ቻይና 'ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች' እንዳይገነቡ ገደብ ጣለች

ሕንጻ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቻይና በትናንሽ ከተሞች "እጅግ ረዣዥም ከፍታ ያላቸው ሕንጻዎች" እንዳይገነቡ ገደብ ጣለች።

ከሦስት ሚሊዮን በታች ሕዝብ ያሏቸው ከተሞች ከ150 ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው ሰማይ ጠቀስ ፎቆች እንዳይገነቡ ተከልክለዋል።

ከዚያ በላይ የሆነ ሕዝብ ያላቸው ከተሞች ደግሞ ከ250 ሜትር በላይ ከፍታ ያላቸው ሕንጻዎችን መገንባት አይችሉም።

ከ500 ሜትር በላይ ከፍታ ያላቸው ሕንጻዎች እንዳይገነቡ የተጣለ ገደብ ቀድሞውኑም ሥራ ላይ ነበር።

632 ሜትር የሚረዝመው የሻንጋይ ማማ እና የ599.1 ሜትር ርዝመት ያለው የሼንዘኑ ፒንግ አን የንግድ ማዕከልን ጨምሮ ቻይና ከዓለማችን ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች የተወሰኑትን ገንብታለች።

እንደ ሻንጋይ እና ሼንዘን ባሉ በተጨናነቁ ከተሞች ሰማይ ጠቀስ ፎቆች ቢያስፈልጉም በሌሎች ከተሞች የመሬት እጥረት አለመኖሩን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ገለጸዋል።

በሌሎች ከተሞች የሚደረጉት ግንባታዎች በአብዛኛው ለታይታ የተገነቡ ናቸው ተብሏል።

በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መጀመሪያ ላይ በሼንዘን የሚገኘው እና 350 ሜትር የሚረዝመው ታሪካዊው ሰማይ ጠቀስ ኤስኢጂ ፕላዛ ሕንጻ በመወዛወዙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲሸሹ ታይተዋል።

ቻይና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ የታይታ ፕሮጀክቶችን እያስቆመች ነው። የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ለዓይን የሚስቡ ሕንጻዎችን የመገንባት አባዜንም ተችተዋል።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ቻይና "አስቀያሚ የሕንጻ ግንባታዎች" ላይ እገዳ ጥላለች።

የቶንግጂ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሕንጻ እና የከተማ ፕላን ኮሌጅ ምክትል ኃላፊ ዣንግ ሻንጉው "ሰዎች በታሪክ ሊሰፍር የሚችል ነገር ለመሥራት በጣም በሚቸኩሉበት እና በሚጓጉበት ደረጃ ላይ ነን" ሲሉ ለሳውዝ ቻይና ሞርኒንግ ፖስት ተናግረው ነበር።

"እያንዳንዱ ሕንጻ ለየት ብሎ እንዲገኝ ሲሉ አልሚዎች እና የከተማ እቅድ አውጪዎች ጥግ ድረስ በመሄድ አዲስ እና እንግዳ ነገር ለመሥራት ይሞክራሉ" ብለዋል።

የቤቶች እና ከተማ-ገጠር ልማት ሚኒስቴር እና የአደጋ ጊዜ አስተዳደር ሚኒስቴር በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ ከሦስት ሚሊዮን የማይበልጡ ነዋሪዎች ያሏቸው ከተሞች ከ150 ሜትር በላይ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻ ለመገንባት ከፈለጉ ልዩ ፍቃድ መጠየቅ እንዳለባቸው አስረድተዋል።

ነገር ግን እነዚህ ከተሞች በምንም ዓይነት ሁኔታ ከ250 ሜትር በላይ የሆነ ሕንጻ መገንባት አይችሉም።

በተመሳሳይ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ያሏቸው ከተሞች ከ250 ሜትር በላይ ከፍታ ያለው ሰማይ ጠቀስ ሕንጻ ለመገንባት በተወሰኑ ሁኔታዎች ፈቃድ ሊጠይቁ ይችላሉ። ከ500 ሜትር በላይ የሆኑ ሕንጻዎች ላይ ግን ጥብቅ እገዳ ተጥሏል።

አዳዲሶቹን ሕጎች የሚጥሱ ፕሮጀክቶችን ያጸደቁ ሰዎች "የእድሜ ልክ ተጠያቂነት" እንደሚጠብቃቸው በመግለጫው ተገልጿል።

እርምጃው የቻይና ማኅበራዊ ሚዲያ የሆነው ዌይቦ ላይ በብዛት ይሁንታ አግኝቷል። እጅግ በጣም ከፍተኛ ርዝመት ያላቸው ሰማይ ጠቀስ ፎቆች "አያስፈልጉም… ለታይታ የተሠሩ ናቸው" ሲሉ ብዙዎች አስተያየት ሰጥተዋል።