነፍስ አድን ሥራ ላይ ያሉት ራሳቸው ነፍሳቸውን እያጡ ነው ይላል ጋዜጠኛው መሐመድ።
"ምክንያቱም በርካታዎቹ ሕንጻዎች በአደገኛ ሁኔታ ላይ ስላሉ ነፍስ በማዳን ሥራ ውስጥ አብሮ መቀበርም አለና።"
“አሁን ራሱ ሦስት ሕጻናትን ከፍርስራሽ አውጥተናቸዋል። በዚህ ፍርስራሽ ሥር ቀሪው ቤተሰብ እንዳለ እናምናለን፥ የሚቻለውን እያደረግን ነው” ብሏል መሐመድ።
በሶሪያ እስከአሁን ሦስት ሺህ ሰዎች በርዕደ መሬቱ እንደሞቱ ይገመታል።
ይህ አሐዝ ግን በአማጺዎች የተያዘውን አካባቢ አደጋ አይጨምርም።
በቱርክና ሶሪያ በአጠቃላይ የሟቾች ቁጥር ከ16ሺህ በላይ እንደሆነ ከአካባቢው የሚወጡ ዘገባዎች ያስረዳሉ።












