የናይጄሪያ ገዢ ፓርቲ የአገሪቱ ጦር በምርጫ ወቅት መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ አሲሯል አለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የናይጄሪያ ገዢ ፓርቲ የአገሪቱ ጦር በምርጫ ወቅት መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ እያሴረ ነው አለ።
ኤፒሲ የተሰኘው ገዢ ፓርቲ አመራር የሆኑት ፖለቲከኛ የጦር ጄነራሎች ባለፈው ስምንት ከኤፒሲ ተቀናቃኝ ከሆነው ፒዲፒ ፓርቲ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ጋር ሚስጥራዊ ስብሰባ አድርገዋል ብለዋል።
የናይጄሪያ ጦር ግን መጪውን ምርጫ ለማስተጓጎል መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ አሲሯል መባሉን አስተባብሏል።
ጦሩ ይህንን ውንጀላ “በክፋት” እና “ተንኮል የተሞላ” ነው ሲል ባወጣው መግለጫ አጣጥሎታል።
በአፍሪካ ከፍተኛውን የሕዝብ ቁጥር በያዘችው ናይጄሪያ የቀጣዩን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አሸናፊን መገመት እጅጉን አዳጋች ሆኗል።
የካቲት 17/2015 ዓ.ም. በሚካሄደው ምርጫ ቦላ ቲንዉቡ ከገዢው ‘ኦል ፕሮግረሲቭ ኮንግረስ’ (ኤፒሲ)፤ አቲኩ አቡበከር ከ ‘ፒፕለስ ዴሞክራቲክ ፓርቲ’ እና ፒተር ኦቢ ከሰራተኞች ፓርቲ ፕሬዝዳንት ለመሆን ጠንካራ ፉክክር የሚያደርጉ ዕጩዎች ናቸው።
ታዲያ ‘ኦል ፕሮግረሲቭ ኮንግረስ’ ፓርቲን ወክለው ለፕሬዝዳንትነት የሚወዳደሩት ቦላ ቲንዉቡ የናጄሪያ ጦር መፈንቀለ መንግሥት ለማድረግ እያሰሬ ነው ማለታቸውን ተከትሎ ሠራዊቱ ባወጣው መግለጫ ጦሩ “ለሕገ መንግስቱ ታመኝ ነው” ብሏል።
ሠራዊቱ ጨምሮም የሲቪል አስተዳደርን ለመፈንቀል በሚሸረብ ሴራ ውስጥ ፈጽሞ ሊሳተፍ አይችለም ብሏል።
“የናይጄሪያ ጦር ኃይል በብዙ ፈተና የተገኘውን ዴሞክራሲ ለመቀልበስ የሚደረግ ሴራ አካል ፈጽሞ ሊሆን አይችለም” ሲሉ የጦሩ ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጄነራል ቱከር ጉሳው ተናግረዋል።
መንግሥትና ዋና ዋና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰራዊቱ በሰጠው መግለጫ ላይ አስተያየት አልሰጡም።
የደኅንነት ስጋት፣ የነዳጅ እጥረትና የአዳዲስ ገንዘብ ኖቶች እጥረት ላሳሰባቸው ናይጄሪያዊያን የአገሪቱ ጦር መፈንቅለ መንግሥት እያሴረ ነው መባሉ እምብዛም ግድ አልሰጣቸውም።












