ዕፅዋትን ፎቶ አንስቶ በሽታ የሚለይ ቴክኖሎጂ የፈጠሩት የጅማ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን

ቦኤዝ ብርሃኑ እና ጀርሚያ ባይሳ

የፎቶው ባለመብት, Debo engineering/FB

የምስሉ መግለጫ, ቦኤዝ ብርሃኑ እና ጀርሚያ ባይሳ

ቦኤዝ ብርሃኑ እና ጀርሚያ ባይሳ ይባላሉ። የጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ናቸው። በርካታ ጥናቶች አድርገዋል። የአካባቢውን አርሶ አደር ችግር ለመቅረፍ ደፋ ቀና ይላሉ።

ፎቶ አይቶ የእንስሳት በሽታ የሚለይ መተግበሪያ ፈጥረው ለሥራ አብቅተዋል። ይህን መተግበሪያ አሁን በርካታ አርሶ አደሮች እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።

ነገር ግን እዚህ ለመድረስ ብዙ ውጣ ውረዶችን አይተዋል። እንዲሁ በቀላሉ የመጣ ስኬት አይደለም ይላሉ?

ጀርሚያ በኮምፒውተር ሳይንስ እንዲሁም በሲቪል ምህንድስናም የመጀመሪያ ድግሪ አለው።ማስተርሱን በኮምፒውተር ኔትዎርኪንግ ይዟል። ቦኤዝ ደግሞ በኤሌክትሪካልና ኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ድግሪውን አግኝቷል። የማስተርስ ዲግሪውን ደግሞ በኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ እያጠናቀቀ ይገኛል።

ሁለቱ ተመራማሪዎች ደቦ ኢንጂነሪንግ የተባለ ድርጅት አቋቁመዋል። በዚህ ድርጅት አማካኝነት ነው የተለያዩ ጥናቶችን እያደረጉ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን ለሕብረተሰቡ የሚያስተዋውቁት።

"ደቦ ኢንጂነሪንግ በፈረንጆቹ 2018 ዓ.ም. ነው የተቋቋመው" ይላል ጀርሚያ ባይሳ።

"ከቦኤዝ ጋር የተዋወቅነው የማስተርስ ተማሪ ሳለን ነው። ቦኤዝ የኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ እኔ ደግሞ የኮምፒውተር ኔትዎርኪንግ ተማሪ ነበርኩ። የጥናታችን ርዕስ የነበረው 'ኢመርጂንግ' [አዳዲስ] ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ ችግር መፍታት የሚል ነበር። ይሄንን ነገር ለምን ወደ ተግባር አንቀይረውም ብለን ነው የተነሳነው።"

"ያው እንደሚታወቀው ደቦ የኢትዮጵያውያን ተባብሮ የመሥራት ባህል ነው። ይህንን ባህል ለምን ከቴክኖሎጂ ጋር አጣምረን ችግር የሚቀርፉ ሐሳቦች አናፈልቅም ብለን ወደ ሥራ ገባን" ይላል ጀርሚያ።

ጀርሚያ አክሎ ሥራችን ምርምርና ጥናት ስለሆነ ለምን መሬት ያለ ችግርን የሚፈታ ቴክኖሎጂ አንሥራ ብለው እንደተነሱ ይናገራል።

ቦኤዝ በበኩሉ ምንም እንኳ ቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረቱ የተለያዩ ሥራዎችን ብንሠራም ዋናው ትኩረታችን 'አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ' [ሰው ሠራሽ ልህቀት] ነው ይላል።

"ሁለታችንም በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዙሪያ የተለያዩ ጥናቶች አካሂደናል። አብዛኛው የሕብረተሰባችን ክፍል ኑሮው ግብርና ላይ የተመሠረተ ስለሆነ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን እንዴት ወደ ግብርና ልናመጣ እንችላለን ስንል ጠየቅን።"

ዕጽዋቶችን በሽታ የሚለይ ፈጠራ
የምስሉ መግለጫ, በድሮን በተነሳ ፎቶ የዕጽዋቶችን በሽታ መለየት ይቻላል

የዕፅዋት በሽታን በፎቶ መለየት

የጀርሚያና ቦኤዝ ሥራ የሆነው መተግበሪያ አርሶ አደሮች ዕፅዋትን ፎቶ አንስተው በሽታውን መለየት እንዲችሉ የሚያደርግ ነው።

"ያለንበት አካባቢም ሆነ ሌሎች ቦታዎች የገበሬው ዋናው ችግር የዕፅዋት በሽታ ነው። በሽታው ከተሠራጨና ማሳዎች ከወደሙ በኋላ ነው በሽታው ምንድነው የሚለው የሚለየው" ይላል ቦኤዝ።

አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ 'ኢሜጅ' ተመልክቶ በሽታን ከወዲሁ መናገር ይችላል ይላል ቦኤዝ አክሎ።

"ለምሳሌ ቡና በበሽታ ከሚጠቁ ዕፅዋት መካከል ነው። በቆሎም እንዲሁም መመረት ከሚኖርበት 50 በመቶ ያክሉ በበሽታ ምክንያት ይወድማል። ይሄ አንድ ክልልን መመገብ የሚችል ብዛት ያለው በቆሎ ነው። እስካሁን ድረስ ለዚህ ችግር የምንጠቀመው መፍትሄ ኋላ ቀር ነው።"

ቦኤዝ፤ አርሶ አደሮች ተንቀሳቃሽ ስልካቸውን ተጠቅመው ዕፅዋትን ፎቶ በማንሳት ምን በሽታ እንዳለ መለየት የሚችል መተግበሪያ ነው የፈጠርነው ይላል።

"አልፎም ለዚያ በሽታ ምን ዓይነት መፍትሄ መፈለግ እንዳለባቸው እንዲጠቁም አድርገን ነው ቴክኖሎጂውን የሠራነው።"

"በዋነኛነት አሁን እየሠራን ያለነው ቡና ላይ ነው። የውጭ ንግዱን እየደገፈ ያለ ትልቅ ምርት ስለሆነ፤ ቡና ላይ መሻሻል መጣ ማለት የውጭ ገበያውም ተሻሻለ ማለት ነው።"

ሁለቱ ተመራማሪዎች በቆሎ ላይም ይህንን ቴክኖሎጂ ተግባራዊ እያደረጉ እንደሆነ ይናገራሉ።

ይህ ቴክኖሎጂ በፈረንጆቹ 2018 ነው ወደ ሥራ የገባው። መጀመሪያ ከነበረው 'ቨርዥን' [የመጀሪያው ዕትም] ተሻሽሎ አሁን የበለጠ ዘምኖ እንደቀረበም ያወሳሉ።

ቦኤዝና ጀርሚያ የድሮን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ነው ማሳዎችን የሚያጠኑት። ይህን ቴክኖሎጂ ተጠቅሞው ኦሮሚያ ውስጥ ሸቤ የሚባል ቦታ ያለን የዕፅዋት በሽታ መለየት እንደቻሉ ይናገራሉ።

የድሮን ቴክኖሎጂውን የሚጠቀሙት ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር እንደሆነ ቦኤዝ ይናገራል።

ሁለቱ ምሁራን ይህንን ቴክኖሎጂ ለገበሬዎች የሚያቀርቡት ጂአይዜድ ከተባለው የጀርመን ተራድዖ ድርጅት ጋር በመተባበር ነው። "እኛ አገልግሎቱን እናቀርባለን፤ እነሱ ደግሞ መሠረተ-ልማቱን ይዘረጉልናል። ጂአይዜ ለገበሬዎች ሁሉም ነገር የተሟላለት የሞባይል ስልክ ጨምሮ ነው የሚያቀርብላቸው።"

ተክሎቻቸውን የሚያርሙ ሴቶች

መተግበሪያው ለገበሬው ምቹ ሆኖ ተሰርቷል?

ቦኤዝ የጀርመኑ ተራድዖ ድርጅት ለ2ሺህ የቡና ገበሬዎች ይህንን መተግበሪያ በነፃ እንዳቀረበ ይናገራል።

ለመሆኑ መተግበሪያው ምን ያህል ለገበሬው እንዲመች ሆኖ ተሰርቷል? የኢንተርኔት ዝርጋታስ ይጠይቃል?

"መተግበሪያው ምንም ዓይነት ኢንተርኔት አይጠይቅም። ከገበሬው የሚጠበቀው ቅጠሉን ፎቶ ማንሳት ብቻ ነው። በሽታ ካለ አለ ብሎ ይነግረዋል። ከሌለም እንዲሁ። ይህንን የምንሠራው ከግብርና ባለሙያዎች ጋር ተባብረን ነው።"

ቦኤዝ ጅማ እንደመሆናችን መጠን የመብራት መቆራረጥና ሌሎች እክሎች በተደጋጋሚ ይገጥሙናል ይላል። ነገር ግን "የእኛ መተግበሪያ ለየት የሚያደርገው ኢንተርኔት ላይ ጥገኛ አለመሆኑ ነው" ሲል ለገበሬው ምቹ ሆኖ መሠራቱን ያወሳል።

መተግበሪያው በተለያዩ የሃገር ውስጥ ቋንቋዎች እንደሚሠራና በድምፅም ትዕዛዝ እንደሚቀበልም ይናገራል።

ቦኤዝ እንደሚለው በአንድ መድረክ ላይ ተወዳድረው ካሸነፉ በኋላ "ማይክሮሶፍት የተሰኘው ኩባንያ ለአንድ ዓመት ያክል ሰርቨራቸውን እንድንጠቀም ፈቅደውልናል" ይላል።

ተመራማሪው አክሎ ከቴክኒካል እክሎች በላይ መረጃ ስብሰባ ላይ ትልቁ ማነቆ ሆኖባቸው የነበረው የፋይናንስ እጥረት እንደሆነ ያስታውሳል።

ወደፊትም ለሚያደርጓቸው ምርምሮች የገንዘብ እጥረት ችግር ቢኖርባቸውም እንኳ የራሳቸውን የሰው ኃይል አሰባስበው ምርምራቸውን እንደሚቀጥሉ ቦኤዝ ይናገራል።

ከመንግሥት ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች፤ ከግብርና ሚኒስቴር አሊያም ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ምንም ዓይነት ድጋፍ ባናገኝም ተወዳድረን ስናሸንፍ በምናገኛቸው የገንዘብ ሽልማቶች እየታገዝን ነው ለዚህ የደረስነው ይላል ጀርሚያ።

ሁለቱ ምሁራን እስካሁን ድረስ ከጎናቸው ሆኖ ሁሉን ነገር በአቅሙ እያገዛቸው ያለው ጅማ ዩኒቨርሲቲ እንደሆነ ከምሰጋና ጋር መግለፅ ይሻሉ።

ቦኤዝና ጀርሚያ መተግበሪያው ለከተማ ግብርናም እንዲውልና ሰዎች ስልካቸው ላይ ጭነውት የጓሮ አትክልቶቻቸውን ጤና እንዲከታተሉበት ይሻሉ።

"ይህንን ሁሉ ጨርሰናል። እየተጠባበቅን ያለነው ወደሥራ እንድንገባ የሚያስችለን ፋይናንስ ነው" ይላል ቦኤዝ።

ሁለቱ ምሁራን በፎቶ አማካይነት በሽታ ከሚለየው መተግበሪያ ባለፈው ኮቪድ-19ኝን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አማካይነት መለየት የሚቻልበትን መንገድ አሳድገዋል።

በርካታ ውድድሮች ላይ ቀርበው አሸንፈዋል። ከተለያዩ ድርጅቶች እውቅና አግኝተዋል። 'አሁንም ወደፊት መግፋታችንን እንቀጥላለን። አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን ችግር ፈቺ ለሆኑ ቴክኖሎጂዎች እናውላለን' ይላሉ።