መንግሥት የአገርን ደኅንነት ለማረጋገጥ “ጠንካራ እርምጃ እወስዳለሁ” አለ

የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

የፎቶው ባለመብት, Government Communication Service

የምስሉ መግለጫ, የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

የኢትዮጵያ መንግሥት ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ ከተከሰተው ችግር ጋር ተያይዞ ከሚታዩ ሁኔታዎች አንጻር የአገር መረጋጋትን እና የዜጎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ ጠንካራ የሕግ ማስከበር እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ።

መንግሥት ይህንን ያለው በኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በኩል በአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ዛሬ ሐሙስ የካቲት 02/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ነው።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አባቶች መካከል የተፈጠረው “መለያየት” ለእኩይ የፖለቲካ ዓላማ ለመጠቀም የሚንቀሳቀሱ አካላት እየተገለጡ ነው ያለው የመንግሥት ኮምዩኒኬሸን፤ “እኩይ ዓላማ ያነገበ ቡድን ተደራጅቶ ወደ ሥራ ገብቷል” ብሏል።

“መንግሥትን የመነቅነቅ ፍላጎት ያለው “የመሥዋዕትነት ሰልፍ አዘጋጅ” በሚል መጠሪያ ባለሃብቶች፣ ፖለቲከኞች እና ወጣቶችን የያዘ አደረጃጀት በትጥቅ ተደግፎ ወጣቶችን እየመለመለ ማሠማራት ጀምሯል” ብሏል የመንግሥት መግለጫ።

ይህ ቡድን ከታጠቁ ኃይሎች ጋርም ግንኙነት እየፈጠረ መሆኑን እና የሚዲያ ቡድን ማደራጀቱንም ጨምሮ አትቷል።

የፌደራሉ መንግሥት ይህን መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የመንግሥት የፀጥታ እና ደኅነት የጋራ ግብረ ኃይል ያስተላለፈውን የሰልፍ ክልከላ አልቀበልም ካለች በኋላ ነው።

መንግሥታዊው ግብረ ኃይል የሰልፍ ክልከላ መደረጉን የገለጸው “በተመሳሳይ ቀን እና ቦታ ሕገ-ወጥ የሰልፍ ጥሪ በማድረግ የዜጎች ሕይወት የሚቀጠፍበት አጋጣሚ እንዲፈጠር ቅስቀሳዎች እየተደረጉ እና ሌሎችም ግጭት ቀስቃሽ ተግባራት እየተፈፀሙ መሆኑን ማረጋገጥ” ስለተቻለ ነው ብሏል።

ሲኖዶሱ ግን የሰልፍ ክልከላ መግለጫው መንግሥት አሁንም “ችግሩን ለመፍታት ሳይሆን . . .ቤተክርስቲያኒቱን ለማጥፋት የታወጀ አዋጅ መሆኑን በጽኑ እንድናምን አድርጎናል” ብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በተመሳሳይ የፌደራሉ መንግሥት የካቲት 02/2015 አመሻሻ ባወጣው መግለጫ ድምጽ ያላቸውና የሌላቸው መሣሪያዎች ይዘው ሁከት የሚፈጥሩ አካላት በሥምሪት ላይ እያሉ ተይዘዋል ካለ በኋላ፣ በሃይማኖት ሽፋን ዓላማቸውን ለማስፈጸም የሚሞክሩ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጿል።

የተፈጠረውን ችግር ከመፍታት ይልቅ ችግሩን ለግልፅ የፖለቲካ ዓላማ ማሳኪያ አድርጎ ወደ መጠቀም ተሸጋግሯል ያለው የኮሙኒኬሽን አገልግሎት፤ በዚህ ተግባር የተሠማሩትን በቁጥጥር ሥር አውሎ ለሕግ የማቅረብ ተግባር መጀመሩን እና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክቷል።

“የመሥዋዕትነት ሰልፍ” ብሎ ሰላማዊ ሰልፍ የለም ያለው የፌደራል መንግሥቱ የአገር መረጋጋትን ለመፍጠር እና የዜጎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ ሲባል መንግሥት ጠንካራ የሕግ ማስከበር ሥራን እንደሚያከናውን ገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተመሳሳይ በወቅታዊው ጉዳይ ላይ ባወጣው መግለጫ በቤተ ክርስቲያኗ ካጋጠመው ችግር ጋር በተያያዘ በሐሰተኛ መረጃ ግጭት እና ሁከት ለመቀስቀስ ሙከራ እየተደረገ ነው ብሏል።

የከተማ አስተዳደሩ በዛሬው ዕለት በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ አየር ጤና ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን “አዳዲስ የተሾሙ ጳጳሳት እየመጡ ነው ቤተክርስቲያናችንን ሊነጥቁን ነው በሚል . . . ውዥንብር በመፍጠር እና ሰዎች ወደ ግጭትና ትርምስ ውስጥ እንዲገቡ ሙከራ ተደርጓል” ብሏል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በሃይማኖት ሽፋን የከተማዋን ሰላም ወደ ሁከት ለመቀየር የሚደረገውን ጥረት ፈፅሞ አልታገስም ብሏል።

ከሁለት ሳምንታት በፊት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ያፈነገጡ ሦስት ጳጳሳት ለ26 ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ከሰጡ በኋላ ነበር ውዝግቡ የተጀመረው።

በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጉዳዩን በተመለከተ ለካቢኔ አባሎቻቸው የሰጡት ማብራሪያ ከቤተክርስቲያኗ በኩል ጠንካራ ተቃውሞ ከገጠመው በኋላ ነገሮች ተካረው አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።

በተለያዩ ቦታዎችም የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች በቤተክርስቲያኗ አባቶች እና ምዕመናን ላይ በወሰዱት እርምጃ ሞት፣ የአካል ጉዳት እና እስር ማጋጠሙን ቤተክርስቲያኗ ገልጻ፣ በጉዳዩ ውስጥ የመንግሥት እጅ እንዳለበት በመግለጽ በተደጋጋሚ ከሳለች ከሳለች።

መንግሥት ግን ጉዳዩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ እንደሚፈልግ በመገልጽ የቀረበበተን ወቀሳ ሲያስተባብል ቆይቷል።