“የሰላም ስምምነቱ ህወሓትን ለማዳን በአሜሪካ ግፊት የተደረገ ነው” ፕሬዝዳንት ኢሳያስ

የፎቶው ባለመብት, shabait
በትግራይ ሲካሄድ የነበረውን ጦርነት ለማስቆም በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተደረገው ስምምነት በአሜሪካ ግፊት ህወሓትን ለማዳን የተደረገ ነው ሲሉ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ተናገሩ።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መሪዎች መካከል ስምምነት ተደርጎ ጦርነቱ ከቆመ ከሦስት ወራት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ እሁድ የካቲት 05/2015 ዓ.ም. ለአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ቃለ መጠይቅ ነው ይህንን ያሉት።
ፕሬዝዳንቱ በቃለ መጠይቃቸው ላይ የኢትዮጵያ እና የኤርትራን ግንኙነት በሚመለከት በሰጡት አስተያየት ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. የእርስ በርስ ጦርነቱን ለማብቃት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ላይ የተፈረመው ስምምነት በአሜሪካ የተሸረበ “የማደናቀፍ ታክቲክ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ጦርነቱ ተብብሶ በቀጠለበት ጊዜ በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት አሜሪካ ቁልፍ ሚና በተጫወተችበት ስምምነት ዘላቂ ግጭት እንዲቆም ተደርጎ ሰላም እንዲመጣ እና በትግራይ ውስጥ ያለው ሁኔታ ወደ መደበኛ ሕይወት እንዲመለስ ማስቻሉ ይታወሳል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ግን ስምምነቱ በዋሽንግተን ግፊት ህወሓት ለማዳን የተደረገ ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
“በእኛ በኩል ብዙ የሚያሰጋን ነገር አልነበረም፤ ስምምነት ተፈርሟል? ጥሩ፤ በተፈረመበት አገባብ ይተግበር። ሳይተገበር እንዲህ ነው፣ እንዲያ ነው ብለን መናገር አንችልም፤ ተግባር ላይ እናየዋለን” ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ በወደብ ከተማዋ ምጽዋ ውስጥ በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት በአሜሪካ አማካይነት ህወሓትን ከጦር ሜዳ ሽንፈት ለመታደግ በጥድፊያ የተደረገ ነው ብለዋል።
ወትሮውንም መልካም ያልነበረው በኤርትራ እና በአሜሪካ መካከል የነበረው ግንኙነት፤ ኤርትራ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በነበራት ምክንያት ክፉኛ መበላሸቱ ይታወቃል።
የኤርትራ ሠራዊት ወደ ትግራይ መግባቱ እና ከባድ ሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈጸሙን መሠረት አድርጋ አሜሪካ ጦሩ ከኢትዮጵያ ግዛት እንዲወጣ ስትጠይቅ ከመቆየቷ በተጨማሪ፣ በኤርትራ ጦር አዛዦች እና ተቋማት ላይ ዕቀባን አስከመጣል ደርሳለች።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በቃለምልልሳቸው ላይም መንግሥታቸው ከዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ጋር አንድ ላይ ለመስራት የተጀመረው እንቅስቃሴ የባይደን አስተዳደር በተከተለው ፖሊሲ ምክንያት ከሽፏል ሲሉ ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በናይሮቢ ኬንያ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ቀጥተኛ መልስ ባይሰጡም፣ በፕሪቶሪያ እና ናይሮቢ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተደረሱተን ስምምነቶች እንደሚቀበሏቸው ገልጸዋል።
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ውስጥ በተካሄደው ጦርነት የአገራቸው ጦር ስለነበረው ሚና በዝርዝር ከመናገር ተቆጥበው የነበረ ሲሆን፣ በእሁዱ ቃለ ምልልሳቸው ላይ ግን አንዳንድ ጉዳዮችን አነስተዋል።
በዚህም በጦርነቱ ወቅት የኤርትራ ኃይሎች ከፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ጋር በመቀናጀት በጋራ ሆኖ መዋጋቱን ጠቅሰው ሠራዊታቸው የነበረው ተሳትፎ “ፀረ ማጥቃት” እንደነበር ተናግረዋል።
“ከሁሉም በላይ ከፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ጋር አንድ አካል ሆነን ስለሠራን ብዙ ልምድ አግኝተንበታል፤ ትልቅ ትምህርት ወስደንበታል” ያሉት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፣ በዚህም በቀጠናው “ሰላም ለመገንባት መልካም ልምዶች ተቀያይረናል” ሲሉ ተናግረዋል።
በተጨማሪም “ይህ ግን ለአሜሪካ ትልቅ ራስ ምታት ነው፤ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ሰላም መምጣቱ ያልጠበቁት ክስተት ሆኗል” ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ምክንያት አድርገው ባደረጉት ንግግር ላይም የአገራቸው ሠራዊት በስም ያልጠቀሱትን ‘ፀብ ጫሪ’ እና ‘ተንኳሽ’ ያሉትን ኃይል አስታግሷል ሲሉ ተናግረው ነበር።
ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ እሁድ ዕለት ከአገራቸው ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ የኤርትራ ጦር ከትግራይ መውጣቱን በሚመለከት የሰጡት አስተያየት የለም።
የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ባለሥልጣናት ከሁለት ዓመት በፊት ትግራይ ውስጥ ጦርነቱ በተቀሰቀሰበት ጊዜ የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊት ጎን ተሰልፎ ትግራይ ውስጥ እየተዋጋ መሆኑ ቢነገርም፣ ሲያስተባብሉ ቆይተው መጨረሻ ላይ በይፋ የአሥመራን ተሳትፎ ማረጋገጣቸው ይታወሳል።
ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ተቀስቅሶ በተፋፋመው ጦርነት ወቅት በተለያዩ ግንባሮች የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ሠራዊት አባላት ተቀናጅተው እየወጓቸው መሆኑን የህወሓት ባለሥልጣንት ሲከሱ ቆይተዋል።
በሁለቱ ወገኖች መካከል በደቡብ አፍሪካ እና በኬንያ የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎም ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ውጪ ያሉ ኃይሎች ከትግራይ እንዲወጡ እና የህወሓት ተዋጊዎችም ትጥቅ እንዲፈቱ መወሰኑ ይታወሳል።
በዚህ ስምምነት መሠረት ባለፈው ጥር ወር ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የኤርትራ ሠራዊት አባላት ይዘዋቸው ከነበሩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች ለቀው ሲወጡ መታየታቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ መናገራቸው ይታወሳል።
የኤርትራ ሠራዊት በትግራዩ ጦርነት ግድያ እና አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ፣ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እንዲሁም ዘረፋ እና የንብረት ውድመት ስለመፈጸሙ ምዕራባውያን ሲገልጹ ቆይተዋል።
ፕሬዝደንቱ ክሶቹ በሚመለከት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ በሰጡበት ወቅት “ውሸት ነው” ሲሉ አጣጥለዋቸዋል።
ከዚህ ባሻገር “ህወሓት በመቶ ሺህ የሚቆጠር ተዋጊ ከስሯል” ያሉት ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ፣ የህወሐት መሪዎች ከእነዚህ ሦስት ሙከራዎች “መማር አለባቸው” ያሉ ሲሆን፣ በኤርትራ በኩል ስለደረሰው ጉዳት ግን ምንም ያሉት ነገር የለም።
ለሁለት ቀናት ጉብኝት ባለፈው ሳምንት ናይሮቢ በነበሩበት ወቅት በተዘጋጀ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይም በኤርትራ ሠራዊት ላይ ስለደረሰው ኪሳራ በተደጋጋሚ ቢጠየቁም ሳይመልሱ ቀርተዋል።
ለሁለት ዓመታት በተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በጦርነቱ እና ጦርነቱ ባስከተላቸው ችግሮች ምክንያት መሞታቸው የሚነገር ሲሆን፣ ከባድ የንብረት ውድመት ወድሟል።
የኤርትራን ሠራዊት ጨምሮ በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑት ሁሉም ወገኖች ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸማቸውን የሰብአዊ መብት ተቋማት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ያወጧቸው ሪፖርቶች ያመለክታሉ።
አሰቃቂው ጦርነት በመንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መሪዎች መካከል በተደረሰ ስምምነት ከቆመ ወራት የተቆጠሩ ሲሆን፣ አብዛኛው የትግራይ ክልል አካባቢ ወደ መደበኛ ሕይወት እየተመለሰ መሆኑ ተዘግቧል።












