በካፒቶል አመፅ ተሳትፋ በትራምፕ ይቅርታ የተደረገላት ሴት የፕሬዝደንቱን ውሳኔ አልቀበልም አለች

የፎቶው ባለመብት, AP
ከአራት ዓመታት በፊት በአሜሪካ መንግሥት መናገሻ ዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘው ካፒቶል ሂል ላይ አመፅ ከቀሰቀሱት መካከል አንዷ የትራምፕን ይቅርታ አልቀበልም ብላለች።
ግለሰቧ "የዚያን ቀን የፈፀምነው ተግባር ትክክል አልነበረም" በሚል የአዲሱን ፕሬዝደንት ይቅርታ አልቀበልም ያለችው።
ፓልመር ሄምፊል የተባለችው ግለሰብ ጥፋተኛ መሆኗን አምና የ60 ቀናት የእስር ፍርድ ተፈርዶባታል። በአውሮፓውያኑ ጥር 6/2021 በነበረው አመፅ የተሳተፉ ሰዎች ምሕረት ሊደረግላቸው አይገባም ስትል ለቢቢሲ ትናገራለች።
"ይህን ምሕረት መቀበል የካፒቶል ፖሊሶችን እንደመዝለፍ ነው፣ የሀገራችንን ሕግን እንዲሁም ሀገራችንን መናቅ ነው" ብላለች።
"ጥፋተኛ ነኝ ያልኩበት ምክንያት ጥፋተኛ ስለሆንኩ ነው። ምሕረትን መቀበል ማለት የሆነውን እንዳልሆነ አድርጎ ትርክቱን ማዛባት ነው።"
ሄምፊል በማኅበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች ዘንድ "ማጋ ግራኒ" የተሰኘው ቅፅል ስም ተሰጥቷት ነበር። ቅፅል ስሙ የትራምፕ ደጋፊ የሆኑ የዕድሜ ባለፀጋ የሚል ትርጓሜ አለው።
ነገር ግን አሁን የተቀየረች ትመስላለች።
"የዚያን ቀን ተሳስተናል። ሕግ ጥሰናል። በፍፁም ምሕረት ሊደረግልን አይገባም" ስትል ለቢቢሲ ትናገራለች።
ትራምፕ ሥልጣን በጨበጡ በመጀመሪያው ቀናቸው በካፒቶል አመፅ ተሳትፈዋል ለተባሉ 1600 ገደማ ሰዎች ምሕረት አድርገዋል።
በወቅቱ የ2020 የአሜሪካ ምርጫን በአመፅ ለመቀልበስ በሚል ነው ግለሰቦቹ ወደ ዋሺንግተን ዲሲ አቅንተው ካፒቶል ሂል የተባለውን ሕንፃ የወረሩት።
ዋይት ሐውስ ማክሰኞ በሰጠው መግለጫ "እኒህ ሰዎች ዓመታት እስር ቤት የከረሙ ናቸው። የእስር ጊዜያቸውን ተወጥተዋል" ብሏል።
ትራምፕ ለጥር 6 አመፀኞች ምሕረት ማድረጋቸው ከአንዳንድ ሪፐብሊካን ጭምር ትችት እንዲገጥማቸው አድርጓል።
የኖርዝ ካሮላይና ሴናተር ቶም ቲሊስ "በዚህ እርምጃ አልስማማም" ብለው የፕሬዝደንቱ ውሳኔ "በካፒቶል ሂል ደኅንነት ላይ ጥያቄ የሚጭር" መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላኛው የኦክላሆማ ሪፐብሊካን ሴናተር ጄምስ ላንፎርድ ሲኤንኤን ለተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ቃለ-ምልልስ የፕሬዝደንቱን ውሳኔ ተቃውመዋል።
"የፖሊስ መኮንን ላይ ጥቃት የምታደርስ ከሆነ ይህ ትልቅ ወንጀል ነው። ለፈፀሙት ወንጀል ደግሞ ዋጋ መክፈል ይገባቸዋል።"
አሜሪካዊያን ፕሬዝደንቱ የሚያስተላልፉትን ምሕረት አልቀበልም የማለት መብት በሕገ-መንግሥቱ ተጎናፅፈዋል ይላል የኮርኑል የሕግ ትምህርት ቤት መረጃ።
ምሕረት ከተደረገላቸው መካከል ጄኮብ ቻንስሊ የተባለው በአመፁ ምክንያት ስሙ የገነነ ግለሰብ የሚገኝበት ሲሆን 27 ወራት ከታሰረ በኋላ መፈታቱ ይታወሳል።
ምሕረት እንደተደረገለት ከጠበቃው የሰማው ጄኮብ ወደ ውጭ ወጥቶ "ነፃነት" እያለ ጩኸቱን እንዳሰመ ለቢቢሲ ይናገራል።












