የአየር ንብረት ለውጥ የኢትዮጵያን ቡና ተፈላጊነት እንደሚጨምር ተጠቆመ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የወቅቱ የዓለማችን አሳሳቢ ሁኔታ የሆነው የአየር ንብረት ለውጥ በበርካታ ነገሮች ላይ ለውጥ እያስከተለ ነው፤ ከእነዚህም መካከል የቡና ምርት አንዱ ነው።
ቡና የሚበቅልባቸው በርካታ የዓለማችን አካባቢዎች በበካይ ጋዞች ምክንያት በሚከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ ምርታቸውና ጣዕማቸው እንደሚቀየር እየተነገረ ነው።
በዚህ ጊዜ ሚሊዮኖች የሚጠጡትን ቡና ጣዕሙ እንደተጠበቀ ሊያቀርቡ ከሚችሉ ጥቂት አገራት መካከል ኢትዮጵያ ትጠቅሳለች። በዚህም በቀጣይ ጊዜያት የኢትዮጵያ ቡና ተፈላጊነት የበለጠ እንደሚጨምር እየተነገረ ነው።

በሮስትዎርክስ ኮፊ ጥግ የተተከለው የቡና ዛፍ የመጣው ከኢትዮጵያ ነው። በስጦታ መልክ ይህን የቡና ተክል ያገኘው ቤተሰብ የቡናውን ሕይወት ለማየት በሚል ነው የተከለው።
የዚህ ቤተሰብ የቡና ንግድ በ90ዎቹ ከፊንላንድ ወደ እንግሊዝ ሲዘዋወር ይህም መገኛውን ከኢትዮጵያ ያደረገው የቡና ተክል አብሯቸው ተጓዘ።
ይህ የቡና ተክል ለ30 ዓመታት ያክል ምንም ፍሬ አላፈራም ይላል አሁን የቤተሰቦቹን ኩባንያ የሚያስተዳድረው ዊሊ ሊትል።
ነገር ግን ይህ የቡና ችግኝ በስተመጨረሻ አጎነቆለ። ሊትል በዚህ ሳይገረም አልቀረም።
የቡናው ተክል ያጎነቆለው በተነፃፃሪ ሞቃታማ ወደሆነ ቦታ ስለተዘዋወረ ይሁን አሊያም ጊዜው ስለደረሰ ሊትል የሚያውቀው ነገር የለም።
ቡናው በማበቡ የተደነቀው ሊትል ችግኙን በአግባቡ ይንከባከበው፤ ውሃ ያጠጣው፤ ማዳበሪያ ይሰጠው ጀመር።
ነገር ግን ሃምሳ ግራም ከሚሞላ ያልደረሰ ፍሬ በቀር የቡናው ተክል ምንም ሊሰጥ አልቻለም። ሊትል ግን ተስፋ አልቆረጠም።
በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ተክሉ የተሻለ ምርት መስጠት ቻለ። 400 ግራም የሚሆን ፍሬ ሰጠ። ይህ ሲፈለፈል 50 ግራም ለጋ ቡና ይወጣዋል።
ይህ ቡናውን ቆልቶ ለናሙና ያክል የሚሆን ምርት ለማግኘት በቂ ነበር። ሊትል ሃምሳውን ግራም ለሁለት ከፍሎ ሃያ አምስቱን ቆላው።
ቡናው ከፈላ በኋላ የሊትል ኩባንያ ሰዎች ተሰባስበው ለመቅመስ ተዘጋጁ። አንድ የቡና ስኒ 12 ግራም ፍሬ ይሆናል። ይህም ማለት ቡናው ከሁለት ስኒ አይዘልም ማለት።
ሊትል ቡናውን ቀመሰው። ጣዕሙ ለየት ያለ ነው። ምንም እንኳ ቡናው እንደተለመደው የኢትዮጵያ ቡና ግሩም የሚባል ባይሆንም ለየት ያለት የቸኮሌት ቃናና ጣዕም ያለው ሆነ።

የፎቶው ባለመብት, Roastworks Coffee Co
ቡና እና የአየር ንብረት ለውጥ ምን አገናኛቸው?
የትየለሌ የዓለማችን ሰዎች ጠዋት ጠዋት የሚጠቱት በቀን ውስጥ ሳይቀምሱት የማይውሉት ቡና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ያለው ቁርኝት አሉታዊ ነው።
በየቀኑ የሚጠጣ ቡና ከ300 ግራም በላይ ተመጣጣኝ በካይ የሆነ ካርበን ያመነጫል። ይህ በዓመት ሲሰላ 116 ኪሎ ግራም ይሆናል። በሌላ አነጋገር አንድ መኪና 1 ሺህ ማይል ተጉዞ ከሚያመነጨው ጭስ በላይ ማለት ነው።
አንድ ስኒ ቡና የሚያመነጨው የበካይ ነገር መጠን ቡና አየር ንብረት ላይ የሚያደርሰው ጫና ከአንድ ብርጭቆ ወይን በላይ ነው።
50 በመቶ የሚሆነው የካርበን ልቀት የሚመነጨው ገበሬዎች ቡናው በሚያበቅሉበት ወቅት ነው። 20 በመቶ ደግሞ ከተረፈ ምርት ይመነጫል። ይህን የልቀት መጠን ቡናን ቤት ውስጥ በማብቀል መቀየር ይቻል ይሆን?
ምንም እንኳ የቡና ምርትን ለማመላለስ ጥቅም ላይ የሚውለውን ትራንስፖርት መቀነስ ለውጥ ቢያመጣም ዋናው ቁም ነገር ግን ቡና የትና እንዴት ይመረታል የሚለው ነው።
የአየር ንብረቱ እየተለወጠ ሲመጣ በአንድ ወቅት ለቡና ምርት አመቺ የሆኑ ሥፍራዎች እየደረቁ ሌሎች ቦታዎች እየተመነጠሩ መሄዳቸው አይቀርም።
በጣም ታዋቂው የቡና ዓይነት አራቢካ [ኮፊ አራቢካ] የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም አይችልም።
ኢትዮጵያና ኬንያ ቡናን ለማምረት ወደፊት የበለጠ አመቺ የሚባሉ ቦታዎች ናቸው ተብሎ ተተንብዮላቸዋል። በተቃራኒው ደግሞ ብራዚል ውስጥ ያለው ለቡና አመቺ የሆነው ቦታ እና ኒካራጉዋ የሚገኘው መሬት ዝቅተኛ ሥፍራ ላይ ስላሉ ይጎዳሉ የሚል ትንበያ አለ።
ሊትል፤ ከፍታ ቦታ ለቡና ምርት አመቺ ነው ይላል። "ቡና ልክ እንደ ተራራማ ቦታ ደረቅ ያለና ለስላሳ አየር ይፈልጋል" ይላል። በእንደዚህ ዓይነት ሥፍራ የበቀለ "ሃይ ግሮውን" የተባለው ቡና ዋጋውም ከፍ ያለ ነው።
ምንም እንኳ ቡናን ቤት ውስጥ ማብቀል ከአየር ንብረት ለውጥ አንፃር ጥቅም ቢኖረውም የኢትዮጵያ ቡና ለየት የሚያደርገውን ዓይነት የእሣተ ገሞራ አፈር ማግኘት የማይታሰብ ነው።
አጥኚዎች የአየር ንብረቱን የማይጎዳ የቡና ዝርያ ለማግኘት ወዲያ ወዲህ እያሉ ነው። ይህ ከተሳካ ቡናን በቀዝቃዛ ሥፍራም ማብቀል ይቻላል ማለት ነው።
"ሊትል ምንም እንኳ በጓሯችን ቡናን ማብቀል ብንችልም ኢትዮጵያ እና ኮሎምቢያ የሚያመርቱትን ቡና የሚያክል የለም" ይላል።















