በሊቨርፑልና በማን. ዩናትድ ጨዋታ ምክንያት ኬንያውያን ተማሪዎች የመኝታ ክፍላቸውን አቃጠሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አራት ኬንያውያን ተማሪዎች የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታን እንዳይመለከቱ በመከልከላቸው የትምህርት ቤታቸውን የተማሪዎች የመኝታ ክፍል ማቃጠላቸው ተነገረ።
ተማሪዎቹ ባለፈው እሁድ በሊቨርፑል እና በማንችስተር ዩናይትድ ቡድኖች መካከል የተካሄደውን ጨዋታ "እንዳንመለከት ተከለከልን" በሚል ነው የተማሪዎች የመኝታ ክፍልን በእሳት ማቃጠላቸው የተዘገበው።
በዚህ ድርጊት የተጠረጠሩት አራቱ ተማሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደሚገኙ ዴይሊ ኔሽን የተባለው የኬንያ ጋዜጣ ዘግቧል።
የኬንያ የባሕር ዳርቻ ግዛት በሆነችው ኪሊፊ ውስጥ የሚገኘው የወንዶች ትምህርት ቤት ውስጥ ተማሪ የሆኑት አራቱ ልጆች ንብረትን በእሳት በማቃጠል ወንጀል ዛሬ ረቡዕ ፍርድ ቤት ቀርበው ክስ እንደሚመሰረትባቸው ፖሊስ አስታውቋል።
አራቱ ተማሪዎች በመኝታ ክፍላቸው ላይ የእሳት ቃጠሎ አደጋ አድርሰዋል ተብለው ተለይተው የተያዙት ተጠርጥረው በፖሊስ ምርመራ ከተደረገባቸው 14 ተማሪዎች መካከል መሆኑን ፖሊስ ገልጿል።
ፖሊስ ምርመራውን ካደረገ በኋላ ቀሪዎቹን አስር ተማሪዎች የለቀቀ ሲሆን አራቱን ግን በወንጀሉ እንደጠረጠራቸው በመግለጽ ክስ እንደሚመሰርትባቸው አስታውቋል።
ተማሪዎቹ ይህንን ድርጊት እንዲፈጽሙ ምክንያት የሆናቸው በእግር ኳስ ተከታታዮች ዘንድ ትልቅ ግምት የተሰጠውን የሁለቱን የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ኃያል ቡድኖችን ጨዋታ እንዳይመለከቱ በመከልከላቸው ነው።
በትምህርት ቤቱ ሕግ መሠረት ተማሪዎች እግር ኳስ እንዲመለከቱ የሚፈቀድላቸው ቅዳሜ ዕለት የሚደረጉትን ውድድሮች ብቻ መሆኑን የአካባቢው የፖሊስ ኃላፊ የሆኑት ኮማንደር ፍሬድሪክ አቡጋ ተናግረዋል።
በተማሪዎች የመኝታ ክፍል ላይ በተፈጸመው የእሳት ቃጠሎ ምክንያት ትምህርት ቤቱ እንዲዘጋ መደረጉም ተገልጿል።
ባለፈው ዕሁድ በማንችስተር ዩናይትድ ሜዳ ኦልድ ትራፎርድ በተካሄደው የሊቨርፑልና የማን ዩናይትድ ጨዋታ ሊቨርፑል በሰፊ የግብ ልዩነት 5 ለ 0 ማሸነፉ ይታወሳል።
በጨዋታው ግብፃዊው የሊቨርፑል አጥቂ ሞሐመድ ሳላህ ሦስት ግቦችን በማስቆጠር በፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች ከፍተኛውን ግብ ያስቆጠረ አፍሪካዊ ለመሆን ችሏል።













