በኢትዮጵያ የኢንተርኔት መልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያዎች ላይ ገደብ ተጣለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሃይማኖት ውጥረት በበረታባት ኢትዮጵያ ብዙዎች መልዕክት ለመለዋወጥ የሚመርጧቸው መተግበሪያዎች ላይ ገደብ ተጣለ።
ኔትብሎክስ የተሰኘው በዓለም ዙሪያ ያለውን የኢንተርኔት አገልግሎት አቅርቦት የሚከታተለው ተቋም ከትናንት ሐሙስ የካቲት 02/2015 ዓ.ም. ጀምሮ ፌስቡክ፣ ሜሴንጀር፣ ቴሌግራም እና ቲክቶክ ላይ ገደብ ተጥሏል ብሏል።
በተመሳሳይ በመዲናዋ በአዲስ አበባ ያሉ በርካታ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች የሚጠቀሟቸውን መልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያዎች ከኢንተርኔት ጋር ማገናኘት እንዳልቻሉ እየገለጹ ይገኛሉ።
ሌሎች ደግሞ እንደ ፌስቡክ ያሉ መተግበሪያዎችን እየተጠቀሙ ያሉት ከመደበኛው መስመር ውጪ በተዘዋዋሪ ‘ቪፒኤን’ በተባለው መተግበሪያ በኩል እንደሆነ እየገለጹ ነው።
ኔትብሎክ ከላይ የተጠቀሱት መተግበሪያዎች ክልከላ የተደረገባቸው በመንግሥት ባለቤትነት በሚተዳደረው የኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢው በሆነው ኢትዮቴሌኮም ነው ብሏል።
ግዙፉ የቴሌኮም አግልገሎት አቅራቢ የሆነው ኢትዮቴሌኮም ግን ስለክስተቱ ለተጠቃሚዎቹ አስካሁን ያሰወቀው ነገር የለም።
የኢንተርኔት አገልግሎት አቅርቦት መቆጣጠሪያዎች እንዳሳዩት የፌስቡክ፣ የሜሴንጀር፣ የቲክቶክ እና የቴሌግራም መልዕክት መለዋወጫዎች ዕቀባ እንደተጣለባቸው ኔትብሎክስ አረጋግጧል።
ኔትብሎክስ እንዳለው ይህ የኢንተርኔት አገለግሎት ዕቀባው የተጣለው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተከሰተውን ችግር ተከትሎ በመንግሥት ላይ ተቃውሞዎች እየተሰማ ባለበት ጊዜ ነው።
በዓለም ዙሪያ የኢንትርኔት መዘጋት እና የተወሰኑ አገልግሎቶች እቀባ በሚያጋጥሙባቸው አካባቢዎች ኢንትርኔትን ለመጠቀም የሚያስችሉ ቪፒኤን የሚባሉትን መተግበሪያዎች አጠቃቀም የሚከታተለው ‘ቶፕ10ቪፒኤን’ የተባለው ድረገጽ በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቪፒኤን የመጠቀም ፍላጎት እንዳለ ገልጿል።
ድረገጹ ያለፉትን 28 ቀናት የቪፒኤን ፍላጎት በዛሬ ዕለት አርብ እኩለ ቀን ድረስ ካለው ጋር በማነጻጸር ባወጣው መረጃ መሠረት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የቪፒኤን ፍላጎት በ414 በመቶ የጨመረ ሲሆን፣ ይህም ከአማካዩ የቪፒኤን ፍላጎት በ1,430 ፐርሰንት ማሻቀቡን አመልክቷል።
ይህ በኢትዮጵያ የቪፒኤን መጠቀሚያ ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያሻቅብ ምክንያት የሆነው፣ በአገሪቱ ውስጥ የተከሰተውን ሃይማኖታዊ ቀውስ ተከትሎ ባለሥልጣናት በፌስቡክ፣ በቴሌግራም እና በቲክቶክ ላይ እገዳዎችን መጣላቸውን ተከትሎ መሆኑን ድረገጹ ገልጿል።
በኢትዮጵያ አለመረጋጋት ሲከሰት እንዲሁም ብሔራዊ ፈተና በሚሰጥበት ወቅት የማኅበራዊ ትስስር መድረኮች መተግበሪያዎች ላይ ገደብ መጣል አንዳንዴም ኢንተርኔትን ሙሉ በሙሉ በመንግሥት መዘጋቱ የተለመደ ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት በአሁኑ ወቅት የኢንተርኔት አገልግሎት ላይ ገደብ ስለመጣሉ ያለው ነገር ባይኖርም፣ ክልከላው ግን ሰሞኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያጋጠመውን ችግር ተከትሎ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።
ይህ የኢንተርኔት አገልግሎት ላይ ገደብ መጣሉ የተሰማው ከሁለት ሳምንት በፊት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተከሰተው ቀውስ እየተባባሰ የቤተክርስቲያኗ መሪዎች እና ምዕመናን በመንግሥት ላይ ጠንካራ ተቃውሞ እያሰሙ ባሉበት ወቅት ነው።
ቤተክርስቲያኗ የመንግሥት ጣልቃ ገብነትን ለመቃወም የጠራችው ሰልፍ እውቅና እንደሌለው መንግሥት ከገለጸ በኋላ፣ ቤተ-ክርስቲያኗ ዳግም ባወጣችው መግለጫ መንግሥት ያስተላለፈውን የሰልፍ ክልከላ እንደማትቀበለው አስታውቃለች።
ቪፒኤን ምንድነው?
በኢንተርኔት አጠቃቀም ላይ ገደብ ሲጣል ሰዎች ክልከላውን ለማለፍ ቪፒኤን (VPN- Virtual Private Newtwork) ይጠቀማሉ።
ባለፉት ዓመታትም በኢትዮጵያ የቪፒኤን ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ የጨመረባቸው ወቅቶች ነበሩ።
ለማሳያም ባፈው ዓመት ታኅሳስ ወር ከ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና መጀመር ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ የኢንተርኔት አጠቃቀም ላይ ገደብ መጣሉን ተከትሎ የቪፒኤን (VPN) አገልግሎት ፍላጎት በ5109 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ቶፕቪፒኤን.ኮም (Top10VPN.com) የተባለ ድርጅት አስታውቆ ነበር።
ቨርቿል ፕራይቬት ኔትዎርክ የኢንርኔት ደኅንነት የሚሰጥ፣ ግለኝነትን የሚጠብቅ እና ነጻነት የሚሰጥ መተግበሪያ (ሶፍትዌር) ነው።
ቪፒኤን መተግበሪያ በስልክዎ ወይም በኮምፒውተርዎ መካከል እና በሌላ ቦታ በሚገኝ ከመረጡት የቪፒኤን ሰርቨር ጋር ግንኙነት ይፈጥራል።
በዚህም ቪፒኤኑ የተጠቃሚውን የኢንርኔት አድራሻ (አይፒ አድሬስ) እና መገኛ ቦታ በመቀየር ክልከላዎችን አልፎ እንዲጠቀም ያስችላል።
ቪፒኤን መጠቀም፤ መጎብኘት የማይቻሉ ድረ ገጾችን ለማየት፣ መተግበሪያዎች እንዲሠሩ ለማደረግ እንዲሁም የኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢዎች (እንደ ኢትዮቴሌኮም ያሉ) ተጠቃሚዎች የሚጎበኙት ድረ ገጽ መረጃ እንዳይኖራቸው ያደርጋል።
Top10VPN.com በብዙ ቪፒኤኖች ላይ ፍተሻዎችን አድርጌ ለይቻለሁ ያላቸውን ቪፒኤኖችን አጋርቷል።
ቡድኑ ክፍያ ከሚጠየቁባቸው ቪፒኤኖች መካከል የተመረጡ ናቸው ካላቸው መካከል ኤክስፕረስቪፒኤን (ExpressVPN)፣ ኖርድቪፒኤን (NordVPN) እና ሳይበርጎስት (CyberGhost) ይጠቀሳሉ።
ክፍያ የማይጠይቁ፣ ደኅንነታቸው የተረጋገጠ እና የተሻለ አገልገሎት ይሰጣሉ ካላቸውን የቪፒኤን አገልግሎቶች መካከል ደግሞ ዊንክራብ (Windcribe) እና ፕሮቶንቪፒኤን (ProtonVPN) ተጠቃሽ ናቸው።












