ፕሬዚዳንት ትራምፕ 10 ሺህ ወታደሮችን በሜክሲኮ ድንበር ለማሰማራት ያስባሉ ተባለ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ከጥቂት ቀናት በፊት የፕሬዚዳንትነቱን መንበር የተረከቡት ዶናልድ ትራምፕ ስደተኞች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ለመከላከል 10 ሺህ ወታደሮችን በሜክሲኮ ድንበር ለማሰማራት እንደሚያስቡ ከመንግሥት የውስጥ ማስታወሻ የተገኘ መረጃ አሳየ።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት 1,500 ወታደሮች አገራቸው ከሜክሲኮ የምትዋሰንበት ድንበሩን የማጠር ስራ እንዲያከናውኑ ቀደም ብለው ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
እነዚህ ወታደሮች "በህግ የማስከበር ስራ" ውስጥ እንደማይሳተፉ አንድ ወታደራዊ ምንጭ ተናግረዋል።
በድንበር የሚሰማሩ ወታደሮች ቁጥር 10,000 እንደሚሆን የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ የተመለከተው የውስጥ የመንግሥት ማስታወሻ ጠቁሟል።
ከትራምፕ በዓለ ሲመት በኋላ ከሁለት ቀናት በፊት ጥር 13/ 2017 ዓ.ም ያረፈበት የጉምሩክ እና የድንበር ጥበቃ የውስጥ ማስታወሻ ተቋሙን ለማገዝ 10 ሺህ ወታደሮችን ለመላክ እንደታቀደ አሳይቷል።
መጀመሪያ 1,500 ወታደሮች ወደ ካሊፎርኒያዋ ሳንዲያጎ እንዲሁም ወደ ኤልፓሶ፣ ቴክሳስ ይላካሉ ተብሎ ነበር። እነዚህም ወታደሮች በድንበር ላይ ተሰማርተው የሚገኙትን 2,500 ወታደሮችን እንዲያግዙ ነበር።
ከነዚህ ወታደሮች ውስጥ 1 ሺዎቹ የጦሩ አባላት 500ዎቹ ደግሞ የአየር ኃይሉ አባል ሲሆኑ ድንበሩን ከማጠር በተጨማሪ በተለያዩ ተልዕኮዎች ይሰማራሉ ተብሏል።
ይህ የውስጥ ማስታወሻ እንደሚያሳየው ይህ በድንበር ላይ የሚገኘው የአሜሪካ መከላከያ ወታደራዊ ሰፈር ከአገር እንዲወጡ የሚደረጉ ስደተኞችን ለመያዝ በማዕከልነት ሊያገለግል ይችላል ተብሏል።
ዶናልድ ትራምፕ ስደተኞች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ለማድረግ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ።
በተጨማሪም ሁለት ሲ-17 እና ሁለት ሲ 130 የተሰኙ አውሮፕላኖች እና ሄሊኮፕተሮች ወደዚሁ ድንበር እንደሚላኩ ተገልጿል።
የመከላከያ ተጠባባቂ ጸሐፊ ሮበርት ሳልስስ "ህገወጥ መጻተኞች" ሲሉ የጠሯቸውን ከ5,000 በላይ ስደተኞችን ወደ ሌሎች አገሮች ለማባረር መስሪያ ቤታቸው በወታደራዊ በረራዎች ያግዛል ብለዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ምክር ቤቱ "ህገወጥ ስደትን ለመቆጣጠር" በሚል የተሻሻለውን 'ሌክን ራይሊ አክት' የተሰኘውን ህግ አጽድቋል።
ስልጣን በተቆጣጠሩባት እለት በርካታ መመሪያዎችን ያስተላለፉት ትራምፕ ይህ የመጀመሪያ ድላቸው ነው ተብሏል። ምክር ቤቱ ይህንን ረቂቅ ህግ ማሳለፉን ተከትሎ ህግ ሆኖ ለመውጣት ትራምፕ መፈረም ይኖርባቸዋል።
ህጋዊ ሰነድ በሌለው ስደተኛ በተገደለችው ስም የተሰየመው ረቂቅ ህግ ባለስልጣናቱ በአንዳንድ ወንጀሎች የተከሰሱ፣ በቁጥጥር የዋሉ ወይም የተፈረደባቸውን ህጋዊ ሰነድ የሌላቸውን ስደተኞች እንዲይዙ ያስገድዳል።
ዶናልድ ትራምፕ የፕሬዚዳንትነታቸውን ቃለ መሐላ ከፈጸሙ ከሰዓታት በኋላ "የአሜሪካ ሉዓላዊነት እየተደፈረ ነው" ሲሉ በሜክሲኮ ድንበር ላይ ብሔራዊ የአደጋ ጊዜ ማወጃቸው ይታወሳል።
ትራምፕ በምረጡኝ ዘመቻቸው ስደትን ዋነኛ መቀስቀሻ አድርገውት የነበረ ሲሆን ድንበሩን ሙሉ በሙሉ ለመዝጋትና ተቆጣጣሪ ኃይልንም ለማጠናከር በተደጋጋሚ ቃል ሲገቡ ተሰምተዋል።












