"በኢትዮጵያ ሰኔ 30 የንባብ ቀን ሆኖ ይታወጃል" ደራሲያን ማኅበር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ሰኔ 30፣ በአገሪቱ የንባብ ቀን ሆኖ እንዲታወጅለት ሲያደርገው የነበረው ጥረት ጫፍ መድረሱን ፕሬዝዳንቱ አቶ አበረ አዳሙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የሴቶች ቀን፣ የሕጻናት ቀን፣ የውሃ ቀን እየተባለ እንደሚታወጀው ሁሉ ሰኔ 30ን ደግሞ በኢትዮጵያ የንባብ ቀን ሆኖ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲጸድቅ ብዙ ጥረት ከተደረገ በኋላ በአዲሱ ዓመት ይኸው እውን እንደሚሆን ይጠበቃል።
የሕግ አወጣጥ ሒደትን በተከተለ ሁኔታ ከባሕልና ቱሪዝም ጀምሮ በሁሉም መዋቅሮች ምክረ ሐሳቡ እንዲያልፍ መደረጉን የጠቀሱት አቶ አበረ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤንም በጉዳዩ ላይ እንዳነጋገሩ ለቢቢሲ ጠቅሰዋል።
ዕለቱ በይፋ ከታወጀ በኋላ ታዲያ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ የሃይማኖት አባቶችና ዕውቅ ፖለቲከኞች እንዲሁም ሌሎች በአገሪቱ ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች ንባብን የሚያነቃቁ ተግባራት በየደረጃው እንዲያከናውኑ ይደረጋል፣ ይህም በመገናኛ ብዙኃን በቀጥታ ይሰራጫል ይላሉ አቶ አበረ።
የሐሳቡ ረቂቅ ተወካዮች ምክር ቤት መድረሱን ለቢቢሲ ያረጋገጡት አቶ አበረ፣ በአዲሱ ዓመት እስከ ጥቅምት ወር ይጸድቃል ብለው እንደሚጠብቁ አብራርተዋል።
ቀኑ በተወካዮች ምክር ቤት ከጸደቀ በኋላ በሚኖር ትዕይንት ሰኔ 30 ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ የተመረጠ ትምህርት ቤት ተገኝተው፣ ለሕጻናት መጽሐፍ እንዲያነቡ ለማድረግ ሐሳብ መኖሩን አቶ አበረ ተናግረዋል።
ይህም በቀጥታ ሥርጭት ለሕዝብ እንዲተላለፍ እንደሚደረግ ዕቅድ መወጠኑን አውስተዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሌላ ታዋቂ ፖለቲከኞች፣ ጳጳሳትና ሼኮችም የተለያዩ ቦታዎች እየተገኙ የንባብ መርሃ ግብር ይታደማሉ፣ ያከናውናሉ።
"አሁን ላለው ፖለቲካዊ ምስቅልቅል አንዱ ምክንያት የንባብ መሳሳት ነው"
አሁን ያለው ፖለቲካዊ ምስቅልቅል እንዲፈጠር አንዱ ምክንያት የንባብ መሳሳት ነው ብሎ ማኅበራችን ያምናል ይላሉ አቶ አበረ።
በየቦታው በብሔር ተቧድኖ መገዳደሉም የዚሁ ቅጥያ ነው የሚሉት አቶ አበረ፣ አንባቢ ትወልድ ቢኖር ኖሮማ "ለምን ብሎ ሳይጠይቅ ገጀራውን ይዞ ወደሚገድለው ሰው አይሮጥም ነበር" ብለዋል፡፡
"አንባቢ ትውልድ እገሌ ጠላትህ ነው ሲባል ለምን ይላል እንጂ አዎ ብሎ ሆ ብሎ አይነሳም። አንባቢ የአንድን ሃይማኖት ወይም የአንድን ብሔር በጠላትነት አይፈርጅም። ጠያቂ አእምሮ ያልተፈጠረው ደግሞ አንባቢ ትውልድ ባለመፈጠሩ ነው" ይላሉ።
ይህን የትውልድ ክፍተት ለመሙላት ሲባል ማኅበሩ አንባቢ ትወልድን በመፍጠር ረገድ አዲስ ዘመቻ መጀመሩንና የተመረጡና ከደራሲዎቻቸው ይሁንታን ያገኙ መጽሐፍን በሶፍትኮፒ ማሰራጨት ወቅቱ የሚፈልገው ተግባር እንደሆነ አብራርተዋል።
"በኛ ግምገማ አሁን ትልቁ ችግር ኢትዮጵያ ውስጥ አንባቢ ትወልድ አለመኖሩ ነው" የሚሉት አቶ አበረ 120 ሚሊዮን ሕዝብ ባለበት አገር ትልቁ የመጽሐፍት ሥርጭት ቁጥር 5ሺ መሆኑ አስደንጋጭ ነው ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, ullstein bild
አቶ አበረ ይህን ሲያስረዱ ከዩኒቨርስቲ እስከ ታች ቀበሌ ድረስ ለማንበብ ብቁ የሆኑ ዜጎችን የማይናቅ አሐዝ ከግምት በማስገባት ነው።
"ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የተማረ ኃይል አለ ብለን እናምናለን። 50 የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ በርካታ የግል ኮሌጆች ከመኖራቸው በላይ በእያንዳንዱ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ትምህርት ቤቶች ተከፍተዋል። ከሺህ በላይ ወረዳዎች አገሪቱ ውስጥ አሉ። በእያንዳንዱ ወረዳ ደግሞ በርካታ ቀበሌዎች አሉ። በእነዚያ ቀበሌዎች ባሉ ትምህርት ቤቶች በእያንዳንዳቸው ቢያንስ አራት መምህራን አሉ። ይህ ሲደማመር በትንሹ ግማሽ ሚሊዮን ይሆናል። እንዲያም ሆኖ በመጽሐፍ ኅትመት ትልቅ ቁጥር ታተመ ከተባለ 5ሺህ ቅጂ ነው።"
አቶ አበረ ከመቶ ሚሊዮን ሕዝብ ባላት አገር ውስጥ ይህ የሳሳ የአንባቢ ቁጥር ብዙ እንደሚናገር የጠቀሱ ሲሆን አሐዙ አሳፋሪም አስደንጋጭም ነው ይላሉ።
"ከዚህ ሁሉ የምንረዳው በኢትዮጵያ ውስጥ አንባቢ ትውልድ አለመፈጠሩን ነው"
አቶ አበረ የአንባቢ ቁጥር በትውልዶች እያደገ መምጣት ሲኖርበት እየሳሳ መምጣቱን ዋቢ በመጥቀስም ያብራራሉ።
አሁን 5ሺህ ትልቅ ቁጥር ሆነ እንጂ፣ በአንጻሩ በደርግ ጊዜ 30ሺህ አንዳንዴም እስከ መቶ ሺህ ቅጂ መጻሕፍት ይታተሙ እንደነበር አስታውሰዋል።
በደርግ ጊዜ ትንሹ የህትመት ቁጥር 20 እና 30ሺህ ሆኖ አሁን ሕዝብ እጥፍ በጨመረበት ሁኔታ እንዴት ወደ 5ሺህ ቅጂ ወረደ የሚለው አሳሳቢ ነው የሚሉት አቶ አበረ፣ "ይህን ሁሉ ግምት ውስጥ ስናስገባ አንባቢ ትውልድ አለመፈጠሩን ነው የምንረዳው" ሲሉ ያስረዳሉ።
የንባብ ባሕል አለመኖር ደግሞ ውጤቱ በተለያዩ ሁኔታዎች እየተገለጹ እንደሆነ አቶ አበረ አብራርተዋል።
"ዛሬ አንድ ወጣት ወደ ዩኒቨርስቲ ሲላክ ተምሮ የራሱን የቤተሰቡንና የአገሩን ችግር እንዲፈታ እንጂ ሰው እንዲገድል አይደለም፤ ጫካ አይደለም የተላከው። ነገር ግን ወይ ጓደኛውን ገድሎ ወይም ራሱ ሞቶ አስክሬኑ ይመጣል። ይህ ሌላ ሳይሆን ያለማንበብ ያመጣው ጣጣ ነው።"
አሁን ባለው ፖለቲካዊ አሰላለፍ እጅግ ጥልቅ አንባቢ ነበር የሚባለው የ60ዎቹ ትውልድ ነው በብዛት በፊታውራሪነት ሆኖ እየዘወረው ያለው።
እንዴት ነው ማኅበራችሁ አሁን ላለው መገዳደል ምንጩ አንባቢ ትውልድ አለመኖር ነው ብሎ በጠባቡ ሊተረጉመው የቻለው ተብለው ከቢቢሲ የተጠየቁት አቶ አበረ፣ "ያ ትውልድ አንባቢ ነው። ይቃወም የነበረው ሥርዓትን እንጂ ከጎኑ የሚኖረውን ብሔረሰብ አልነበረም። አመዛዛኝ ትውልድ ነው የነበረው" ብለዋል።
የደራሲያን ማኅበር ይህን አገራዊ እውነታ ግምት ውስጥ በማስገባትም ነው የሶፍትኮፒ ሥርጭትና የንባብ ዘመቻን የወጠነው ይላሉ አቶ አበረ።
ለምን ወደ ሶፍትኮፒ ሐሳብ እንደመጡ ከቢቢሲ የተጠየቁት የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ትውልዱ ጋዜጣና መጻሕፍት ማንበብ ትቶ አብዛኛውን ጊዜውን በስልኩ ላይ እንደሚያሳልፍ በመረዳታችን ነው ብለዋል።
"መጻሕፍትን በሚወደው ሞባይሉ በኩል እንዲያገኘው ለማድረግ ነው እየሞከርን ያለነው" የሚሉት አቶ አበረ ከአንድ ድርጅት ጋር ድርድር አድርገን ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሰናል። ልክ እንደነ አማዞን መጻሕፍትን በኦንላይን ለመሸጥ ነው ያሰብነው" ሲሉ ሂደቱን አስረድተዋል።
መጻሕፍቱ በሶፍትኮፒ ከተገዙ በኋላ ሰዎች በነጻ ሊያራቧቸው ስለሚችል በዚህ ረገድ የቅጂ መብትን እንዴት ልታስተናግዱ ትችላላችሁ ተብለው የተጠየቁት አቶ አበረ፣ ይህ እንዳይከሰትና ሶፍትኮፒው እንዳይራባ የሚያደርግ ቴክኖሎጂ እንደሚጠቀሙ ገልጠዋል።
የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ከ61 ዓመት በፊት የካቲት 12 ቀን፣ በ1952 የተመሠረተ አንጋፋ ማኅበር ነው።
















