የአሜሪካ ባለስልጣን የቻይናው ፊኛ መረጃ የመሰብሰብ አቅም ነበረው አሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከሰሞኑ በአሜሪካ ተመትቶ እንዲወድቅ የተደረገውና በስላላ የተጠረጠረው የቻይና ፊኛ መረጃዎችን የመሰብሰብ አቅም እንዳለው የአሜሪካ ባለስልጣን አስታወቁ።
ፊኛው “የስልላ ሥራ ለማከናወን” የሚያስችል በርካታ አንቴናዎች የተገጠሙለት መሆኑን አንድ ከፍተኛ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ባልደረባ ዝግ በሆነ ውይይት ላይ ተናግረዋል።
ሐሙስ ዕለት የአሜሪካ ህግ አውጪዎች የቻይናን ፊኛ በማውገዝ አስገዳጅ ያልሆነ ውሳኔ አሳልፈዋል።
ፊኛው ለስለላ ተግባር ይውላል መባሉን ቻይና አስተባብላለች።
ለአየር ንብረት ምርምር ብላ የሠራችው ፊና ከቁጥጥር ውጭ መሆኗንም ጨምራ ገልጻለች።
አሜሪካ በበኩሏ ፊኛዋ በአምስት አህጉራት መጠነ ሰፊ ስለላ ሥራ የምታከናውን መሆኗን አስታውቃለች።
የአሜሪካ ህዝብ እንደራሴዎች ፊኛዋን “የዩናይትድ ስቴትስን ሉዓላዊነት የጣሰች” ያሉ ሲሆን ጥቅም ላይ መዋሏንም 419 ለ 0 በሆነ ድምጽ ተቃውመዋል።
ጉዳዩ ዲፕሎማሲያዊ ችግር የፈጠረ ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ወደ ቻይና ሊያደርጉት የነበረውን ጉብኝትም ሰርዘዋል። ጉብኝቱ ከዓመታት በኋላ በከፍተኛ ደረጃ የተደረገ የአሜሪካ እና ቻይና ግንኙነት ይሆናል ተብሎ ነበር።
የአሜሪካ ጦር ፊኛውን አትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ ለመጣል ተዋጊ ጄት ለመጠቀም ተገዷል።
ቻይና መጠነ ሰፊ የስለላ ሥራ ስለሚያከናውኑ ፊኛዎች እንደማታውቅ ሐሙስ ዕለት አስታውቃለች። ጉዳዩ “አሜሪካ ቻይና ላይ የከፈተችው የህዝብ አስተያየት የመቀየር ጦርነት አካል ነው” ሲሉ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ማኦ ኒንግ ገልጸዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ባደረጉት ቃለመጠይቅ የቻይናው መሪ ዢ ጂንፒንግ “በርካታ ፈተናዎች” እየገጠሟቸው ነው ማለታቸው ላይም ቤጂንግ ምላሽ ሰጥታለች። እነዚህ አስተያየቶች “በከፍተኛ ደረጃ ኃላፊነት የጎደላቸው እና መሠረታዊ ዲፕሎማሲ መርህዎችን የጣሱ ናቸው” ሲሉ ሚንግ ተናግረዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ከፍተኛ ኃላፊ ሐሙስ ዕለት እንደገለጹት 60 ሜትር ያህል ቁመት ያለው ፊኛ በጸሐይ ኃይል የሚሠራ ነው። “በርካታ የስለላ ሥራ የሚሠሩ ሴንሰሮች” የተገጠሙለት እና የኮሙኒኬሽን መሣሪያዎችን ቦታ ለመለየት የሚችልም ነው።
ከፊኛው ጋር በተያያዘ ከቻይና ጋር በተባበሩ አካላት ላይ አሜሪካ እርምጃ ለመውሰድ እያሰበች መሆኗን ኃላፊው ተናግረዋል።
ይህ የአሜሪካ መረጃ በእርግጥም ፊኛዋ የስለላ መሆኗን ያሳያል ሲሉ አንድ ባለሙያ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
“እንደዚህ ዓይነት አንቴናዎች ለሌላ ዓይነት ሳይንሳዊ ሥራዎች ሳይሆን ለስለላ የሚውሉ ናቸው” ያሉት በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የሲቪል እና ሲስተምስ ምህንድስና ክፍል ባልደረባ የሆኑት ግሪጎሪ ፋልኮ ናቸው።
ቻይና ምን ዓይነት መረጃዎችን ለመሰብሰብ እንደፈለገች አይታወቅም ያሉት ባለሙያዎች ሆኖም ፊኛዋ በበረረችባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የጦር ካምፖች የሚገኙ የራዲዮ፣ የስልክ እና ሌሎች መገናኛዎችን እየሰለለች ይሆናል ሲሉ በአትላንቲክ ካውንስል የስኮውክሮፍት የስትራቴጂ እና ደህንነት ማዕከል ባልደረባ የሆኑት ማት ክሮኒንግ ገልጸዋል።
ፊኛዋ ያላት ትልቅ የጸሐይ ኃይል ማንመንጫዎች እና በአሜሪካ የአየር ክልል መብረር መቻሏ አስጊ ያደርጋታል ብለዋል ዶ/ር ፋልኮ።
ኤፍቢአይ የፊኛዋን የወዳደቁ ክፍሎች በመፈለግ መረጃዎችን የማጠናቀር ሥራ እያከናወነ ይገኛል።
የአሜሪካ የስለላ፣ ወታደራዊ እና የውጭ ፖሊሲ ባለስልጣናት ስለ ፊኛዋ ሐሙስ ዕለት ለኮንግረሱ አባላት ማብራሪያ መስጠት ጀምረዋል።
ይህ የሆነው የባይደን አስተዳደር በፖለቲካ ተቃዋሚዎቹ ዙሪያ በሚወሰደው እርምጃ ላይ የሚሰነዝረው ትችት እየጨመረ በሄደበት ወቅት ነው።
ረቡዕ ዕለት የሪፐብሊካን ሴናተሮች ማርኮ ሩቢዮ እና ሮጀር ዊከር በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ መንግስት ስለፊኛው በሰጠው ምላሽ ዙሪያ "የጠራ ግንዛቤ" እንደሌላቸው ተናግረዋል።












