በግሪክ የጀልባ አደጋ ቢያንስ 79 ስደተኞች ሲሞቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጠፍተዋል

ሄለኒክ የተሰኘው ጀልባ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በደቡባዊ ግሪክ የባህር ዳርቻ የዓሳ ማጥመጃ ተገልብጣ ቢያንስ 79 ስደተኞች ሲሞቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ መጥፋታቸው ተነገረ።

ከመቶ በላይ የሚሆኑ ስደተኞችን ማትረፍ ቢቻልም ከአደጋ የተረፉ እና የግሪክ ባልስልጣናት በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በጀልባው ውስጥ እንደነበሩ ተናግረዋል።

ጀልባዋ ከሊቢያ ወደ ጣልያን እየተጓዙ የነበሩ ስደተኞን ጭና እንደነበርም ተነግሯል።

በጀልባዋ ተሳፍረው ከነበሩት መካከልም አብዛኛዎቹ በ20ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወንዶች ናቸው ተብሏል።

ከአደጋ የተረፉ ስደተኞች ከ500 እስከ 700 የሚደርሱ ስደተኞች በጀልባዋ ላይ ተሳፍረው እንደነበር ተናግረዋል።

የአካባቢው የጤና ዳይሬክተር ያንኒስ ካርቬሊስ ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ አሳዛኝ እልቂት ሊያጋጥም እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

“በጀልባዋ ላይ ተሳፍረው የነበሩ መንገደኞች ቁጥር ከአቅሟ በላይ በሆነ ሁኔታና ከሚፈቀደውም በላይ ነው” ብለዋል።

ይህ በግሪክ ውስጥ ካጋጠመ የስደተኞች አደጋ የከፋ ነው ያለው የግሪክ መንግሥት ሶስት የሃዘን ቀናትም አውጇል።

ጀልባዋ ከፒሎስ ደቡባዊ ምዕራቅ አቅጣጫ 80 ኪሎሜትር ርቀት ላይ እንደተጓዘችና የባህር ዳርቻ ጠባቂዎችንም እርዳታ አንቀበልም ማለታቸውም ተነግሯል።

የባህር ጠረፍ ጠባቂ እንዳስታወቁት ጀልባዋ ማክሰኞ አመሻሽ ላይ አለም አቀፍ የውሃ አካል በሆነው ውቅያኖስ ላይ ታይታለች ተብሏል። የአውሮፓ ህብረት የድንበር ኤጀንሲ የሆነው ፍሮንቴክስ አውሮፕላን ጀልባዋን ማየቱን ተዘግቧል።

በጀልባዋ ተሳፍረው ከነበሩት ስደተኞች ውስጥ አንዳቸውም የህይወት አድን ጃኬቶችን አለመልባሳቸውንም ጠባቂው ተናግረዋል።

የመርከብ ሚኒስቴርን መረጃ በማጣቀስ የግሪክ የመንግሥት ሚዲያ ኢአርቲ ባለስልጣናቱ ከጀልባዋ ኃላፊዎች ጋር በተደጋጋሚ በስልክ ተገናኝተው እርዳታ ለመለገስ ጥያቄ ቢያቀርቡም “ወደ ጣልያን ከመሄደው ውጭ ምንም አንፈልግም” መባላቸውን ዘግቧል።

የሃገሪቱ ሚዲያዎች እንደዘገቡት ስደተኞቹ ለቀናት መጓዛቸውንና ማክሰኞ ከሰዓት በኋላም ምግብ እና ውሃ በሚያቀርብ የማልታ ካርጎ መርከብ ጀልባዋን ቀርቧት እንደነበር ነው።

ረቡዕ በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር ከሌሊቱ 7፡40 ላይ በጀልባው ላይ ያለ አንድ ሰው ሞተር መበላሸቱን ለግሪክ የባህር ዳርቻ ጠባቂ ማሳወቁ ተነግሯል።

ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ጀልባዋ ሙሉ ለሙሉ ለመስጠም ከአስር እስከ አስራ አምስት ደቂቃ ብቻ ነው የወሰደባት ተብሏል።

የፍለጋ እና ነፍስ የማዳኑ ስራ ቢቀጥልም ያለው ከፍተኛ ንፋስ ሁኔታውን ማወሳሰቡ ተነግሯል።