የአውሮፓ ኅብረት የድንበር ኤጀንሲ ለስደተኞች ጀልባ ያቀረብኩት ድጋፍ በግሪክ ችላ ተብሏል አለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በቅርቡ ሰጥማ የበርካቶች ሕይወት የተቀጠፈባትን የስደተኞች ጀልባ ቀድሞ ለመከታተል የሚረዳ አውሮፕላን ለመላክ ለቀረበላት ጥያቄ ግሪክ ምላሽ አለመስጠቷን የአውሮፓ ኅብረት የድንበር ባለሥልጣናት ተናገሩ።
ባለፈው ሳምንት በደረሰው የጀልባ አደጋ እስካሁን ቢያንስ 82 ሰዎች መሞታቸው የታወቀ ሲሆን ሌሎች 500 ሰዎች ሳይሰምጡ እንዳልቀረ የተባበሩት መንግሥታት ገልጿል።
በዚህም ግሪክ ላጋጠመው ችግር ምላሽ ለመስጠት በበቂ ሁኔታ ባለመስራቷ ትችት አጋጥሟታል።
ግሪክ ጀልባዋ በአስተማማኝ እና በተረጋጋ ጉዞ ላይ እንደነበረች የገለጸች ቢሆንም ቢቢሲ የስደተኞች ጀልባዋ ከመገልበጧ በፊት ባሉት ሰዓታት ጉዞዋ ተገ'ቶ እንደነበር ማወቅ ችሏል።
በርካታ ስደተኞችን ያሳፈረችው የአሳ ማስገሪያ ጀልባ ከሊቢያ ተነስታ ወደ ግሪክ እያቀናች ነበር።በዓለም አቀፍ የውሃ አካል ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየችውም በአውሮፓውያኑ ሰኔ 13 ጠዋት ላይ ነበር።
ይህንን ቀድሞ የተመለከተው በአውሮፓ ኅብረት የድንበርና ጠረፍ ጥበቃ ኤጀንሲ (ፍሮንቴክስ) ሥር የሚተዳደረው አውሮፕላን ቢሆንም በወቅቱ አውሮፕላኑ ነዳጅ መሙላት አስፈልጎት ነበር።
ፍሮንቴክስ እንደሚለው ሁኔታውን ለመከታተል አውሮፕላኑን መልሶ ወደ አነስተኛ ጀልባዋ ለመላክ ጥያቄ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም የግሪክ ድንበር ጠባቂ ምንም ምላሽ አልሰጡኝም ብሏል።
ይሁን እንጂ የግሪክ ባለሥልጣናት ያጋጠመው አሳዛኝ ክስተት እንዳይፈጠር ፈጣን እርምጃ አልወሰዱም በሚል የቀረበባቸውን ክስ ውድቅ አድርገውታል።
ባለሥልጣናቱ ስደተኞቹን ለመርዳት ጥረት መደረጉን ገልጸው፣በጀልባዋ ላይ የነበሩ ስደተኞች ጣልያን መግባት እንደሚፈልጉና እንዲተዋቸው ለባሕር ዳርቻ ጠባቂዎቹ እንደነገሯቸው ጠቅሰዋል።
ሆኖም ቢቢሲ አደጋው በተከሰተበት ዕለት በሌሎች መርከቦች እንቅስቃሴ ላይ የሠራው ትንተና ጀልባዋ ከመገልበጧ በፊት ቢያንስ ለሰባት ሰዓታት ለመጓዝ ተቸግራ እንደነበር አመልክቷል።
የአውሮፓ ኅብረት የድንበር ኤጀንሲ ተጨማሪ የአየር ድጋፍ ለማድረግ አቅርቤ ለነበረው ጥያቄ ምላሽ አላገኘሁም ሲል ላቀረበው ክስ የግሪክ የባሕር ዳርቻ ጠባቂ እስካሁን አስተያየት አልሰጠም።
ጀልባዋ ከዐሥር ቀን በፊት ከባሕር ዳርቻዋ ከተማ ፕይሎስ ደቡብ ምዕራብ 80 ኪሎሜትር ርቀት ላይ መስመጧን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ከ100 በላይ ሰዎችን መታደግ የተቻለ ሲሆን 100 የሚሆኑ ሕጻናትን ጨምሮ 750 የሚሆኑ ሰዎች በጀልባዋ ላይ ተሳፍረው እንደነበር ከአደጋው የተረፉት ስደተኞች ገምተዋል።
የፓኪስታን የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ራና ሳናውላህ፣ ቢያንስ 350 የሚሆኑ ፓኪስታናውያን በጀልባዋ ላይ እንደነበሩ ገልጸው፣ “ከዚህ በፊት በሽብር ጥቃትም ቢሆን በዚህ መጠን ጉዳት ደርሶ አያውቅም” ብለዋል።
ሳይሞቱ እንዳልቀረ ከተገለጸው ስደተኞች መካከል ግብጻውያን እና ሶሪያውያንም ይገኙበታል።
በተያያዘም ሰኞ ዕለት ዘጠኝ ግብጻውያን ወንዶች በግድያ ፣ሕይወትን ለአደጋ በማጋለጥ እና በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በግሪኳ ከተማ ካላማታ ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር።
ሁሉም ግን በቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ አይደለንም ብለዋል።












