ክሪፕቶከረንሲ፡ ኢራን ከመብራት መጥፋት ጋር በተያያዘ ቢትኮይንን ለአራት ወራት አገደች

ቢትኮይን

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ከቢትኮይን ማይኒንግ ውስጥ 4.5 በመቶ የሚሆነው በኢራን እንደሚካሄድ ይገመታል

በከተሞቿ ተደጋጋሚ የመብራት መጥፋት ያጋጠማት ኢራን እንደ ቢትኮይን ያሉ እና ከፍተኛ ኃይል የሚፈልጉ የክሪፕቶከረንሲ ሥርዓቶች ላይ ለአራት ወራት እገዳ መጣሏን አስታውቃለች፡፡

ክሪፕቶከረንሲን ዲጂታል ገንዘብ ወይም መገበያያ ብለን በግርድፉ ልንተረጉመው እንችላለን። ቢትኮይን ከእነዚህ ገንዘቦች መካከል አንዱ ሲሆን አዲስ ቢትኮይን ወደ ገበያ የሚገባበት ሥርዓት ደግሞ ማይኒንግ ይባላል።

ፕሬዝዳንት ሀሰን ሩሃኒ በካቢኔያቸው ስብሰባ እንደተናገሩት የመብራቱ መጥፋት ዋነኛ መንስኤ በድርቅ ምክንያት በሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ላይ ተጽዕኖ በመፈጠሩ ነው፡፡

የክሪፕቶከረንሲ ማይኒንግ (85 በመቶው ያልፈቃድ የሚሠራ ነው) በየቀኑ ከ2 ጌጋዋት በላይ ኃይል እየተጠቀመ መሆኑንም ፕሬዚደንቱ ተናግረዋል፡፡

ከቢትኮይን ማይኒንግ ውስጥ 4.5 በመቶ የሚሆነው በኢራን እንደሚካሄድ ይገመታል።

ኢሊፕቲክ እንደተባለው የትንታኔ ኩባንያ ከሆነ ውሳኔው አገሪቱ ማዕቀቦችን እንድታልፍ እና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመግዛት የሚያስችል በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር የክሪፕቶ-ሃብት እንድታገኝ ያስችላታል፡፡

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኑክሌር ስምምነት በመተዉ እአአ በ2018 በጣሉት ማዕቀቦች ምክንያት የኢራን ባንኮች ከዓለም የገንዘብ ሥርዓት ውጭ ሲሆኑ የነዳጅ ሽያጯም እየቀነሰ በመሄዱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እና ገቢ እንዳታገኝ አድርጓታል፡፡

ቢትኮይን እጅግ ከፍተኛ የኮምፒተር ኃይል ስለሚጠይቅ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ይጠቀማል።

ኢሊፕቲክ እንደሚለው የኢራን ባለሥልጣናት እ.ኤ.አ. በ2019 ነበር የክሪፕቶከረንሲ ማይኒንግን በይፋ እውቅና የሰጡት። በኋላም በሥራው የሚሳትፉ እንዲለዩ፣ ለኤሌክትሪክ ከፍተኛ ታሪፍ እንዲከፍሉ እና ቢትኮይናቸውን ለኢራን ማዕከላዊ ባንክ እንዲሸጡ የሚያስገድድ የፈቃድ ሥርዓት ይፋ አደረጉ፡፡

ብሔራዊው የኤሌክትሪክ ኩባንያ ቅዳሜ ዕለት እንደገለጸው ፈቃድ የተሰጣቸው የክሪፕቶከረንሲ ማይንኒግ ተቋማት የኃይል መቆራረጥ ችግሩን ለማቃለል ሥራቸውን ቀድሞውኑ በፈቃደኝነት አቁመዋል፡፡

ሩሃኒ ረቡዕ ዕለት እንደተናገሩት ፈቃድ ያልተሰጣቸው ተቋማት ከስድስት እስከ ሰባት እጥፍ የሚበልጥ ኃይል እየተጠቀሙ በመሆኑ እስከ መስከረም 22 ቀን ድረስ ሁሉንም የክሪፕቶከረንሲ እንቅስቃሴዎች ለማገድ ተገደዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ አያይዘውም የኢነርጂ ሚንስትሩ ባለፈው ሳምንት በቴህራን እና በሌሎች በርካታ ከተሞች ባልታሰበ ሁኔታ መብራት በመጥፋቱ ኢራናውያንን ይቅርታ መጠየቃቸው ትክክል መሆኑን ተናግረዋል፡፡