በናይጄሪያ ጀልባ ላይ በተከሰተ አደጋ 100 ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች የደረሱበት አልታወቀም

አደጋው የተከሰተበት የኒጀር ወንዝ
የምስሉ መግለጫ, አደጋው የተከሰተበት የኒጀር ወንዝ

ባለፈው ሰኞ በደቡብ ምዕራባዊ ናይጄሪያ ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዘ የነበረ ጀልባ ሰጥሞ ከ100 በላይ ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች የገቡበት አለመታወቁን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ጀልባው በአንድ ሰርግ ላይ የታደሙ ወደ 300 የሚጠጉ መንገደኞችን ካዋራ ከተባለችው የናይጄሪያ ግዛት ወደ ሌላኛው ኒጀር ግዛት በማጓጓዝ ላይ ሳለ ነበር የሰጠመው።

ሰዎችን የማፈላለጉና ነፍስ የማድን ተግባሩም ቀጥሏል።

ጀልባው ባጋጠመው ችግር ምክንያት በውሃ የተጥለቀለቀ ሲሆን ላጋጠመው ችግር መነሻው ያ እንደሆነ ፖሊስ ገልጿል።

የሟቾችን ቁጥር በተመለከተ በተመለከተ የተለያዩ ቁጥሮች እየወጡ ይገኛሉ።

የካዋራ ግዛት ፖሊስ 106 ሰዎች እንደሞቱና 144 ሰዎችን ደግሞ መታደግ እንደተቻለ ገልጿል።

ጨምሮም ከሟቾች ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት ኢቡ ከተባለ መንደር እንደመጡና ሌሎች 38 ሟቾች ደግሞ መነሻቸው በአቅራቢያው ካለ ደዝካን ከተባለ መንድር ነው ብሏል።

ቀደም ብሎ አደጋው ያጋጠመት አከባቢ ባህላዊ መሪ ኡመር ቦሎጊ ከ150 በላይ ሰዎች ሞተዋል ተብሎ እንደተሰጋ ተናግሯል።

በርካታ ሴቶች ከአደጋው ልጆቻቸውን ለማትረፍ ሲሞክሩ መሞታቸውን ከአደጋው ከዳኑት መካከል አንዱ ሞሃመድ አልሃሰን ለቢቢሲ ገልጿል።

የሞሃመድ እህት ከአደጋው ብትተርፍም የ7 ዓመት ልጇን ግን በአደጋው አጥታለች።

ሌላኛዋ ከአደጋው የተረፈችው አይሻ ሞሃመድ በቅርቡ ሊሞሸሩ የነበሩ ሦስት ልጇቿን በጀልባው አደጋ እንዳጣች ተናግራለች።

በአደጋው የቅርብ ዘመዱን ያጣው ሞሃመድ ሳሊሁ “ክስተቱ እጅግ አሳዛኝና ማኅበረሰቡን እጅግ ያስደነገጠ ነው” ሲል ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ገልጿል።

የአደጋው መነሻ አሁንም እየተጣራ ይገኛል።

የአካቢው ፖሊስ የጀልባው ክፍል ጉዳት በመድረሱ ጎርፍ በመፍጠር ጀልባው እንዲጥለቀለቅና እንዲገለበጥ ምክንያት ሆኗል ብሏል።

ሆኖም የአካቢው ባህላዊ መሪ ማዕበል ጀልባውን መትቶ ወንዝ ውስጥ ከወደቀ ዛፍ ጋር እንዲጋጭ ምክንያት በመሆኑ ጀልባዋ ተገልብጣለች ብለዋል።

የካዋራ ግዛት አስተዳዳሪ የተሰማቸውን ሀዘን ለተጎጂ ቤተሰቦች ገልጸው የጠፉትን ሰዎች የማፈላለጉ ስራ ይቀጥላል ብለዋል።

አስተዳዳሪው ጉዳት የደረሰባቸውን አከባቢዎች ትላንት ረዕቡ የጎበኙ ሲሆን 100 ሺህ የመንሳፈፊያ ሰደሪያ እንደሚሰጡና የአደጋ ጊዜ ትምህርት እንደሚጀመር ቃል ገብተዋል።

የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ቦላ አህመድ “በካዋራ የዜጎቻችንን ሕይወት በቀጠፈው በዚህ እጅግ አሳዛኝ ክስተት በጥልቅ አዝኛለሁ” ብለዋል።

“ተጎጂዎቹ የሰርግ እድምተኞች ሆነው እንዳለመታደል ይህ አይነት አደጋ ላይ መውደቃቸው ክስተቱን እጅግ አዛሳኝ ያደርገዋል” ሲሉም አክለዋል።

በናይጄሪያ ወንዞች ላይ ጀልባ አደጋ ሲያጋጥማቸው መስማት የተለመደ ነው።