ቺቺኒያዊው የምክር ቤት አባል በዩክሬን ጦርነት ቆስለዋል መባሉ እያነጋገረ ነው

የቺቺኒያ ከፍተኛ የጦር አዛዥና የሩሲያ የምክር ቤት አባል የሆኑት አዳም ደሊምክሃኖቭ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የቺቺኒያ ከፍተኛ የጦር አዛዥና የሩሲያ የምክር ቤት አባል የሆኑት አዳም ደሊምክሃኖቭ በጦርነቱ ቆስለዋል መባሉ እያነጋገረ ነው።

የምክር ቤት አባሉ መቁሰላቸው ሪፖርቶች መውጣቱን ተከትሎም የስራ ባልደረቦቻቸው በህይወት እንዳሉና ደህና መሆናቸውን ተናግረዋል።

አዳም ደሊምክሃኖቭ የዝነኛው የቺቺኒያ መሪ ራምዛን ካዲሮቭ የቅርብ አጋር ናቸው።

መሪው “ውድ ወንድሜን ፈልጉልኝ” ሲሉም ለዩክሬን የስለላ ድርጅት ተማጽነዋል ተብሏል።

የቺቺኒያ ልዩ ኃይሎች ለሩሲያ በመወገን በዩክሬን ጦርነት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በአሁኑ ወቅት ደብዛቸው ጠፍቷል የተባሉት እኚሁ የፓርላማ አባል ሩሲያ የማሪዮፖልን ወደብ ለመያዝ ለወራት ስትታገልም የቺቺኒያን ጦር በማዘዝ ተሳታፊ ነበሩ።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ከዩክሬን በተሻገሩ ታጣቂዎች ጥቃት ተፈጽሞባታል የተባለውን የሩሲያን የቤልጎሬድ የድንበር ግዛት አስተዳዳሪ ጋር መገናኘታቸውን አሳውቀዋል። አካባቢውንም ከጥቃት ለመጠበቅ እንደሚረዱ ቃል መግባታቸውም ተነግሮ ነበር።

ሆኖም ረቡዕ ዕለት የፓርላማ አባሉ የት እንዳሉ አለመታወቁ እንቆቅልሽ ሆኗል።

የሩስያ ወታደራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ዝቬዝዳ የጦር አዛዡ “በህይወት ቢኖሩም ቆስለዋል” ሲልም የሩሲያ ምክር ቤት መረጃን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።

ዝቬዝዳ በዚሁ ዘገባው ተገድለዋል የሚሉ አንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያ ሪፖርቶችን ውድቅ አድርጓል።

የዩክሬን ምንጮች በቺቺኒያው አኽማት ልዩ ኃይል ላይ ጥቃት መፈጸሙን ጠቅሰዋል።

ቢቢሲ ያላረጋገጠመው ይህ ጥቃት ተፈጸመ የተባለው በዩክሬን ደቡባዊ ዛፖሪዝሂዝያ ክልል ራቅ ብሎ በሚገኘው የባህር ዳርቻዋ ፕሪሞርስክ ውስጥ ነው።

የቺቺኒያው መሪ ራምዛን ካዲሮቭ “ውድ ወንድማቸውን” ላገኘ ከፍተኛ ሽልማት እንደሚሰጡ ተናግረው ከዚያም ባለፈ የዩክሬን የስለላ መዋቅርንም በመፈለጉ እንዲተባበራቸው ጠይቀዋል።

ይሁን እንጂ የሩሲያ ባለስልጣናት እንዲህ ያለ ከፍተኛ የጦር አዛዥ ቆስለዋል የሚለውን ዘገባም ለማስተባባል ብዙ ጥረቶችን አድርገዋል።

የፓርላማ አባሉ ዲሚትሪ ኩዝኔትሶቭ የሩሲያ ምክርቤት ዱማ አፈ ጉባዔን ቭያቼስላቭ ቮሎዲንን ዋቢ በማድረግም ከጦር አዛዡ አዳም ጋር ማውራታቸውንና “በህይወት እንዳሉ እና ደህና” መሆናቸውን ነግረውኛል ብለዋል።

ከሰዓታት በኋላ የቺቺኒያው መሪ ንግግራቸውን በመቀየር አጋራቸው “እንዳልቆሰሉና” ዩክሬናውያን እየዋሹ ነው ሲሉም ተናግረዋል ተብሏል።

“ይህ ሃሰተኛ ዜና መነገር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እንዳልቆሰለ አውቃለሁ። ነገር ሁሉንም ሰዎች በዋናነት ዩክሬናውያን ሚዲያቸው ምን ያሀል እንደዘቀጠ ለማየት ወሰንኩ” ብለዋል የቺቺኒያው መሪ

የክሬምሊን ቃለ አበቃይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ በበኩላቸው የተፈጠሩ ክስተቶችን በጥንቃቄ እየተከታተሉ እንደሆነና ስለተፈጠረው ነገር ማብራሪያ እየጠበቁ መሆኑን ተናግረዋል።