በናይጄሪያ እራሱን በ50 ሺህ ዶላር ለመሸጥ ገዢ ሲፈልግ የነበረው ግለሰብ ተያዘ

አሊዩ ኢድሪስ

የፎቶው ባለመብት, Aliyu Idris

ናይጄሪያ ውስጥ በምትገኝ አንዲት ግዛት "በድህነት" ምክንያት እራሱን ለሽያጭ ያቀረበው ወጣት በሐይማኖታዊ ፖሊሶች መያዙ ተነገረ።

ካኖ በምትባለው ግዛት ውስጥ የ26 ዓመቱ አሊዩ ና ኢድሪስ የተባለው ወጣት እራሱን ለሽያጭ ማቅረቡን በተመለከተ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ መነጋገሪያ ከሆነ በኋላ ነው ሂስባህ በሚባሉት እስላማዊ ፖሊሶች የተያዘው።

የፖሊሶቹ አዛዥ ሃሩን ኢብን የወጣቱ ድርጊት በሐይማኖቱ የተከለከለ በመሆኑ መያዙን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

"ማክሰኞ ዕለት በቁጥጥር ስር አውለነዋል፣ ድርጊቱ በእስልምና እምነት የተከለከለ ነው። ማንም ሰው ምንም ያህል አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ቢሆንና ቢቸግረው እራሱን መሸጥ አይችልም" ብለዋል።

ልብስ ሰፊ የሆነው ወጣቱ አሊዩ በሐይማኖታዊ ፖሊሶች ከመያዙ በፊት በከባድ የገንዘብ ችግር ውስጥ መሆኑን ለጋዜጠኞች ተናግሯል።

በዚህም ሳቢያ ነው 'የሚገዛው' ሰው ለመፈለግ በአንገቱ ላይ ዋጋውን አንጠልጥሎ ወደ ጎዳና የወጣው። ለራሱ የሰጠው ዋጋም 20 ሚሊዮን የናይጄሪያ ገንዘብ (ናይራ) ሲሆን ይህም ወደ 50 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ገደማ ይሆናል።

ወጣቱ ይህንን ገንዘብ ከፍሎ ለሚገዛው ሰው በሙሉ ልቡ ሊያገለግል ዝግጁ መሆኑንም ገልጿል።

"እዚህ ውሳኔ ላይ የደረስኩት በድህነት ምክንያት ነው። የሚገዛኝ ሰው ካገኘሁም የሽያጩን ግማሽ ማለትም 24 ሺህ ዶላር ለቤተሰቦቼ እሰጣለሁ" ብሎ ነበር።

በተጨማሪም ሽያጩ ሕጋዊ እንዲሆን የፈለገው አሊዩ "ከሽያጩ ለመንግሥት የሚገባውን 12 ሺህ ዶላር በግብር መልክ ለመክፈል እና ገዢ እንዳገኝ ለሚረዳኝ ደላላ ደግሞ አምስት ሺህ ዶላር የምከፍል ሲሆን የቀረውን ለእራሴ ወጪ አውለዋለሁ" ሲል በፖሊስ ከመያዙ በፊት ለጋዜጠኞች ተናግሮ ነበር።