የአይኤምኤፍ ትንበያ፡ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ዕድገት ደረጃ መሻሻል አንድምታ

አይኤምኤፍ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አይኤምኤፍ እንደሚለው ከሆነ አንጎላ፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ እና ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ በሚቀጥሉት ዓመታት ከፍተኛ የምጣኔ ሃብት ዕድገት የሚያስመዘግቡ ናቸው።

ከናይጄሪያ በመቀጠል በአፍሪካ ሁለተኛዋ የነዳጅ አምራች አገር የሆነችው አንጎላ በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርቷ 8.6 በመቶ ይደርሳል ይላል ትንበያው።

ናይጄሪያ ደግሞ አጠቅላይ የአገር ውስጥ ምርቷን ወደ 422 ቢሊዮን ዶላር በማድረስ ምጣኔ ሃብቷን ታሳድጋለች ሲል ድርጅቱ ተንብይዋል።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም በቅርቡ ባወጣው መረጃ ኢትዮጵያ፤ ኬንያን በመተካት ከሰሃራ በታች ካሉ አገራት አራተኛዋ ግዙፍ የምጣኔ ሃብት ባለቤት ትሆናለች ይላል።

በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የነበረው ግጭት መቆሙ እንዲሁም የምጣኔ ሃብት ለውጥ ዕቅዷ፤ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ የምጣኔ ሃብት አውራዎች መካከል እንድትካተት ያስችላታል ይላል የአይኤምኤፍ ትንበያ።

ተቋሙ እንደሚተነብየው የኢትዮጵያ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት በ13.5 በመቶ በማደግ በያዝነው ዓመት (2023) 126.2 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል።

ነገር ግን ይህ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ዘገባ በብዙዎች ዘንድ ጥያቄ ጭሯል። ጦርነቱ ቢቆምም የጦርነቱ ተጽእኖ በአገሪቱ አጠቃላይ ምጣኔ ሃብት ላይ ያለው ተጽእኖን ለማስወገድ እና ለማገገም ያስፈልገዋል የሚሉ በርካቶች ናቸው።

በተጨማሪም በበርካታ ቦታዎች አገሪቱ አሁንም ባለመረጋጋት እየተናጠች ባለችበት ሁኔታ እንዴት ምጣኔ ሃብቷ ሊመነደግ ይችላል? ሲሉ የሚጠይቁ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም።

ለመሆኑ አይኤምኤፍ ማነው? መረጃዎችን የሚያገኘውስ ከየት ነው? ትንበያውን ባለሙያዎች እንዴት ያዩታል?

አይኤምኤፍ ማነው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) 190 አገራትን በአባልነት ያቀፈ ሲሆን፤ አገራቱ የዓለም ምጣኔ ሃብትን ለማረጋጋት አብረው ይሠራሉ።

የተቋሙን ጥቂት መስፈርቶች ያሟሉ አገራት አባል መሆን የሚችሉ ሲሆን፤ አባል ለመሆን እንደ ምጣኔ ሃብት ደረጃቸው የሚከፍሉት ክፍያ አለ። ባለጸጋ የሆኑት ደግሞ በዚያው መጠን የሚከፍሉት ከፍ ይላል።

ተቋሙ ሦስት ዐበይት ዓላማዎች አሉት። የአገራትን ምጣኔ ሃብት እና የገንዘብ ሁኔታ መከታተል፤ አገራት እንዴት ምጣኔ ሃብታቸውን ማሳደግ እንደሚችሉ ምክር መለገስ እና ችግር ለገጠማቸው ደግሞ ብድር እና እርዳታ ይሰጣል።

ተቋሙ ብድር የሚሰጠው አገራቱ ባዋጡት የብር አቅም ነው። በፈረንጆቹ 2018 አርጀንቲና ከአይኤምኤፍ ያገኘችው 57 ቢሊዮን ዶላር በተቋሙ ታሪክ ትልቁ ብድር ሆኖ ተመዝግቧል።

የዓለም አገራት ገንዘብ የሚያገኙበት የብድር እና የስጦታ ቋት ተደርጎ የሚቆጠረው ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስ ላጋጠማቸው አገራት የችግር ጊዜ ደራሽ ነው።

የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲው የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ቤንጃሚን ፍሬድማን፤ የተቋሙን ውጤታማነት መለካት ቀላል አይደለም ይላሉ።

ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ተቋሙ በተለያዩ ጉዳዮች ጣልቃ መግባቱ ነገሮችን አሻሽሏል ወይስ አባብሷል የሚለውን ማወቅ ከባድ መሆኑ ነው ይላሉ።

ሆኖም ሌሎች ምሑራን፤ ተቋሙ በፈረንጆቹ 1980ዎቹ ለሜክሲኮ፤ እንዲሁም በ2002 ለብራዚል ያደረገው ድጋፍ ሁነኛ እንደነበር ያወሳሉ።

አይኤምኤፍ፤ ብድር ለመስጠት አገራት እንዲያሟሉ የሚጠይቃቸው ቅድመ ሁኔታዎች “አስቸጋሪ” ተብለው ሲገለጡ ይሰማል።

መንግሥታት፤ ኮርፖሬት ግብር እንዲቀንሱ አልፎም ምጣኔ ሃብታቸውን ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት እንዲያደርጉ ያስገድዳል ተብሎ ይወቀሳል።

አይኤምኤፍ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ተቋሙ መረጃ የሚያገኘው ከየት ነው?

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አማኑዔል ኤሊያስ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) አንድ የምጣኔ ሃብት ዕድገት አመላካች ቢሆንም ብቻውን የተሟላ ምስል አያሳይም ይላሉ።

የአንድ ግለሰብ “የደም ግፊቱን ለክተን ብቻ ጤነኛ ነው፤ አይደለም” እንደማንለው ሁሉ “ጂዲፒን ብቻ እንደ መመዘኛ ልንወስድ አይገባም” ይላሉ።

የአገሪቱ የፋይናንስ ሁኔታ፣ የግል ዘርፉ በነፃነት መዋዕለ-ንዋይ የማፍሰስ አቅሙ፣ የምግብ ዋስትና፣ ብቁ መሠረተ-ልማት እና በነፃነት የሚሠሩ ተቋማት መኖራቸውን መገምገም እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ።

ምሑሩ አክለው ጥናት አካሂደው ለዓለም አቀፍ ተቋማት የሚሰጡት ባለሙያዎች መሆኑን ቢገልጹም የጥናቱ ገለልተኝነት ግን አጠራጣሪ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማሉ።

“ጥናቶችን የሚያካሂዱት ሙያተኞች እንጂ ፖለቲከኞች አይደሉም። ነገር ግን እንደ ዓለም ባንክ እና አይኤምኤፍ ያሉ ተቋማት ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ ናቸው ማለት አንችልም። ኃያላኑ ምዕራባዊያን አገራት ተፅዕኖ የማሳደር አቅም አላቸው።”

የኢትዮጵያ መንግሥት ከትግራይ ኃይሎች ጋር ጦርነት በገጠመበት ወቅት ከምዕራባዊያን የገንዘብ ተቋማት የገጠመውን ተፅዕኖ እንደምሳሌ ይጠቅሳሉ።

በወቅቱ እንደ ዓለም ባንክ እና የዓለም ገንዘብ ተቋም ያሉ ድርጅቶች የኢትዮጵያ መንግሥት ጦርነቱን ካላቆመ ድጋፍ እንደማያገኝ ሲገልጡ እንደነበር ምሐሩ ያስታውሳሉ።

በምጣኔ ሃብታዊ ጉዳዮች ላይ ትንታኔ በመስጠት የሚታወቁት የኩዌት የሳይንስ ጥናት ተቋም ተመራማሪ አየለ ገላን (ዶ/ር)፤ የአይኤምፍን ዘገባ በጥርጣሬ ከሚመለከቱ ሰዎች መካከል ናቸው።

ምሑሩ አንደሚሉት ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም መረጃውን የሚያገኘው ከአባል አገራት ሲሆን፣ ይህን መረጃ መርምሮ ነው ትንበያ የሚያወጣው።

አይኤምኤፍም ሆነ የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ የምትልከውን መረጃ በተለመከተ በተለይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፊት ከነበረው አስተዳደር ጋር እሰጣገባ ውስጥ ነበሩ የሚሉት ባለሙያው፤ እነዚህ ዓለም አቀፍ ተቋማት አገራት ከሚልኩት መረጃ ራቅ ማለት እንደማይፈልጉ ይገልጻሉ።

ትንበያው ምን ያህል ይሳካል?

አይኤምኤፍ በፈረንጆቹ ዓመት 2021 የኢትዮጵያን አጠቃላይ አገራዊ ምርት (ጂዲፒ) የተለመከተ ትንበያ ለማውጣት አልችልም ማለቱ ይታወሳል።

በወቅቱ ማዕከላዊው መንግሥት የትግራይ ኃይሎች ጦርነት ውስጥ ነበሩ። ይህን ግጭት ተከትሎ ዓለም አቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና ያሳድሩ እንደነበር አይዘነጋም።

ዘንድሮ አይኤምኤፍ ያወጣውን ዘገባ በጥርጣሬ የሚመለከቱት አየለ ገላን (ዶ/ር)፤ “ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ፤ በርካታ ዜጎች የምግብ እርዳታ ፈላጊ መሆናቸው እና የቀንድ ከብቶች በድርቅ ምክንያት እየሞቱ መሆናቸውን ስንመለከት እንዴት ነው የአገሪቱ ‘ጂዲፒ’ በ5% የሚያድገው እንድንል ያደርጋል” ይላሉ።

ምሑሩ አክለውም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ባለው የሰላም መደፍረስ ምክንያት አርሶ አደሮች የግብርና ሥራቸውን በማከናወን ማምረት እንዳልቻሉ በመጥቀስ የአይኤምኤፍ ዘገባ “መሬት ያለውን እውነታ ያገናዘበ አይደለም” ይላሉ።

ተቋሙ በየዓመቱ የዓለም አገራትን ምጣኔ ሃብት አስመልክቶ የተለያዩ ዘገባዎች እንደሚያወጣ የሚጠቁሙት ባለሙያው፣ በርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ይህን ዘገባ ለራሳቸው ጥቅም እንደሚጠቀሙበት ይገልጻሉ።

“የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት በብዙ እጥፍ ያድጋል ብሎ መገመት የተለመደ ነገር እየሆነ መጥቷል” የሚሉት ምሑሩ ይህ የሚመነጨው የሚቀርበውን መረጃ ካለመረዳት ነው የሚል እምነት አላቸው።

የአህጉረ አፍሪካ የምጣኔ ሃብት ጉዳዮችን በመዘገብ የሚታወቀው ቢዝነስ ዴይሊ የተሰኘው ጋዜጣ አይኤምኤፍን ዋቢ አድርጎ ኢትዮጵያ እና አንጎላ፤ በምጣኔ ሃብት ዕድገት ከኬንያ በልጠው ይገኛሉ ሲል ፅፏል።

ምሑሩ እንደሚሉት ቀድሞውንም ቢሆን የኬንያ የምጣኔ ሃብት ዕድገት ከኢትዮጵያ መብለጡ “የኢትዮጵያን ምጣኔ ሃብት ድክመትን የሚያሳይ ነው።”

ይህን ሲያስረዱ ኢትዮጵያ በበርካታ ነገሮች ለምሳሌ በሕዝብ ብዛት፣ በቆዳ ስፋት. . . ኬንያን ትበልጣታለች ብለው የሁለት አገራት አጠቃላይ አገራዊ ምርት እኩል መሆኑ የኬንያ ምጣኔ ሃብት ኃያል እንዲሆን ምክንያት ነው ይላሉ።

“አጠቃላይ አገራዊ ምርቱን ለነብስ ወከፍ ገቢ ስናሰላው የኬንያ ምጣኔ ሃብት በእጥፍ ይበልጠናል ማለት ነው። በአጠቃላይ የኬንያ ዜጎች ሃብት ከኢትዮጵያ በአጥፍ ይበልጣል ማለት ነው።”

ኢትዮጵያ፤ የቡድን 20 አገራትን ‘ኮመን ፍሬምዎርክ’ በተሰኘው ማዕቀፍ አማካይነት ዕዳዋ እንዲቀነስ ብትጠይቅም የትግራይ ጦርነት ሂደቱ እንዲጓተት ምክንያት ሆኗል።

አይኤምኤፍ ብድር ከመስጠቱ በፊት ብድር ጠያቂ አገር ከአበዳሪዎች እፎይታ ማግኘት አለባት ይላል። የትግራይ ጦርነት መቆሙን ተከትሎ አይኤምኤፍ ለኢትዮጵያ ብድር ይሰጥ ይሆን ወይ የሚለው መነጋገሪያ ሆኗል።