አርሰናል እና ብራይተን በዳኝነት ስህተት ሙሉ ነጥብ ካጡ በኋላ የዳኞች ስብሰባ ተጠራ

አይቫን ቶኒ ክለቡን አቻ ካደረገ በኋላ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አይቫን ቶኒ ክለቡን አቻ ካደረገ በኋላ

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግን የሚዳኛው የፕሮፌሽናል ዳኞች ማኅበር (ፒጂኤምኦኤል) ሰብሳቢ ሃዋርድ ዌብ በሊጉ ጨዋታዎች የዳኝነት ስህተቶች ማጋጠማቸውን ተከትሎ ስብሰባ ጠሩ።

የዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታን ዳኝተው የሚያውቁት ሃዋርድ ዌብ፤ ቅዳሜ ዕለት በተካሄዱ ጨዋታዎች የዳኝነት ስህተት ሰለባ ለሆኑት አርሰናል እና ብራይተን የስልክ ጥሪ ማድረጋቸው ተገልጿል።

የብሬንትፎርዱ አይቫን ቶኒ ከጨዋታ ውጪ ከነበረ ተጫዋች ኳስ ተቀብሎ ቡድኑን አቻ አድርጎ፣ መድፈኞቹን ሙሉ ሦስት ነጥብ አስጥሏል።

የብራይተን ኤንድ ሆቭ አልቢየኑ እስቲፑኛ ክርስታል ፓላስ ላይ ያስቆጠረው ጎል ጨዋታ ውጪ ተብሎ በስህተት በመሰረዙ ቡድኑ ከፓላስ ጋር ነጥብ ለመጋራት ተገዷል።

አርሰናል ከብሬንትፎርድ ባደረገው እና 1 አቻ በተለያየበት ጨዋታ፤ መድፈኞቹ ላይ የተቆጠረው ኳስ ከጨዋታ ውጪ ከሆነ ተጫዋች የመጣች ነበረች።

የዕለቱ የቫር ዳኛ ሊ ሜሰን ብሬንትፎርድን አቻ ያደረገችው ግብን በቪዲዮ [በቫር] መልሰው ሲመለከቱ ኳሷን ለጎል አመቻችቶ ያቀበለው ተጫዋች ከጨዋታ ውጪ መሆኑን አላረጋገጡም።

ሊ ሜሰን 75ኛ ደቂቃ ላይ ኳሷ ለጎል አስቆጣሪው አይቫን ቶኒ እንድትደርስ በጭንቅላቱ ያቀበለው ኖርጋርድ ከጨዋታ ውጪ መሆን ወይም አለመሆኑን ለማረጋገጥ የቫር ሥርዓትን በመጠቀም መስመር ሳያሰምሩ ቀርተዋል።

የአይቫን ቶኒ ጎል ብትሰረዝ ኖሮ የሊጉ መሪ አርሰናል በሁለተኛ ደረጃ ከሚከተላቸው ማንችስተር ሲቲ ጋር የፊታችን ዕረቡ ከመገናኘታቸው በፊት የነጥብ ልዩነታቸውን አምስት አድርጎ ማስቀጠል ይችል ነበር።

ብራይተኖችም ከክርስታል ፓላስ ጋር በነበራቸው ጨዋታ በዳኝት ስህተት ያስቆጠሩት ግብ ተሰርዞ ወሳኝ ሦስት ነጥብ ከማግኘት ተከልክለዋል።

የኤኳዶራዊው ፔርቪስ ኢስቱፒኛ በ32 ደቂቃ ለቡድኑ ብራይተን ጎል ቢያስቆጥርም፣ የተጫዋቾችን መገኛ የሚለየው መስመር በስህተት ከተሰመረ በኋላ ግቧ ከጨዋታ ውጪ ተብላ ተሰርዛለች።

በዕለቱ በቪዲዮ ዳኝነት ላይ [ቫር] ላይ በዳኝነት ተሰይመው የነበሩት ጄምስ ፖምኪንስ መስመሩን በስህተት ስለማስማራቸው ተገልጿል።

በሊጉ እነዚህ ሁለት “የሰው ልጅ ስህተቶች” ማጋጠማቸውን ተከትሎ ሃዋርድ ዌብ በጠሩት ስብሰባ ላይ በዚህ ሳምንት በሚደረጉ የአውሮፓ ሊጎች ጨዋታዎች ከሚመሩ ዳኞች ውጪ ሁሉም ዳኞች በስብሰባው ላይ ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የዳኞች ማኅበሩ ሰብሳቢ ሃዋርድ ዌብ በዳኝነት ላይ እያጋጠሙ ስላሉ ስህተቶች፣ እንዲሁም ተጫዋቾች እና አሠልጣኞች በዳኝነት ሥርዓቱ ላይ እምንት እንዲኖራቸው ተመሳሳይ ስህተቶች ዳግም እንዳይከሰቱ ከዳኞች ጋር ይነጋገራሉ ተብሏል።

በብራይተን እና በፓላስ ጨዋታ ላይ ስህተት የሰሩት ጆን ብሩክስ የዛሬውን የኤቨርተን እና ሊቨርፑል መርሲሳይድ ደርቢን እንዲሁም የፊታችን ረቡዕ የሚካሄደውን ወሳኙን የአርሰናል እና ሲቲ ጨዋት የቫር ዳኛ መሆናቸው ተረጋግጧል።