በግሪክ የጀልባ አደጋ እስከ 500 የሚደርሱ ስደተኞች ጠፍተዋል- ተመድ

የጀልባ አደጋ

የፎቶው ባለመብት, ERT/GEETHA

በግሪክ ቢያንስ ለ78 ስደተኞች ህይወት መቀጠፍ ምክንያት በሆነችው የጀልባ አደጋ 500 ያህል ስደተኞች መጥፋታቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ቢሮ አስታወቀ።

ከጠፉትም መካከል በርካታ ቁጥር ያላቸው ሴቶች እና ህጻናት እንደሚገኙበት ቃለ አቀባዩ ጄረሚ ሎረን ተናግረዋል።

አሰቃቂው አደጋ ያስከተለውን የህይወት መጥፋትም ህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ለፍርድ ማቅረብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ትልቅ ስፍራ ሊሰጠው እንደሚገባ አመላካች ነው ብለዋል።

ሆኖም በአሁኑ ወቅት ስደተኞቹን መፈለግና ህይወታቸውን መታደግ ቀዳሚ ሰብዓዊ ተግባር መሆኑንም ግልጽ አድርገዋል።

የአለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ከተመድ የሰብዓዊ ቢሮ ጋር በጋራ በሰጡት መግለጫ የፍለጋ ስራው ሞቶችን ለመከላከል መሆን እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከ750 በላይ ስደተኞችን አሳፍራ ከሊቢያ ወደ ጣልያን እያመራች የነበረችው የዓሳ ማጥመጃ ጀልባ በደቡባዊ ግሪክ አደጋ የደረሰባት ከሰሞኑ ነበር።

በዚህም ዓደጋ ላይ የባህር ዳርቻ ጠባቂዎች ተሳትፎ አድርገዋል የሚለው ሪፖርት እያወዛገበም ይገኛል።

የግሪክ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር ዮአኒስ ሳርማስ ለጀልባዋ የመስጠም ምክንያት እንደሆነ ለማወቅ “በጥልቀት ምርመራ” እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።

የግሪክ ባለስልጣናት ረቡዕ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ላይ መስጠሟንና የባህር ዳርቻ ጠባቂዎችም ገመድ አያይዘውባት እንደነበር የሚገልጹ ሪፖርቶችን ውድቅ አድርገዋል።

ከአደጋው ከተረፉት 104 ስደተኞች መካከል ሁለቱ ጀልባዋ በከፍተኛ ሁኔታ ተጨናንቃ እንደነበርና በአደጋው ወቅት በርካታ ጊዜ መገልበጧንም ተናግረዋል።

መጀመሪያ ላይ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች ጀልባዋን በርቀት ሲከታተሏት እንደነበር ጠቅሰዋል።

ነገር ግን የግሪክ ጋዜጣ ካትሜሪ ምንጭን ጠቅሶ እንደዘገበው ጠባቂዎች ጀልባዋን በገመድ በማሰር የስደተኞቹን ሁኔታ መፈተሻቸውንና በጀልባዋ ላይ ያሉትም ስደተኞች ገመዱን ፈትተው ወደ ጣሊያን ለማቅናት መንገድ ጀምረዋል ብሏል።

ይህ ክስተት በጀልባዋ ላይ አደጋ ከመድረሱ ከሶስት ሰዓት በፊት ከምሽቱ አምስት ሰዓት ላይ ተከስቷል ተብሏል።

የመንግስት ቃል አቀባይ ኢሊያስ ሲያካንታሪስ የባህር ዳርቻ ጠባቂዎች ገመዱን በጀልባዋ ላይ ያሰሩት ስደተኞቹ እርዳታ ይፈልጉ እንደሆነ ቀርቦ ለመጠየቅ እንዲያስችላቸው ነው ብለዋል።

ነገር ግን ጀልባዋን ጎትቶ ለመጣል ወይም ለመገልበጥ አላሰሩም ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

“ስደተኞቹ እርዳታን አንሻም አሉ። ወደ ጣሊያን እንሄዳለን” ብለው መንገዳቸውን ቀጠሉ ብለዋል።