ሰው የማይራብባት ከተማ

አምሪሳር ትባላለች። ሁለት ሚሊዮን ሰዎች ይኖሩባታል። በሰሜን ሕንድ የምትገኝ ከተማ ናት።
አምሪሳር በጣፋጭ ምግብ፣ በታሪካዊ ሥነ ሕንጻ፣ በወርቃማ ቤተ አምልኮና በሌሎችም መስህቦች ትታወቃለች።
በዋነኛነት ስሟ የሚጠራው ግን በሲክ ሃይማኖት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ቤተ መቅደስ መገኛ መሆኗ ነው።
ከእነዚህ ሁሉ በላይ የአምሪሳር መገለጫ የሚባለው የነዋሪዎቿ ደግነት ነው።
ደግነታቸው ከከተማዋ ምሥረታ ጀምሮ ይታወቃል።
በ16ኛው ክፍለ ዘመን በሲክ የሃይማኖት መሪ ነው የተቆረቆረችው።
ከተማዋ የምትገኘው የሲኪዝም መነሻ በሆነው የሕንድ ፑንጃብ ግዛት ነው።
ግዛቱ ሴቫ በተባለ ባህል ይታወቃል።
በሴቫ ባህል ሰዎች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ወይም ድርጊታቸው እንደ ውለታ እንዲቆጠር ሳይፈልጉ በጎ ሥራ ማከናወን ይጠበቅባቸዋል።
በመላው ዓለም ያሉ የሲክ ተከታዮች በቤተ መቅደስ ሴቫ ማከናወን አለባቸው።
ሴቫ በቀላል ድርጊቶች ሊገለጽ ይችላል። ማጽዳት፣ ምግብ ማቅረብ፣ ቤተ መቅደስ ውስጥ ማስተናበር ይጠቀሳሉ።
ሌሎች ሴቫ የሚከውኑት በግል ሕይወታቸው በጎ አድራጎት በመፈጸም ይሆናል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሲነሳ የሲክ ማኅበረሰብ ፈተናውን ለመቋቋም በአንድነት ቆሟል።
ኦክስጅን እና ሌሎችም የሕክምና መሣሪያዎች ለሚያስፈልጋቸው ሲያከፋፍሉ ነበር።
ስለ ሴቫ መጽሐፍ የጻፈችው ጃስረን ማይል “ሴቫ በሲኪዝም ውስጥ ለራስ ሳይሳሱ ደግ መሆን ማለት ነው። እለት በእለት ነው የሚተገበረው። ደግነት የሲኮች መገለጫ የሆነው ከቀድሞውም ነው” ትላለች።
ሴቫን ከቤተሰቡ ጋር ሆኖ ከስምንት ዓመቱ ጀምሮ የተገበረው የ23 ዓመቱ አብሂንዳን ቻዳሪ “የሴቫ ሌላኛው ስም ፍቅር ነው” ይላል።
አንድ ሰው ምሥጢራዊ እንዲሆንና ከራሱ አልፎ ለሌሎች እንዲያስብ ይጠበቃል።
“በቀኝ እጅህ ሴቫ ስታደርግ ግራ እጅህ እንኳን እንዳያየው” ሲል ይገልጸዋል።
በዚህ ግላዊና ካፒታሊስት ዓለም እንዲህ ያለ እሳቤ መስማት ተስፋ ይፈነጥቃል።
በመላው ዓለም ያሉ ሲኮች ደግነት መርሀቸው ነው።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን ሲያስጨንቅ በዩናይትድ ኪንግደም ያሉ የሲክ በጎ ፈቃደኞች በሺዎች የሚቆጠሩ ምግቦችን ለጤና ባለሙያዎች አድርሰዋል።
በተለያዩ የአሜሪካ ከተሞች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ምግቦች አብስለው በነጻ ሰጥተዋል።
ካናዳ ማዕበል ሲነሳ በኒው ዚላንድ አውሎ ነፋስ ሲከሰትም በጎ አድራጎት ፈጽመዋል።
የሲክ ማእከል በሆነችው አምሪሳር ከተማ ሴቫ ከእነዚህም ከፍ ባለ ደረጃ ነው የሚተገበረው።
በአምሪሳሪ አንድም ሰው ተርቦ እንደማያድር በመላው ሕንድ ይታወቃል።
ሁሌም ቢሆን ትኩስ ምግብ ተዘጋጅቶ ጎልደን በሚባለው ቤተ አምልኮ ይቀመጣል።
ይህ በሃይማኖቱ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ስፍራ ነው።
ወደ ቤተ መቅደሱ ሲገቡ በነጻ የሚገባበት ማኅበረሰባዊ ጓዳ ያገኛሉ። በዓለም ትልቁ ጓዳ ነው። በየቀኑ 100,000 ሰዎች ያስተናግዳል። የሚዘጋበት ቀን የለም።
ያለ መድልዎ ሁሉም ሰው ሄዶ መመገብ ይችላል።

መጠለያ እና ምግብ የሚፈልጉ ሰዎችን ጓዳው ያስተናግዳል።
24 ሰዓት ምግብ አለ።
ኒው ዮርክ የሚገኘው ሼፍ ቪካስ ካና በወረርሽኙ ወቅት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ምግቦች አድሏል።
“ተወልጄ ያደግኩት አምሪሳር ነው። ሁሉም ሰው የሚመገብበት የማኅበረሰብ ጓዳ አለን። መላ ከተማው እዛ ሊመገብ ይችላል” ይላል።
ወደ ኒው ዮርክ ከሄደ በኋላ ግን “ረሃብ እንደገጠመው” ይናገራል። አነስተኛ ሥራ እየሠራ ራሱን ለማስተዳደር ሲታገል ነበር የተራበው።
ጎልደን ቤተ መቅደስ በሥነ ምግባር ነው የሚመራው።
በጎ ፈቃደኞች ጣፋጭ ምስር፣ ቻፓቲ፣ የሽንብራ ሾርባ እና እርጎ በንጹህ ሰሃን በየቀኑ ያቀርባሉ።
ክፍሉ በአንዴ 200 ሰው ያስተናግዳል። ሴት ወንድ፣ ወጣት አዛውንት፣ ሃብታም ድሃ ይገኝበታል።
ተጨማሪ ምግብ የሚጠይቁ፣ በፍጥነት ተመግበው የሚወጡም አሉ።
በየ15 ደቂቃው በጎ ፈቃደኞች ክፍሉን አጽድተው ሌላ ዙር እንግዶች ይቀበላሉ። በዚህ መንገድ 24 ሰዓት ይቀጥላሉ።
በከተማዋ በቤተ መቅደስ ያሉም ይሁን ጎዳና ላይ ያሉት ቀናነትና በጎ ነት ይስተዋልባቸዋል።
ጎብኚዎችን በፈገግታ ይቀበላሉ። ለመተባበር ፈጣን ናቸው። እንግዳ ይቀበላሉ።
በትልቅ ሬስቶራንት እንግዳ ሲመጣ ወንበር ለቀው ያስተናግዳሉ።
ሻይ እንጠጣ፣ ስለ ሕይወት እንጨዋወት ብሎ መጋበዝ ልማዳቸው ነው።
በከተማዋ ተወልዳ ያደገችው ራሀት ሻርማ “በዛ ከተማ ማደግ በአንድ ትልቅ ማኅበረሰብ የማደግ ስሜት አለው” ትላለች።
በጎልደን ቤተ መቅደስ አኩኩሉ እየተጫወተች ነው ያደገችው።
“ሁላችንም ሴቫ እናደርጋለን። አንዳችን ለሌላችን እንቆረቆራለን። ሲኮችና ሂንዱዎች በፖለቲካ አመለካከት ብንለያይም በፍቅር ነው የምንኖረው።

ከተማዋ ሕይወት የተሞላች ናት። መለኮታዊ ግርማ ተላብሳለች።
መንገድ ዳርቻ የሚሸጠው ባህላዊ ምግብ ሩዝና የሽንብራ ሾርባ ያለው ሲሆን ወተት በቂቤም ይቀርባል።
ከተማዋ ጥንታዊ ናት። ጠባብ መንገዶች አሏት። አነስተኛ አደባባዮች ይበዛሉ። የመንገድ ትርዒቶች ማየት የተለመደ ነው።
ከተማዋ የከፋ የኋላ ታሪክም አላት። ከተማዋን የቀረጸው እንዲሁም የሲክ ሃይማኖት መሠረት ተደርጎ የሚወሰደውም ይህ ታሪክ ነው።
በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ዘመን ከተማዋ የተቃውሞ መነሻና የተቃዋሚዎች መሰብሰቢያም ነበረች።
በፑንጃብ ግዛት ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ ናት።
እአአ በ1919 ጠባሳ ትቶ ያለፈ ክፉ ድርጊት ተከናውኗል።
አንድ የእንግሊዝ ጀነራል በሰላም የተሰበሰቡ ሰዎች ላይ ተኩስ እንዲከፈት ካዘዘ በኋላ ወደ 1,500 ሰዎች ተገድለዋል።
የጃሊናዋላ ባግ ጭፍጨፋ በሚል ይታወቃል።
እንግሊዞች በ1947 ከሕንድ ሲወጡ የተፈጠረው ቀውስ ክፉኛ ከጎዳቸው ከተሞች አንዷ አምሪሳር ናት።
ይህ ወቅት የፖለቲካ ድንበሮች እንደ አዲስ የተዋቀሩበት፣ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሥር የነበረ ሃብት ክፍፍል የተካሄደበትም ወቅት ነበር።
እአአ በ2017 ለዚህ መታሰቢያ የሚሆን ሙዝየም አምሪሳር ውስጥ ተከፍቷል። በሕንድ ለዚህ ታሪክ መታሰቢያ የሚገኘው በዚች ከተማ ብቻ ነው።

በ1984 ከተማዋ ሌላም ክፉ ጠባሳ ገጠማት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኢንድራ ጋንዲ ወታደራዊ ኦፕሬሽን እንዲካሄድ አዘዙ።
ጎልደን ቤተ መቅደስ ውስጥ ወታደሮች ገብተው ተገንጣዮች ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ተደርጓል።
ይህም የፈጠረው ሕመም እስካሁንም ድረስ ይስተዋላል።
ክስተቱን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሯና ሁለት ሲክ ጠባቂዎቻቸው ከወራት በኋላ ተገድለዋል።
በቀጣዩቹ ቀናት በመላው ሕንድ በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ሲኮች ተጨፍጭፈዋል።
የሲክ ሰማዕታትን ማስታወስ ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል። በፀሎት ውስጥም ስማቸው ይነሳል።
ስለ ሴቫ መጽሐፍ የጻፈችው ጃስረን ማይል “እነዚህ ክፉ ታሪኮች የሚነገሩት ጥላቻና በቀል ለማነሳሳት አይደለም። ታሪካችን የጽናታችን ማሳያ ነው” ትላለች።
በጋራ ብዙ ሐዘን የደረሰበት ማኅበረሰብ ተቀባይ መሆኑ አስገራሚ እንደሆነም ትናገራለች።
“ሲኪዝምን የፈጠሩት የሃይማኖት መሪ ሴቫ የሲክ መዝሙር ውስጥ እንዲገባ አድርገዋል። ሲኮች ከራስ በላይ ለሰው ማሰብን ባህላቸው እንዲያደርጉም አስችለዋል” ስትል ታስረዳለች።
ይህ ባህል ሰዎችን በሃይማኖትና ዘር ሳይለዩ መቀበልን ይጠይቃል። ደግነትንም ያበረታታተል።
በአምሪሳር ምንም ያህል ነገሮች የከፉ ቢሆኑ ደግነት፣ ፍቅር እና በጎነት ያሸንፋሉ።












