ትግራይ፡ ‘ወይ አይገድል ወይ ነፍስ አይዘራ፣ ጥቂት እርዳታ ስንጠብቅ ሳር አከልን’

እርዳታ የሚቀበሉ ሰዎች በትግራይ

በትግራይ በተቀሰቀሰው ደም አፋሳሽ ጦርነት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ሞቶ ሚሊዮኖች ተፈናቅለው እርዳታ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።

የፕሪቶሪያ ስምምነትን ተከትሎ አንጻራዊ ሰላም እና የንግድ እንቅስቃሴ ቢታይም በሺዎች የሚቆጠሩ በተለይም ከመኖሪያ ቤታቸው የተፈናቀሉ ሰዎች አሁንም አስቸኳይ እርዳታ በመጠባበቅ ላይ ናቸው።

የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የእርዳታ እህል ለገበያ አቅርበዋል መባሉን ተከትሎ፣ ዩኤስኤአይዲ እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከሁለት ወራት በፊት ዕርዳታ ሲያቆሙ ተረጂዎች ከፍተኛ ችግር ውስጥ መግባታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (ዩኤስኤአይዲ) እንዳስታወቀው ስንዴው በትግራይ አንዳንድ ከተሞች ውስጥ በግልጽ ገበያ ላይ ሲሸጥ ታይቷል።

በተጨማሪም ለአንድ ወር 134,000 ድሆችን ሊቀልብ የሚችል የእርዳታ እህል፣ ከትክክለኛው ዓላማ ውጪ በጅምላ አከፋፋይ ድርጅቶች ውስጥ ሲፈጭም መገኘቱ ተነግሯል።

በዚም ምክንያት ድርጅቶቹ የእርዳታ አገልግሎታቸውን አቁመዋል፤ ወንጀሉን የፈጸሙ ግለሰቦች ማን እንደሆኑ እስኪጣራ ድረስ እርዳታ ጠባቂው ሕዝብ ኑሮ እያሽቆለቆለ እንደመጣ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ከሁለት ዓመታት ጦርነት በኋላ የምግብ ዋስትናው እጅግ የከፋ ደረጃ ላይ ደርሷል፤ በትግራይ ያለው የተደራሽነት ችግር እና የሕይወት አድን የምግብ ርዳታ ስርቆት ተጎጂዎችን እንደገና ስጋት ላይ እየጣለ ነው ሲል የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (ዩኤስኤአይዲ) ገልጿል።

የስምንት ልጆች እናት የሆነችው ወይዘሮ ምፅላል ተኽላይ እርዳታ ሳትጠብቅ ራሷን ችላ የኖረችበትን ጊዜ ታስታውሳለች።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“በምዕራብ ትግራይ ከሚኖሩት ቤተሰቦቼ ጋር ሰርቼ፣ የምለብሰውን መርጬ ነበር የምኖረው። ሃብቴም ንብረቴም ተዘርፏል። እኔ ከሞት አምልጬ መቀለ መኖር ከጀመርኩ ሁለት ዓመት አለፈኝ፤ ወይ አይገድል ወይ ነፍስ አይዘራ ጥቂት እርዳታ ስንጥበቅ ሳር አከልን” በማለት የተጋፈጠችውን ችግር ትገልጻለች።

ሓደራ አጽብሃ የሦስት ልጆች እናት ነች። ልጆቿ በምግብ እጦት እየተሰቃዩ በመሆኑ ለልመና ተዳርጋለች። ባለቤቷ በህመም ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየ በኋላ ሕይወት ሊቋቋሙት የማይችሉት ተራራ ሆኖባታል።

“ትምህርት መጀመሩን እያወቅኩ ልጆቼን በባዶ ሆድ መላክ አልፈለግኩም። እርዳታ በመቋረጡ ከባድ ችግር ውስጥ ገብተናል። እኔ ብቻ አይደለሁም፤ እንደእኔ የተቸገሩ ጎረቤቶች አሉኝ” ትላለች።

ማዕከላዊ ዞን ወረዳ ወረዳ አሕፈሮም ውስጥ ከምትገኘው ገርሁ ስርናይ አካባቢ ተፈናቅለው መቀለ የሚገኙት ተክላይ ዉነህ፣ አማቾቻቸው ቤት ተጠግተው መኖር ከጀመሩ አንድ ዓመት አልፏቸዋል።

ተክላይ 51 ዓመታቸው ነው። ነገር ግን እግራቸው እና አይናቸው ላይ ጉዳት ስላለባቸው የፈለጉትን ያህል መንቀሳቀስ አይችሉም። ተክላይ የአስም ታማሚ ቢሆኑም ለመድኃኒት የሚሆን ገንዘብ የላቸውም።

“ቤቱን ያከራዩኝ ቤተሰቦች [ኪራይ ሳያስከፍሉ] ምግብ ችለው አቆይተውኛል” በማለት ያመሰግናሉ።

ተክላይ ግን ከዚህ በፊት ከሁለት ጊዜ በላይ የእርዳታ እህል አግኝተው እንደማያውቁ ይናገራሉ።

ባለትዳሮቹ አቶ ተስፋይ ባህረ እና ወይዘሮ ለምለም የዕብዮ፣ መምህራን ናቸው።

ደሞዝ ለሁለት ዓመታት አልተከፈላቸውም። በቤታቸው ካለው ረሃብ የበለጠ የሚያሳስባቸው የ12 ዓመት ልጃቸው ሥር በሰደደ ሕመም መሰቃየቱ ነው።

“የነበረንን ንብረት ሸጠን ቀለብ ችለን የልጃችንን ጤና ለመመለስ ብዙ ጥረት አድርገናል፤ ማንም የረዳን የለም። የእርዳታ እህሉ ትንሽ ያግዘን ነበር። ወሬው ከጠፋ ግን ወራት ተቆጠሩ። አሁን ተስፋ ቆርጠናል” ይላል መምህር ተስፋይ።

እርዳታ በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ እናቶች

በክልሉ ዋና ከተማ መቀለ የሚገኙ ነዋሪዎች ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ ኑሯቸውን ለማሸነፍ እየታገሉ እንደሆነ ይናገራሉ።

ነገር ግን የመንግሥት ሠራተኛው የሦስት ወር ደሞዝ አንድ ጊዜ ብቻ ከተቀበለ በኋላ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ገብቷል።

ጡረተኞች “ገንዘባችንን ስጡን” ሲሉ ባለፈው ሳምንት በመቀሌ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል።

ይህ ሁሉ በእርዳታ መቆራረጥ እየተባባሰ የመጣ ችግር መሆኑን ቢቢሲ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ገብረዮሐንስ እጅጉ በከተማዋ በተደረገ ሰልፍ ላይ ወጥቶ ቅሬታውን ገልጿል።

“ወይ ገንዘባችንን አይሰጡንም ወይም ዕርዳታውን አያከፋፍሉም፤ ከአምስቱ ልጆቼ ጋር ከባድ ችግር ውስጥ ነን” ይላል።

ይህ ሁሉ ሲሆን በመንግሥት ባለሥልጣናት በኩል ምንም አይነት መፍትሄ አልተገኘም።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ቅሬታዎችን ከመስማት በቀር ምንም ማድረግ አልቻለም።

የፌደራል መንግሥት የሠራተኞቹን ወርሃዊ ደሞዝ ለመክፈል ዓመታዊ በጀት አልመደበም።

በመሆኑም በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ያሉ መምህራን እየተራቡ እንዴት ማስተማር እናስተምር በሚል ሥራቸውን ለመተው እያመነቱ እንደሆነ መሰማቱ ይነገራል።

እናቶች እና ህፃናት ለምግብ እጥረት የበለጠ ተጋላጭ መሆናቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ መረጃ ያሳያል።

ከጥር ወር ጀምሮ 13 ህጻናት በምግብ እጦት ሞተዋል ሲል ከአይደር ከፍተኛ ህክምና ማዕከል የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያወጣው ሪፖርት እንደሚያመለክተው በትግራይ ክልል ሁለት ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች እና እርዳታ ጠባቂዎች አሉ።

ነፍሰ ጡር እናቶች፣ ጨቅላ ህጻናት እና የሚያጠቡ እናቶች በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸው ይነገራል።

ትግራይ የሁለት ዓመት ጦርነት ካስከተለው ጉዳት ለማገገም እየጣረች ባለችበት በዚህ ወቅት 84 በመቶ የሚሆነው የክልሉ ሕዝብ ለምግብ እጥረት የተጋለጠ ሆኗል።

በኢትዮጵያ በትግራይ ክልል በተከሰተው ጦርነት እና በቅርቡ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።

አሜሪካ ለኢትዮጵያ ከ1.8 ቢሊዮን ዶላር በላይ እርዳታ በመስጠት ትልቁን የሰብዓዊ እርዳታ የምትሰጥ ለጋሽ አገር ናት።

ይሁን እንጂ የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና ዩኤስኤአይዲ ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን ድጋፍ ማቋረጣቸውን በቅርቡ እንዳስታወቁ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) የእርዳታ አቅርቦቱ መቋረጥ “የጅምላ ውሳኔ” መሆኑን በመጥቀስ፣ በዚህም ሚሊዮኖችን መቅጣት “ፖለቲካዊ እንጂ ሰብአዊ ገጽታ የለውም” በማለት ተቃውመውታል።

ውሳኔው እርዳታ የሚሹ ሚሊዮኖችን ለችግር የሚዳርግ እና ለቀውስ የሚያጋልጥ በመሆኑ የገለጸው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ለጋሾቹ ውሳኔያቸውን እንዲጤኑት ጠይቋል።