በህወሓት ኃይሎች ስር ናቸው በተባሉ የዋግ ኽምራ ወረዳዎች ነዋሪዎች ለከፋ ረሃብ መጋለጣቸው ተገለጸ

ጨቅላ ሕጻኗን አቅፋ የተኛች እናት

የፎቶው ባለመብት, Solomon Meaza

በአማራ ክልል፣ ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የሚገኙ ተፈናቃዮች ለከፋ የምግብ እጥረት መጋለጣቸውን የክልሉ ባለሥልጣናት እና ተፈናቃዮች ለቢቢሲ ገለጹ።

የዞኑ አደጋ መከላከልና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን መሪ የሆኑት ወ/ሮ ዝናሽ ወርቁ በዞኑ ብቻ ከ67 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ እና በቂ ድጋፍ እያገኙ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ከእነዚህ መካከል ከ19 ሺህ በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮች በሰቆጣ እና በዙሪያው በሚገኙ አራት መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ደግሞ በቤት ኪራይ፣ በፈራረሱ ቤቶች እንዲሁም ከወዳጅ ዘመድ ጋር ተጠግተው ይገኛሉ።

አብዛኞቹ ተፈናቃዮች አሁንም ድረስ በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ይገኛሉ ካሏቸው ሁለት ወረዳዎች ተፈናቅለው የመጡ መሆናቸውንም ባለሥልጣኗ ገልጸዋል።

ወ/ሮ ዝናሽ እንዳሉት ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ሸሽተው ከኦሮሚያ ክልል፣ ወለጋ እንዲሁም በጦርነቱ ምክንያት ከአጎራባቹ የትግራይ ክልል ተፈናቅለው የተጠለሉም ይገኛሉ።

እነዚህ ተፈናቃዮች በተለይም ከአበርገሌ እና ከጻግብጅ ወረዳዎች ከእነ ቤተሰባቸው ተፈናቅለው የሚገኙት ነዋሪዎች እየተደረገላቸው ያለው ድጋፍ በቂ ባለመሆኑ ከነ ቤተሰባቸው ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“ የመንግሥትን እጅ እያየን ሞትን እየተጠባበቅን ነው”

ወጋህታ አርአያ ከአበርገሌ ወረዳ ነው የተፈናቀሉት። አሁን ላይ ከአራት ልጆቻቸው ጋር በሰቆጣ ከተማ በሚገኝ ጊዜያው መጠለያ ውስጥ ነው የሚገኙት። ቀያቸውን ከለቀቁ አንድ ዓመት አልፏቸዋል።

አሁንም በአካባቢያቸው ሰላም ባለመኖሩ ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው መመለስ እንዳልቻሉ ይናገራሉ።

“በቂ እርዳታም እየቀረበልን ስላልሆነ ለልጆቻችን የምናጎርሰው አጥተናል። ችግር ላይ ነው ያለነው” ሲሉ መንግሥት እንዲመለከታቸው ተማፅነዋል።

ከጻግብጅ ወረዳ የተፈናቀሉት ገብረ መድኅን አገዘም ከስምንት ቤተሰባቸውን ጋር ለችግር መዳረጋቸውን ገልጸዋል።

ገብረ መድኅን ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩት በእርሻ ሥራ ነበር። አሁን ግን ማቄን ጨርቄን ሳይሉ ቀያቸውን ጥለው ከወጡ ከአንድ ዓመት በላይ እንደሆናቸው ይናገራሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት የህወሓት ኃይሎች አሁንም ከአካባቢው ባለመውጣታቸው እዚያ የቀሩት ዘመድ አዝማዶቻቸውም ጭምር ለከፋ ረሃብ ተጋልጠዋል።

“ወደ አካባቢው እርዳታ አይገባም። አዝመራም የለም። ችግራቸው የከፋ ነው። ታጣቂዎቹም ያላቸውን ከብቶችና ጥሪት አስገድደው ይወስዱባቸዋል”ይላሉ።

እርሳቸው ባሉበት በአንድ ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ እስከ ስድስት የሚደርስ አባወራ ከእነ ቤተሰቡ ተጠልሎ ይገኛል የሚሉት ገብረ መድኅን፣ የሚደረግላቸው ድጋፍ በቂ አለመሆኑን ይናገራሉ።

“ርሃባችንን ርሃብ አድርገን እንድንኖር ቢያንስ ወደ ቀያችን እንድንመለስ መንግሥት የአካባቢውን ፀጥታ እና ሰላም ያረጋግጥልን” ሲሉም ይጠይቃሉ።

ሦስት ሕጻናት ልጆቿን ይዛ የተፈናቀለችው አያልነሽ ጉላም “መኝታም፣ ውሃም፣ ምግብም የለም። በዚህ ሁኔታ ልጆችን ይዞ መቆየት ፈተና ነው። የመንግሥትን እጅ እያየን ሞትን እየተጠባበቅን ነው ” ብላለች።

የተፈናቀሉ እናቶች እና ሕጻናት

የፎቶው ባለመብት, Solomon Meaza

በህወሓት ቁጥጥር ስር ያሉ አካባቢዎች

በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት አመራሮች መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የሰሜኑ ጦርነት ቢቆምም አሁንም ግን ይኖሩባቸው የነበሩት ወረዳዎች በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ሥር በመሆናቸው ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው መመለስ አለመቻላቸውንም ተናግረዋል።

የዞኑ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ሔኖክ ነጋሽ፣ በዞኑ የሚገኙት ሁለቱ ወረዳዎች አሁንም በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ሥር እንደሚገኙ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

መንግሥት በጦርነቱ ሳቢያ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም ጥረት እያደረገ እና ተቋርጠው የነበሩ መሠረታዊ አገለግሎቶችን ወደነበሩበት እየመለሰ ቢሆንም፣ በእነዚህ ወረዳዎች ግን አሁንም የስልክ፣ የትራንስፖርት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎትም ሆነ ሌሎች አገልግሎት መስጠት አልጀመሩም።

ነዋሪዎች አሁንም ከዓለም ተቆራርጠው ነው ያሉት።

በመሆኑም ለከፋ ረሃብ እና ችግር ስለመዳረጋቸው መረጃ እንዳላቸውና በተከሰተው የምግብ እጥረት ሳቢያም ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች ስለመኖራቸውም ባለሥልጣኑ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ህወሓት የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የለቀቃቸውን ቦታዎች ዝርዝር ባይጠቅስም ይዟቸው ከነበሩት አካባቢዎች ተዋጊዎቹን ማስወጣቱን መግለጹ ይታወሳል።

በህወሓት ስር ናቸው ስለተባሉት አካባቢዎች እና በስፍራው ስላለሁ ሰብአዊ ቀውስ ለማወቅ ቢቢሲ የህወሓት ከፍተኛ አመራር አባል የሆኑትን ክንደያ ገ/ሕይወትን (ፕሮፌ.) ጠይቆ፣ በአካባቢው በቡድናቸው ቁጥጥር ስር የሚገኝ ቦታ የለም ብለዋል።

“በምግብ እጥረት ሳቢያ ሞት ሊከሰት ይችላል”

ወ/ሮ ዝናሽ ለቢቢሲ እንደገለጹት ለተፈናቃዮቹ አስቸኳይ ድጋፍ ከተቋረጠ አምስት ወራት ተቆጥረዋል።

አብዛኞቹ ተፈናቃዮች ሕጻናት፣ ነፍሰ ጡር ሴቶች፣ እናቶች እና አረጋውያን በመሆናቸው አስቸኳይ የአልሚ ምግቦች እንደሚያስፈልጋቸውም ወ/ሮ ዝናሽ አሳስበዋል።

ይህ ካልሆነ ግን በምግብ እጥረት ሳቢያ ሞት ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

“አንድ ሰው 15 ኪሎ ግራም ስንዴ እና 1.5 ኪሎ ግራም ክክ ነው የሚያገኘው። ይህ በቂ አይደለም” የሚሉት ኃላፊዋ፣ በተለይም በህወሓት ቁጥጥር ሥር በሚገኙ ወረዳዎች ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች ምንም ዓይነት ድጋፍ እየተደረጋቸው አለመሆኑን ቡድን መሪዋ ተናግረዋል።

በአካባቢው ያለውን ችግር በተመለከተ በተደጋጋሚ ለፌደራል መንግሥቱ ጥያቄ ቢያቀርቡም አፋጣኝ ምላሽ አላገኘንም ብለዋል።

አሁንም መንግሥት እና የእርዳታ ድርጅቶች በአፋጣኝ እንዲደርሱላቸው ጥሪ አቅርበዋል።

“በክልሉ ከ1.2 ሚሊየን በላይ ተፈናቃዮች አሉ”

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ እያሱ መስፍን እንደተናገሩት በክልሉ ከ1.2 ሚሊየን በላይ ተፈናቃዮች ይገኛሉ።

ይህ ቁጥር በቅርቡ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር እና ሰሜን ሸዋ ዞኖች የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የተፈናቀሉ ሰዎችን ይጨምራል።

እንደ ኃላፊው ከሆነ በዚህ ግጭት ሳቢያ ከሁለቱ ዞኖች ከ400 ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል።

አብዛኞቹ ተፈናቃዮች ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ማንነትን መሠረት ባደረጉ ጥቃቶች ሳቢያ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ከኦሮሚያ ክልሎች የተፈናቀሉ፣ እንዲሁም በጦርነቱ ሳቢያ ከቀያቸው ተፈናቅለው ወደነበሩበት ያልተመለሱ መሆናቸውንም ኃላፊው ገልጸዋል።

“መንግሥት እርዳታ ለማቅረብ ጥረት እያደረገ ቢሆንም በየቀኑ በርካታ ተፈናቃዮች ወደ ክልሉ ስለሚገቡ ተፈናቃዮቹ በቂ ድጋፍ እና የምግብ አቅርቦት እያገኙ አይደለም” ብለዋል።

በተለይም በህወሓት ኃይሎች እስካሁን ተይዘው በሚገኙት አበርገሌ እና ጻግብጅ ወረዳዎች ያሉ ነዋሪዎች ለከፋ ረሃብ መጋለጣቸውን ገልጸዋል።

“ክልሉ በተለያየ ጊዜ ባጋጠሙት የሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች በርካታ ጉዳቶች ደርሰውበታል” የሚሉት ኃላፊው፣ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እና ግጭቶች ባለመቆማቸው እና ተዘዋውሮ የመኖር መብት ባለመረጋገጡ የተፈናቃይን ሰቆቃ እና መከራ መቀነስ አልተቻለም” ብለዋል።

እንደ አቶ እያሱ ከሆነ ከኦሮሚያ ክልል፣ ወለጋ በቀን 250 የሚሆኑ ሰዎች የሚፈጸም ጥቃትን ሽሽት ወደ ክልሉ ይገባሉ። አንዳንድ ጊዜ ቁጥሩ እስከ 800 ይደርሳል።

የክልሉ መንግሥት፣ ሕዝቡ፣ ባለሃብቶች ድጋፍ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ቢሆንም በቂ ድጋፍ ማድረግ አለመቻሉንም ተናግረዋል።

“ከፌደራል መንግሥት ድጋፍ ቢደረግም የሚቀርበው እርዳታ፣ የድጋፍ ፈላጊዎችን ቁጥር መሠረት ያደረገ አይደለም” ብለዋል።

“ባለፈው 6.7 ሚሊየን የክልሉ ሕዝብ ድጋፍ ይፈልጋል ብለን ጠይቀን፣ የተፈቀደልን ለ3.5 ሚሊዮን ሰዎች ብቻ ነው” ሲሉም ከፍተኛ የሆነ ክፍተት መኖሩን ተናግረዋል።