መጽሐፍትን በፍጥነት ለማንበብ ምን ማድረግ አለብን?

መጽሀፍ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ማንኛውንም አይነት መጽሐፍት በፍጥነት አንብቦ መጨረስ የበርካቶች ፍላጎት ቢሆንም አስቸጋሪ እንደሆነ ይነገራል። በሌላ በኩል አንድን መጽሐፍ በፍጥነት አንብቦ መጨረስ ሙሉ መልዕክቱን በደንብ ሳናገኘው እንድናልፍ ሊያደርግ ይችላል የሚል አመለካከትም አለ።

አብዛኞቻችን መጽሐፍትን በፍጥነት ማንበብ ልንወድ እንችላለን፤ ነገር ግን እንደሚታሰበው ቀላል አይደለም። በአንድ ሰዓት ውስጥ ምን ያህሎቻችን ጠለቅ ያለ ንባብ ማካሄድ እንችላለን?

በጣም የተለመደውና ብዙዎቻችን የምንሞክረው 'የገረፍ ገረፍ' ንባብ የሚባለውን ነው። በዚህ የንባብ አይነት በጽሁፉ ውስጥ ወሳኝ የሆኑትን ነገሮች ከላይ ከላይ ቶሎ ለማንበብ መሞከርን ያካትታል።

ሌላኛው መንገድ ደግሞ ጣቶቻችንን በመጠቀም አንዳንድ ወሳኝ ቃላት በሚገኙበት መስመር ላይ አጽንኦት ለመስጠት መሞከር ሲሆን ዓይኖቻችን ጣቶቻችንን በመከተል ያለምንም መረበሽ ቃላቱን ይመለከታል።

በእጅጉ እየተሻሻለ በመጣው የዘመኑ ቴክኖሎጂ ደግሞ አንዲትን ቃል ብቻ በአንድ ጊዜ እያሳዩ በፍጥነት መጽሐፍትን የሚያስነብቡ መተግበሪያዎችም መጥተዋል።

ከላይ የተጠቀሱት አይነት የንባብ መንገዶች በፍጥነት ለማንበብ ለሚፈልግ ሰው እርዳታ እንደሚያደርጉ ጥርጣሬ ባይኖርም ምን ያህሉን እናስታውሰዋለን የሚለው ግን ብዙዎችን የሚያከራክር ጥያቄ ነው።

ከእነዚህ ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የሥነ አእምሮ ባለሙያ የሆኑት ኪት ሬይነር ምርምር አድረገዋል። እ.አ.አ በ2016 በሰሩት ጥናት በፍጥነት ለማንበብ የሚደረጉ ሙከራዎችን ዳሰዋል።

በጥናቱ መሰረት አንዳንድ የፍጥነት አንባቢዎች አንድ ትልቅ መጽሐፍን በሰዓታት ውስጥ ጨርሰው ሃሳቡንም በአግባቡ መረዳት የሚችሉ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ቀናት ወስዶባቸው እንኳን የመጽሐፉን ጭብጥ በአግባቡ ላይረዱት ይችላሉ።

መጽሐፍ በምናነብበት ወቅት በዓይናችን 'ሬቲና' በሚባለው ክፍል ውስጥ የሚገኘው 'ፎቪያ' የተባለው አካል በብዙ ህዋሳትና ብርሃን አስተላላፊዎች የተሞላ ነው። እነዚህ ህዋሳት ብርሀንን በመከተል መጽሐፍትን በምናነብበት ወቅት እያንዳንዱን ቃል እያጣሩ ወደ ጭንቅላታችን የሚልኩ ሲሆን ጭንቅላታችን ደግሞ ለቃላቱ ትርጉም ይሰጣል።

አንዳንድ የፍጥነት አንባቢዎች 'ፎቢያን' በአግባቡ በመገልገል በአንድ ጊዜ በርካታ ቃላትን ለማንበብ ይጠቀሙበታል። ምናልባትም የፍጥነቱ ጉዳይ ከሰው ሰው የሚለያይበት አንደኛው ምክንያት ይህ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም ጭንቅላታችን ለቃላቱ ገና ትርጉም ሳይሰጥ ወደ ሌሎች ቃላት የምንሸጋገር ከሆነ ዝም ብሎ ጊዜ ማጥፋት ነው የሚሆነው ይላሉ ባለሙያዎች።

መጽሀፍ የምታነብ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በፍጥነት ለማንበብ የሚረዱ ነጥቦች

• መጽሐፍትን በምናነብበት ወቅት ጣቶቻችንን በእያንዳንዱ መስመር ላይ አድርጎ እነሱን እየተከተሉ ማንበብ

• ወሳኝ የምንላቸውን የመጽሐፍት ክፍልን በእስኪሪብቶ ወይንም በእርሳስ እያሰመሩ ማለፍ

• አንዴ ያነበብናቸውን ቃላት ደግሞ አለማንበብ (ይህንን ልማድ እየደጋገምነው እንኳን እንደምናደርገው አናውቅም)

• በመጨረሻም ግብ አስቀምጡ (በቀን፣ በሳምንት፣ በወር. . . . )

ታዲያ በፍጥነት ለማንበብና ቃላቱን በአግባቡ ለመረዳት መፍትሄው ምንድነው?

መጽሐፍትን በምናነብበት ወቅት በትንሹ ድምጽ እያወጡ ቃላቱ ለራሳችን እንዲሰሙ ማድረግ መጥፎ የንባብ ልምድ ወይም በፍጥነት እንዳናነብ የሚያደርገን ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፤ ነገር ግን ይህ እውነት አይደለም።

አንዳንድ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ድምጽ እያወጡ ማንበብ ቃላቱን በደንብ እንድንረዳቸው ያደርጋል። አሁንም ጥያቄው ድምጽ አውጥተንም ሆነ ጸጥ ብለን አነበብን፤ በፍጥነት ንባብ ውስጥ ምን ያህሉን እንረዳዋለን? የሚለው ነው።

መጽሀፍ የምታነብ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ምንም እንኳን በዚህ በቴክኖሎጂ በተራቀቀ ዘመን መጽፍትን በፍጥነት አንብቦ ሃሳቡን ሙሉ በሙሉ ለመረዳት የሚያስችሉ ናቸው የተባሉ ፈጠራዎች እዚህም እዚያም ብቅ ቢሉም ሁሉንም ሰው በእኩል ሁኔታ ውጤታማ ማድረጋቸው ግን አጠራጣሪ ነው።

አንዳንዶች የጨረፍታ ንባብ በቂያቸው ሲሆን ሌሎች ደግሞ ጊዜ ወስደው ማንበብን ይመርጣሉ። እዚህ ጋር ዋናው ነገር ለእራሳችን የሚሆንና ሳንጨነቅ መጽሐፍትን በአግባቡ እንድንረዳ የሚያስችለንን መንገድ መምረጡ ላይ ነው።

አንዳንድ ጊዜም እንደ ሁኔታዎች መለያየት የንባብ መንገዳችንም ሊለያይ ይችላል። ቀስ ብለን አንብበን ሙሉውን ሃሳብ ለመያዝ መሞከር ያለብን ጊዜ ሲኖር በሌላ አጋጣሚ ደግሞ አንዲት መረጃን ፍለጋ ቶሎ ቶሎ ገጾችን ልናገላብጥ እንችላለን።

በመጨረሻም በፍጥነት ለማንበብ አንድና አንድ መፍትሄ እንዳለ ሁሉም ባለሙያዎች ይስማማሉ፤ እሱም ሁሌም ቢሆን መጽሐፍትን ማንበብ ነው። ብዙ መጽሐፍትን ባነበብን ቁጥር ፍጥነታችን በራሱ ጊዜ እየጨመረ ይመጣል።

አንድ አነስተኛ መጽሐፍን ለማንበብ ሳምንት የፈጀበት ሰው ያለማቋረጥ ለሁለት ወራት ቢያነብ፤ በሁለተኛው ወር መጨረሻ ላይ ተመሳሳይ መጽሐፍ በአንድ ቀን አንብቦ መጨረስን ይለማመዳል።

ብዙ ሰዎች የሚሳሳቱት መጽሐፍ አንብቦ መጨረሱ ላይ ብቻ ትኩረት ሲያደርጉ ነው፤ ዋናው ቁም ነገር ግን መጽሐፉን መጨረስ ሳይሆን በአግባቡ መረዳቱ ላይ ነውና።