እውን ልብ-ወለድ መፃሕፍትን ማንበብ በጎ ሰው ያደርገናል?

እውን ልብ-ወለድ መፃሕፍትን ማንበብ በጎ ሰው ያደርገናል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በየቀኑ ከ1.8 ሚሊዮን በላይ መፃሕፍት አሜሪካ ውስጥ ይሸጣሉ፤ እንግሊዝ ውስጥ ደግሞ ግማሽ ሚሊዮን። ስለሃገራችን የመፃሕፍት ገበያ ውሉ የታወቀ መረጃ ባይኖርም የሚያኩራራ እንዳልሆነ ግን በርካቶች ይስማማሉ።

ዘመኑ ደግሞ በብዙ ጉዳዮች የተወጥርነበት ነው። መፃሕፍት እንዳናገላብጥ ሊያደርጉን የሚቋምጡ ደንቃራዎች ብዙ ናቸው። ቢሆንም ቅሉ አንባቢ አሁንም አለ።

'ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል' ይባላል። እውን ማንበብ መሉ ሰው ያደርጋል? ምን ዓይነት መፃሕፍት ማንበብስ ነው ሙሉ ሰው የሚያደርገው? ሙሉ ሰው ማለትስ እንዴት ያለው ነው? እኒህን ጥያቄዎች ለጊዜ ገታ እንዳርግ እና ልብ ወለድ መፃሕፍት ላይ እናተኩር።

ለመቼትና ለይዘት ወሰን የሌላቸውን ልብ-ወለድ መፃሕፍትን ማንበብስ የተሻለ ሰው ያደርጋል?

አሪስቶትል ልብ-ወለዶች ላይ 'አሳዛኝ ክስተቶች ስንመለክት ሁለት ዓይነት ሰሜቶች ይውጡናል' ይላል፤ አንድ ለገፀ-ባሕርዩ አንዱ ደግሞ ለራሳችን።

ሳናስተውለው ራሳችንን በገፀ-ባሕርያቱ ቦታ ተክተን፤ እነርሱ የሚሆኑትን እንሆናለን። አንዳንድ ጊዜ እኛ ብንሆን ምን እናደርግ ይሆን ስንል እንጨነቃለን፤ ካሳለፍነው ወይም ከሚመጣው ሕይወታችን ጋር እያነፃፀርነው በሐሳብ ጭልጥ የምንልበት አጋጣሚ በርካታ ነው።

ራሳችንን በገፀ-ባሕርያቱ ቦታ ተክቶ ማሰብ ሌሎችን ለመረዳት እጅግ ጠቃሚ ነው። ካናዳዊው የኮግኒቲቭ ሳይኮሎጂስት [ግርድፍ ትርጉም፡ የግንዛቤ ስነ-ልቡና አጥኚ] ኪይዝ አትሊ 'ይህ ማለት እኮ የጭንቅላታችን ፍላይት ሲሙሌተር ነው' ይላሉ።

«አስቡት አውሮፕላን አብራሪዎች መጀመሪያ ሥልጠና የሚወስዱት 'ፍላይት ሲሙሌተር' በተሰኘ መሬት ላይ በተተከለ መሣሪያ እንጅ አየር ላይ አይደለም። እንደዚህ ሁሉ ልብ-ወለድ የሚያነቡ ሰዎች እያንዳንዷን ገፅ በከፈቱ ቁጥር የሕይወት ቀመርን እያጠኑ ነው የሚመጡት።»

እንደ ስነ-ልቡና ባለሙያው ገለፃ አንዳንድ ጊዜ ከራሳችን በላይ ለገፀ-ባሕርያቱ ትኩረት እንሰጣለን። አደጋ ውስጥ ሲገቡ ልባችን በፍጥነት ይመታል፤ ትንፋሻችን ጮክ ብሎ ሊሰማ ሁላ ይችላል። ምንም እንኳ ውስጣችን ገፀ-ባሕርያቱ ላይ እየተከሰተ ያለው ነገር እኛ ላይ እየሆነ እንዳልሆነ ብንረዳም።

የምናነባቸው ቃላት ከጭንቅላታችን ጋር የሚጫወቱት ጨዋታ መፃሕፍትን ስናነብ ከሚሰሙን የጋራ ስሜቶች አንዱ ነው። ለምሳሌ 'መማታት' የሚለውን ቃል ስናነብ ጭንቅላታችን ሰዎችን መማታት ከሚለው ጋር ያይዘዋል። ገፀ-ባሕርይዋ መብራቱን አጠፋች የሚል ብናነብ ደግሞ ጣታችን ከሚሰራቸው ሥራዎች ጋር ያያይዘዋል።

እውን ልብ-ወለድ መፃሕፍትን ማንበብ በጎ ሰው ያደርገናል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ገፀ-ባሕርያቱ የሚሰማቸው እንዲሰማን ግን መጀመሪያ እነማን እንደሆኑ፣ ምን እንደሆኑ፣ ምን እንደሚሠሩ ልናውቅ ይገባል። ከዚያ ምን እንደሚያስቡ፣ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ አስቀድመን ልናውቅ እንችላለን። ይህ የጭንቅላት ክህሎት 'ቲዎሪ ኦፍ ማይንድ' ይባላል።

ግን አንድ ጥያቄ ብዙዎችን ሰቅዞ የያዘ ይመስላል። እውን ልብ-ወለድ የሚያነቡ ሰዎች ኢ-ልብወለዳዊ መፃሕፍትን ማንበብ ከሚቀናቸው ሰዎች የተሻለ የአስተሳሰብ ዕድገት ያመጣሉ? የሚል።

ሌላኛዋ የስነ-ልቡና ባለሙያ ዳያና ታሚር ልብ-ወለድ መፃሕፍትን የሚያነቡ ሰዎች የተሻለ ማሕበረሰባዊ ግንዛቤ [ሶሻል ኮግኒሽን] አላቸው ትላለች። «ልብ-ወለድ የሚያነቡ ሰዎች ሌሎች ሰዎች ምን እንደሚያስቡ እና ምን እንደሚሰማቸው ከሌሎች በተሻለ መልኩ ማወቅ ይችላሉ።»

ሰዎች ልብ-ወለዶችን ሲያነቡ ጭንቅላታቸው ከሌላው ጊዜ በበለጠ ይሠራል። ይህም ለጭንቅላት ዕድገት የራሱ አስተዋፅኦ አለው ባይ ናት ባለሙያዋ።

ሰዎች ከገፀ-ባሕርይ ጋር ብቻ ሳይሆን ዜናም ይሁን ሌላ ማሰራጫ ጣብያ ላይ ካዩት ወይም ከሰሙት ምስኪን ሰው ጋር ራሳቸውን አጣምረው ሃዘኔታ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። ነገር ግን ልብ-ወለድ የገፀ-ባሕህያትን ውስጥ በትኖ ያሳየናል። ዜና ግን ይህንን ማድረግ አይችልም። አልፎም ልብ-ወለድ ላይ የተፃፉ ባህሕያት የሆኑት ነገር የውሸት ነው ብለን የምናምንበት ቀዳዳም የለንም። ሌላው ጠንካራ ጎን ደግሞ መፅሐፍት ላይ ያነበብናቸው ገፀ-ባሕርያትን ለበርካታ ዘመን መርሳት አለመቻላችን ነው።

በርካታ ጥናቶች ልብ-ወለድ ማንበብ የሰው ልጅ በጎ አስተሳሰብ እንዲኖረው እና የሰው ልጅን በቀላሉ እንዲረዳ ያደርገዋል የሚል መድምደሚያ ይዘው ብቅ ብለዋል። አንዳንድ ትምህርት ቤቶች እንደውም ልብ-ወለድን በትምህርት ሥርዓታቸው ውስጥ ማካተት ጀምረዋል።

ወጣም ወረደ ማንበብ ለተሻለ አስተሳሰብ እንደሚያበቃ ባለሙያዎችና ፀሐፊያን ሁሌም ያሳስባሉ። እስቲ እናንብብና የሚሆነውን እንይ. . .