የሰጠመችው የግሪክ መርከብ 100 ሕፃናት ይዛ እንደነበር ተሰማ

የፎቶው ባለመብት, HELLENIC COAST GUARD
በደቡባዊ ግሪክ የሰጠመችው መርከብ ቢያንስ 100 ሕፃናትን ይዛ እንደነበር ከአደጋው የተረፉ ተናገሩ።
እስካሁን ቢያንስ 78 ሰዎች በአደጋው ምክንያት መሞታቸው ሲረጋገጥ በርካቶች እስካሁን ያሉበት አይታወቅም።
እየወጡ ያሉ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት መርከቧ በትንሹ 740 ሰዎችን አሳፍራ ነበር።
በርካታ ግብፃዊያንን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ምክንያት በቁጥጥር ሥር ውለዋል ሲል የግሪክ ቴሌቪዥን ዘግቧል።
የሃገሪቱ የድንበር ኃይል አደጋው ከመድረሱ በፊት ከውሳኔ ባለመድረሱ ቢወቀስም ባለሥልጣናት ግን ኃይሉ እርዳታ ለማቅረብ ጠይቆ ምላሽ እንዳጣ ገልጿል።
ምንም እንኳ ከአደጋው በሕይወት የተረፉ ሰዎች የመኖራቸው ተስፋ እየመነመነ ቢመጣም መርከቧ የሰጠችበት አካባቢው የሕይወት አድን ሥራው ቀጥሏል።
የካላማታ አጠቃላይ ሆስፒታል ነባር ዶክተር የሆኑ ግለሰብ 100 ያክል ሕፃናት መርከቧ ላይ እንደነበሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ከአደጋው የተረፉ ሰዎች እንደነገሩን በመርከቧ የታችኛው ሥፍራው ሕፃናት ነበሩ። ሴቶችና ሕፃናት” ይላሉ ዶክተር ማኖሊስ ማካሪስ።
የልብ ሐኪሙ እንደሚሉት ሁለት ከአደጋው የተረፉ ሰዎች የሕፃናቱ ቁጥር ግምት አስቀምጠዋል።
“አንዱ 100 ብሎኛል። ሌላኛው ደግሞ 50። የትኛው ትክክል እንደሆነ አላውቅም። ነገር ግን ቁጥሩ ቀላል አይደለም።"
ዶክተር ማካሪስ 600 ያክል ሰዎች በአደጋው ምክንያት ሳይሞቱ እንዳልቀሩ ይገምታሉ።
“መርከቧ ላይ የነበሩ ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር 750 ነበር። ሁሉም ሰው የነገረኝ ይህን ቁጥር ነው።”
የአንዳንድ ግብፃዊ ሕፃናት ቤተሰቦች ምናልባት እርዳታ ሲሰጡ አይተዋቸው ከሆነ በሚል ፎቶዎች እንደሚልኩላቸው ዶክተሩ ይናገራሉ።
“በጣም አሳዛኝ ነው። ሁሉም አውሮፓ ውስጥ ያለ ይህን መቀበል የለበትም። የሆነ ነገር ማድረግ አለብን። ድጋሚ እንዳይከሰት ሁሉም ሊረባረብ ይገባል።”
ኤኤንቲ1 የተሰኘው የግሪክ ጣቢያ ከአደጋው የተረፉ ሰዎችን “100 ሕፃናት ነበሩ ወይ?” ሲል ጠይቆ “አዎ” የሚል ምላሽ ተሰጥቶታል።
ቢቢሲ በግሉ ይህን ቁጥር ማረጋገጥ ባይችልም ሴቭ ዘ ቺልድረን ከአደጋው የተረፉ ሰዎችን አነጋግሮ ቁጥሩ ትክክል መሆኑን አረጋግጧል።
ቤተሰቦቻቸው የጠፉባቸው ሰዎች ዘመድ አዝማድ ፍለጋ ወደ ካላማታ መጉረፍ ጀምረዋል።
“ዘመዶቼ መርከቧ ላይ ነበሩ” ይላል አፍታብ። ከዩኬ የመጣው አፍታብ ቢያንስ 4 ዘመዶቹ ከፓኪስታን ተሰደው መርከቧ ላይ እንደነበሩ ይናገራል።
“አንዱ ዘመዳችን በሕይወት መትረፉን አረጋግጠናል። ነገር ግን ሌሎቹ የት እንዳሉ አናውቅም።”
አንድ ሶሪያዊ ግለሰብ ሚስቱና የሚስቱ ወንድም ከጠፉት መካከል መሆናቸውን ሲያውቅም በሐዘን ሲሰበር ቢቢሲ ተመልክቷል።
አክቲቪስት ናዋል ሱፊ ማክሰኞ ጠዋት ከመርከቧ ላይ በደረሳት የስልክ ጥሪ መሠረት ስለጉዳዩ ድምጿን ያሰማች የመጀመሪያዋ ሰው ነበረች።
የግሪክ ድንበር ጠባቂዎች ማክሰኞ በሥፍራው አቆጣጠር ከሰዓት ስምንት ሰዓት ከዓሳ አጥማጇ መርከብ ግንኙነት ቢመሠርቱም የእርዳታ ጥሪ ግን እንዳልቀረበላቸው ይናገራሉ።
ሱፊ በፌስቡክ ገጿ አንድ መርከብ ወደ ስደተኞቹ ተጠግቶ ገመድ ካሰረ በኋላ ውሃ ማደል ሲጀምር ነው ሁኔታዎች የተመሰቃቀሉት።
መርከቡ ገመድ ሲያስር በሰጠመችው መርከብ ላይ የነበሩ ሰዎች “አንዳች አደጋ” እንደመጣ በማሰብ ግርግር መጀመራቸው ለመርከቧ መስጠም ምክንያት ሳይሆን አይቀርም።
ግሪክ በአደጋው ምክንያት የሶስት ቀናት ሃዘን አውጃለች። ሰኔ 25 ሊደረግ የታሰበው የሕዝብ እንደራሴዎች ምርጫ ቅስቀሳም ተገትቷል።
በተለያዩ የሃገሪቱ ከተሞች የተቃውሞ ድምፆች መሰማት ጀምረዋል።
ግሪክ፤ ከመካከለኛው ምስራቅ፣ እስያና አፍሪካ ወደ አውሮፓ መድረስ ለሚሹ ስደተኞች ዋነኛ መግቢያ ናት።












