ቻይና ክሪፕቶከረንሲን ሕገ ወጥ ስትል ፈረጀች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የቻይና ማዕከላዊ ባንክ ቢትኮይንን ጨምሮ ማንኛውም የክሪፕቶከረንሲ ግብይት ሕገ ወጥ እንዲሆን ወሰነ።
"ቨርቹዋል ገንዘብን በመጠቀም የሚደረግ ማንኛውም ግብይት ሕገ ወጥ የፋይናንስ እንቅስቃሴ ነው" ሲል የቻይና ሕዝቦች ባንክ ትናንት አርብ ገልጿል።
"ይህ የሕዝቦችን ንብረት ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው" ሲልም አስጠንቅቋል።
የቻይና የክሪፕቶከርንሲ (ዲጂታል መገበያያ ገንዘብ) ገበያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ግዙፍ ከሚባሉት መካከል ነው።
የክሪፕቶከረንሲ ገበያ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችም ሆኑ መንግሥታት በሚወስኗቸው ውሳኔዎች ምክንያት በተደጋጋሚ ከፍ እና ዝቅ እያለ ይገኛል።
ቻይና ትናንት ያሳለፈችውን ውሳኔ ተከትሎም አንድ ከረንሲ ላይ የ2000 ዶላር ቅናሽ ታይቷል።
ቻይና እአአ በ2019 ክሪፕቶከረንሲን መጠቀምን ብትከለክልም ግብይቱ በውጪ ምንዛሬ ሲካሄድ ቆይቷል። ነገር ግን በተያዘው ዓመት የቻይና መንግሥት ግብይቱን ለማስቆም ሰፋፊ እርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል።
በግንቦት ወርም የቻይና መንግሥታዊ ተቋማት በቢትኮይንም ሆነ በማንኛውም የክሪፕቶከረንሲ ለሚደረጉ ግብይቶች ሽፋን እንደማይሰጡ ገልጸው ነበር።
ይህም የመንግሥት ባለሥልጣናት በኢንዱስሪው ላይ እያደረሱት ያለው ጫና መጨመሩን ተከትሎ የመጣ ነበር።
በሰኔ ወር ላይም ባንኮችን ጨምሮ ማንኛውም የክፍያ ዘዴዎች የክሪፕቶከረንሲ ክፍያዎችን ማሳለጥ እንዲያቆሙ መንግሥት ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር። እንዲሁም ከረንሲውን የማምረት ተግባራትን ማገድም ሌላው እርምጃ ነበር።
ነገር ግን እነዚህ እርምጃዎች እንዳሉ ሆነው ትናንት አርብ የተሰጠው ውሳኔ ቻይና የክሪፕቶከረንሲን ግብይት በየትኛውም መልኩ ለማስቆም ማሰቧን ያመላከተ ነው።
እንደ መግለጫው ከሆነ ከዚህ በኋላ በግብይቱ የሚሳተፉ ሰዎች የወንጀል ተጠያቂነት ይከተላቸዋል። ይህ ብቻም ሳይሆን ይህንን አገልግሎት የሚያሳልጡ የውጪ የበይነ መረብ ገበያዎችም በሕገ ወጥ ድርጊቱ ተሳታፊ እንደሆኑ እንደሚታመንም መግለጫው አክሏል።












