ክሪፕቶከረንሲ፡ የሰሜን ኮሪያ የመረጃ ሰርሳሪዎች 400 ሚሊየን ዶላር ክሪፕቶከረንሲ መስረቃቸው ተነገረ

የኮምፒዩተር ኪቦርድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሰሜን ኮሪያ የመረጃ ሰርሳሪዎች ባለፈው የአውሮፓውያኑ 2021 በክሪፕቶከረንሲ ገጾች ላይ ቢያንስ ሰባት ጥቃቶችን በመፈፀም 400 ሚሊየን ዶላር የሚጠጋ ዋጋ ያለው ዲጂታል ሀብት መዝረፋቸውን አንድ ሪፖርት አመለከተ።

የክሪፕቶከረንሲን ዝውውር መረጃ የሚሰጠው ብሎክቼይን ኩባንያ- ቼይንአናሊስስ፣ ያለፈው ዓመት ዝግ በሆነችው ምሥራቅ እስያዊቷ አገር ሰሜን ኮሪያ ውስጥ ለሚገኙ የሳይበር ወንጀለኞች ስኬታማ ከሆኑ ዓመታት አንዱ ነበር ብሏል።

ድርጅቱ በሪፖርቱ እንዳለው ጥቃቶቹ በዋናነት ኢላማ ያደረጉት የኢንቨስትመንት ድርጅቶች እና የተማከለ የንግድ ልውውጦች ላይ ነው።

ይሁን እንጂ ሰሜን ኮሪያ የተጠረጠሩ የሳይበር ጥቃቶች ላይ አለመሳተፏን ደጋግማ አስተባብላለች።

ቼይንአናሊስስ በሪፖርቱ "ከ2020 እስከ 2021 ከሰሜን ኮሪያ ጋር የተያያዙ የመረጃ ጠለፋዎች ከአራት ወደ ሰባት ተመንጥቋል፤ ከእነዚህ ጠለፋዎች የሚወጣው ሀብትም 40 በመቶ ጨምሯል" ብሏል።

ጠላፊዎቹ፣ ተጠቃሚዎች እነሱ ወደሚፈልጉት መንገድ እንዲያመሩ በማታለል [ፊሽንግ ለርስ]፣ ኮዶችን በመስረቅ እና ከተጠቁ ኮምፒዩተሮች ከርቀት የተጠቃሚዎችን ገንዘብ መቆጣጠር የሚያስችለውን ማልዌርን ጨምሮ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ከድርጅቶቹ የዲጂታል ገንዘብ ማስቀመጫ [ሆት ዋሌት] ገንዘብ መውሰዳቸውንና ከዚያም በሰሜን ኮሪያ ወደሚገኙ አድራሻዎች ማዛወራቸውን ሪፖርቱን አመልክቷል።

ወደ ዝውውር በቀላሉ ለመግባት የሚችል ገንዘብ በዲጂታል የሚቀመጥበት ክሪፕቶከረንሲ 'ሆት ዋሌት' ሁልጊዜም ከኢንተርኔት እና ከክሪፕቶከረንሲ ኔትዎርክ ጋር የተገናኘ በመሆኑ ለጥቃት የተጋለጠ ነው።

የክሪፕቶከረንሲ ዲጂታል ገንዘብ ማስቀመጫ [ሆት ዋሌት] ክሪፕቶከረንሲ ለመቀበልና ለመላክ የሚያገለግል ሲሆን ተጠቃሚዎችም ምን ያህል እንዳላቸው ያሳያል።

በርካታ ባለሙያዎች ከፍተኛ መጠን ያላቸውን ክሪፕቶከረንሲ በየቀኑ ወደማይፈልጉትና ከሰፊው ኢንተርኔት ጋር ወደማይገናኘው ዲጂታል የገንዘብ ማስቀመጫ [ኮልድ ዋሌት] እንዲወስዱ ተጠቃሚዎችን ይመክራሉ።

የባለፈው ዓመት አብዛኞቹ ጥቃቶች የተፈፀሙት አሜሪካ ማዕቀብ የጣለችበት 'ላዛረስ' በተባለው የመረጃ ጠላፊ ቡድን ሳይሆን እንደማይቀር ቼይንአናሊስስ አመልክቷል።

ቡድኑን የሚቆጣጠረው የሰሜን ኮሪያ የመጀመሪያ ደረጃ የደኅንነት ቢሮ፣ ምስጢራዊ ኦፕሬሽኖችን በሚቆጣጠረው ሪኮኔሰንስ ጀነራል ቢሮ እንደሆነ ይታመናል።

ላዛረስ ቡድን ቀደም ብሎ 'ዋናክራይ' በተባለ ሶፍትዌር ጥቃት በመፈፀም ዓለም አቀፍ ባንኮችን እና የደንበኛ የሒሳብ ቁጥር በመጥለፍ እንዲሁም እአአ በ2014 በሶኒፒክቸርስ ላይ የሳይበር ጥቃት በመፈፀም ተከስሷል።

የባለፈው ዓመትን የሳይበር ጥቃት አስመልከቶ የወጣው ሪፖርት እንዳመለከተው "ሰሜን ኮሪያ ገንዘቡን አንዴ በእጇ ካስገባች በኋላ ለመደበቅና እና ገንዘቡን ለማውጣት ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ሂደት ጀምራለች" ብሏል።

በሰሜን ኮሪያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ የሚከታተለው የተባበሩት መንግሥታት ቡድን በበኩሉ ፒዮንግያንግ ዓለም አቀፍ ማዕቀቦችን ለመቋቋም የኒዩክሌር እና የባለስቲክ ሚሳይል መርሃ ግብሯን ለመደገፍ የተሰረቀ ገንዘብ ተጠቅማለች ሲል ከሷል።

በሌላ በኩል ባለፈው ዓመት የካቲት ወር አሜሪካ ከ1.3 ቢሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ እና ክሪፕቶከረንሲ ለመስረቅ በፈፀሙት ከፍተኛ የመረጃ ጠለፋ ወንጀል ሦስት የሰሜን ኮሪያ የኮምፒዩተር ፕሮግራም ባለሙያዎች ላይ ክስ አቅርባለች።

የአገሪቷ የፍትሕ ሚኒስቴር የሳይበር ጥቃቱ ከባንክ እስከ የሆሊውድ ፊልም ስቱዲዮ ድረስ ያሉ ኩባንያዎችን ጎድቷል ብሏል።