ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ቢትኮይንን ለምን ይፋዊ መገበያያ አደረገች?

ቢትኮይን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ቢትኮይንን ይፋዊ መገበያያዋ ማድረጓ ብዙዎችን አስገርሟል።

የአገሪቱ መንግሥት ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው የወደፊቱን ምጣኔ ሀብት በተሻለ ሁኔታ ለማሳለጥ አስቦ እንደሆነ ገልጿል።

ፕሬዝዳንት ፋውስቲን አርቼንጅ ቶዋድራ ልክ እንደ ኤለን መስክ የክሪፕቶከረንሲን መንገድ እየተከተሉ ይመስላል።

“በቁጥር ውስጥ ኃይል አለ” ሲሉ የጻፉት ትዊት ከቢትኮይን ጋር ይተሳሰራል። የአገሪቱ መሪ ቃልም ሆኗል።

ከኤል ሳልቫዶር ቀጥሎ ቢትኮይንን ይፋዊ መገበያያዋ ያደረገችው አገር ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ናት።

በማዕድን ሀብት ብትታወቅም ከዓለም ድሃ አገራት መካከል አንዷ ነች።

አገሪቱ በእርስ በእርስ ጦርነት ለአሠርታት ተንጣለች።

አማጽያንን ለመግታት ሲል መንግሥት የሩሲያ ቅጥረኛ ታጣቂዎች ቡድን ዋግነር ግሩፕን መቅጠሩ ከተሰማ ሰነባብቷል።

አገሪቱ ቢትኮይንን ሕጋዊ መገበያያ ያደረችው ከፈረንሳይ ጋር ያላት ግንኙነትን ትታ ከሩሲያ ጋር አጋርነት መመሥረቷን ለማሳየት ይሆን? ብለው የጠየቁ አልጠፉም።

በመዲናዋ ባንጉይ ያሉ መደብሮች ቢትኮይን መገበያያ መሆኑን ተከትሎ ገበያ አልደራላቸውም።

እአአ በ2020 የወጣ አሐዝ እንደሚጠቁመው፣ ከአሥር የማዕከላዊ አፍሪካ ነዋሪዎች ዘጠኙ ኢንተርኔት አያገኙም።

ኢንተርኔት ከሌለ ደግሞ ቢትኮይንን ማንቀሳቀስ አይቻልም።

ይባስ ብሎ በአገሪቱ ውስጥ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አቅርቦት የለም።

ሁኔታዎች ምቹ ሳይሆኑ ለምን ቢትኮይንን መገበያያ አደረገች ታዲያ?

“ለአገሪቱ አዲስ ጅማሮ ይሆናል” ከማለት ውጪ ዝርዝር ነገር አልተነገረም።

አዲስ ጅማሮ?

ፕሬዝዳንት ፋውስቲን አርቼንጅ ቶዋድራ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ፕሬዝዳንቱ ‘ሳንጎ’ የተባለ ፕሮጀክት ዘርግተዋል።

ፕሮጀክቱ “ማንኛውም በክሪፕቶ ኢንቨስትመንት መሠማራት ለሚፈልግ ሰው ድንቅ አማራጭ” በማለት ነው የተገለጸው።

ስለፕሮጀክቱ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ወደ ድረ ገጹ ሲገቡ፣ የኢንቨስተሮች ማውጫ ያገኛሉ።

ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክን የመጀመሪያዋ የክሪፕቶ መገበያያ ማዕከል የማድረግ ዕቅድ እንዳለ ድረ ገጹ ለኢንቨስተሮች ያስረዳል።

የክሪፕቶ ተመራማሪ ስቶን አትዊን እንደሚሉት፣ ድረ ገጹ የሚፈለገውን መረጃ በዝርዝር አይሰጥም።

በቢትኮይን አማካይነት በማዕድን እና በሌሎችም ዘርፎች መሠማራት እንደሚቻል ተገልጿል።

በቢትኮይን ለሚደረግ ኢንቨስትመንት ታክስ እንደማይጠየቅም ይጠቁማል።

ክሪፕቶ ያለ ኢንተርኔትና መብራት?

የወርቅና አልማዝ አገር የሆነችው ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ አሁን ደግሞ ኢንቨስተሮችን በቢትኮይን ለመሳብ እየሞከረች ይመስላል።

ፕሬዝዳንቱ “በቢሮክራሲ ታስረን ቆይተናል። አሁን የምጣኔ ሀብት ፍልስፍናችንን የምንከልስበት ጊዜ ነው” ይላሉ።

ነገር ግን ቢትኮይንን ያለ ኢንተርኔትና መብራት ዝርጋታ መተግበር አይቻልም።

ካሳቫ በመሸጥ የምትተዳደረው ኤዲት ያምቦጋዚ “ቢትኮይን ምን እንደሆነ አይገባኝም” ትላለች።

“ተንቀሳቃሽ ስልክ ቢኖረኝም ኢንተርኔት አላገኝም። ኢንተርኔት ላይ ብዙ አጭበርባሪዎች ስላሉ ክሪፕቶከረንሲ መጠቀም አልፈልግም።”

ክሪፕቶ ላይ ጥያቄ ያላቸው የኤል ሳልቫዶር ዜጎችም ናቸው። ፕሬዝዳንት ናይብ ቡክሌ፣ ክሪፕቶከረንሲን በስፋት ሲያስተዋውቁ ታይተዋል።

‘ሺቮ ዋሌት’ የተባለ ፕሮጀክትም ዘርግተዋል። ፕሮጀክቱ ቢትኮይንን ለማሳለጥ የሚረዳ መተግበሪያን የያዘ ነው። ሲጀመር ብዙዎች መተግበሪያውን ቢጭኑም እያደር ተቀዛቅዟል።

አንዳንድ የአገሪቱ ነዋሪዎች “ቢትኮይንን አናምነተው” ብለዋል። ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ክሪፕቶከረንሲን እንድትጠም የሚደግፉ በበኩላቸው፣ ሂደቱ ጊዜ ስለሚወስድ ትዕግስት ያሻል ይላሉ።

የፓርላማ አባሉ ጃን ጋልቫኒስ ንግሲምቦ፣ አገሪቱ ገና የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ዝርጋታዋን ባታጠናቅቅም በሂደት እንደምታሳካው ይናገራሉ።

በ2020 መጨረሻ የፋይበር ኔትወርክ ዝርጋታ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የፓርላማ አባሉ እንደሚሉት የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ዝርጋታው ከመገበያያ ትግበራው ጎን ለጎን ይሄዳል።

“እኔ የክሪፕቶ ተጠቃሚ ነኝ። ዛሬ ራሱ ገንዘብ አግኝቻለሁ” ይላሉ።

የባንክ ተጠቃሚዎች ቁጥር አነስተኛ በሆነበት አገር ክሪፕቶ የተሻለው አማራጭ እንደሆነ ይከራከራሉ።

አሠራሩ ገንዘብ በተሻለና ደኅንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ እንደሚያስቀምጥ ይናገራሉ።

ማዕከላዊ አፍሪካ የምትገበያይበት ፍራንክ በፈረንሳይ የሚደገፍ ሲሆን፣ በቀጠናው አምስት አገራት ይጠቀሙበታል።

በካሜሩን የሚገኘው የማዕከላዊ አፍሪካ አገራት ባንክ፣ በክሪፕቶ ለመገበያየት የተላለፈው ውሳኔ ብዙም አላስደሰተውም።

የባንኩ ገዢ አባስ ማህማት ቶሊ፣ ክሪፕቶን መገበያያ ማድረግ በማዕከላዊ አፍሪካ የሚገኙ አገራት የሚገለገሉበትን ፍራንክ የሚገዳደር መገበያያ ሥርዓት መዘርታ ይሆናል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ይህም ቀጠናውን የሚያውክ ነው ብለዋል።

አይኤምኤፍም ውሳኔውን ነቅፏል።

ምናልባትም ውሳኔው ከምጣኔ ሀብታዊ ምክንያቱ ጎን ለጎን ፖለቲካዊ አንድምታ ሊኖረው ይችላል ብለው የሚያምኑ ብዙ ናቸው።

በፍራንክ አማካይነት በፈረንሳይ እጅ አዙር የምጣኔ ሀብት ጫና ለመላቀቅ የተወሰነ ነው የሚሉም አልታጡም።

የምጣኔ ሀብት ተንታኙ ናታን ሄይስ እንደሚሉት፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ፍራንክን መገበያያዋ አድርጋ ለተወሰነ ጊዜ መቆየቷ አይቀርም።

ክሪፕቶን መገበያያ ማድረጓ አገሪቱ ከሩሲያ ጋር የቅርብ ወዳጅነት የመመሥረቷ አንድ መገለጫ ተደርጎም ይወሰዳል።

የሩሲያ ቅጥረኛ ተዋጊዎች በማዕድን ኮንትራት እንደተከፈላቸው መረጃዎች ወጥተዋል።

ክሪፕቶከረንሲ የዚህ ቅጥያ ሊሆን ይችላል ቢባልም፣ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ውሳኔው ከሩሲያ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም ብለዋል።

አገሪቱ ወደ ዲጂታል ዓለም የምታደርገው ሽግግር የሕዝቡን ፍላጎት ያማከለ እንደሆነ በመግለጽም ፕሬዝዳንቱ ይከራከራሉ።