ዓይነ ስውሩ የተሰጠውን ጽሁፍ ባለማንበቡ የአሜሪካ ዜግነት ተከለከለ

የፎቶው ባለመብት, CBS
አንድ ዓይነስውር የአሜሪካ የኢሚግሬሽን መስሪያ ቤት በብሬል በተጻፈ የእንግሊዝኛ ንባብ ፈተና ምትክ ለአይናማዎች የተዘጋጀን ጽሁፍ ሰጥተውት ፈተናውን ባለማለፉ የአሜሪካ ዜግነት ተከለከለ።
ሉሲዮ ዴልጋዶ የተባለው የ23 ዓመት ወጣት ሲወለድ ጀምሮ ዓይነ ስውር የነበረ ሲሆን ከስድስት ዓመታት በፊት ነበረ አሜሪካ የገባው።
ዴልጋዶ እንዳለው ምንም እንኳን ሙሉ ለሙሉ ዓይነ ስውር ቢሆንም የኢሚግሬሽን ሰራተኞቹ በወረቀት ላይ የሰፈረ ጽሁፍ እንዲያነብ ሰጥተውት ለማንበብ አልቻለም።
በአሜሪካዋ ኢሊኖይ ግዛት ሕግ መሠረት ዴልጋዶ ዓይነ ስውርነቱ የተረጋገጠ ቢሆንም፤ ከዶክተር ይህንኑ የሚገልጽ ማስረጃ እንዲያቀርብ ተነግሮታል።
የዕይታ ምርመራውን ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ከወሰደ በኋላ ከአሜሪካ የዜግነትና ስደተኝነት አገልግሎት መስሪያ ቤት በቅርቡ የደረሰው ደብዳቤ ዜግነት ለማንኘት ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ መደረጉን የሚያመለክት ነው።
"በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተጻፈን ዓረፍተ ነገር ማነበብ አልቻልክም" ይላል የደረሰው ደብዳቤ። "ዜግነት ለማግኘት በተሰጠህ ፈተና ላይ ያለውን የንባብ ክፍል ለማለፍ የሚያስችል ነጥብ ማግኘት አልቻልክም" በማለት ጥያቄው ውድቅ መሆኑን አመልክቷል።
ዓይነ ስውሩ ዴልጋዱ ለእሱ በሚያመች ሁኔታ ፈተናው አለመቅረቡ እንዳስደነገጠውና በውጤቱም ማዘኑን ለዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ገልጿል።
በፈተናው ወቅት ዓይነ ስውር መሆኑን የሚገልጽ ማስረጃ ከሐኪም ዘንድ እንዲያመጣ የተነገረው ቢሆንም የጤና ኢንሹራንስ ስለሌለው ለምርመራው መክፈል አልቻለም።
የአሜሪካ የዜግነትና ስደተኝነት አገልግሎት ቃል አቀባይ ስለዚህ ጉዳይ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ዴልጋዶ ፈተናውን ከወሰደ ከወራት በኋላ ለዓይነ ስውራን ተፈታኞች የንብብ ፈተናውን በብሬል መስጠት እንደጀመሩ ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት የዓይነ ስውሩ ዴልጋዶ ጉዳይ ከተዘገበ በኋላ የኢሚግሬሽን መስሪያ ቤቱ ዴልጋዶ ሌላ ፈተና እንዲወስድ ቀጠሮ እንደተያዘለት ለጠበቃ ነግሮታል።












