በአሜሪካ የማክዶናልድ ሠራተኞች በወሲባዊ ትንኮሳ ምክንያት የሥራ ማቆም አድማ አደረጉ

የማክዶናልድ ሰራተኞች

የፎቶው ባለመብት, Fight for $15

በ12 የአሜሪካ ከተሞች የሚገኙ የማክዶናልድስ ሠራተኞች ድርጅቱ ጾታዊ ጥቃትን በተመለከተ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን የሚይዝበትን መንገድ በመቃወም የሥራ ማቆም አድማ እና የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል።

የተቃውሞ ሰልፉ አዘጋጆች ከአውሮፓውያኑ 2018 ጀምሮ ጾታዊ ጥቃቶችን በተመለከተ ተቃውሞ ሲያደርጉ እንደነበረ የገለጹ ሲሆን፣ እንሱ እንደሚሉት ድርጅቱ ሠራተኞች የሚያቀርቡትን ቅሬት ችላ ሲል ነበር።

በቺካጎ፣ ዴትሮይት፣ ሂዩስተን እና ማያሚን ጨምሮ በሌሎች ከተሞች የሚገኙ የማክዶናልድስ ሬስቶራንቶች ውስጥ የሚሰሩ ገንዘብ ተቀባዮች እና አስተናጋጆች የሥራ ማቆም አድማ አድርገዋል።

ድርጅቱ በበኩሉ ''ማክዶናልድስ ውስጥ ጾታዊ ጥቃትና ትንኮሳ ቦታ የላቸውም'' ብሏል።

እስካሁን ድረስ ምን ያክል ሠራተኞች ሥራቸውን እንዳቆሙ በግልጽ የታወቀ ነገር የለም።

ይህንን የሥራ ማቆም አድማ እና ተቃውሞውን ያዘጋጀው 'ፋይት ፎር 15 ዶላር' የተሰኘው ቡድን እንደገለጸው ከ2016 ጀምሮ ሠራተኞች ከ50 ጊዜ በላይ ቅሬታዎችን እና ክሶችን አቅርበዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ቅሬታ ያቀረቡ የድርጅቱ ሠራተኞች ከኃላፊዎች በኩል ያልተገባ ምላሽና የሥራ ሰዓት መቀነስ እንዲሁም ከሥራቸው እስከመባረርም መድረሳቸውን ቡድኑ ገልጿል።

"አኔም ተቃውሞውን እቀላቀላለሁ። ምክንያቱም ለዓመታት ተቃውሞ ብናደርግም ማክዶናልድስ በበርካታ ሴቶች ላይ ለሚደርሰው ጾታዊ ጥቃትና ትንኮሳ ኃላፊነት አልወሰደም" ብላለች ሳንፎርድ ፍሎሪዳ ውስጥ በሚገኘው ሬስቶራንት የምትሰራው ጃሚላ ፌይርሊ።

"ድርጅቱ የፈለገውን ነገር ሁሉ ቢልም እኔ ግን እንደ ሠራተኛ ምንም የተቀየረልኝ ነገር ያለም።"

በ2020 ላይ በተሰራ አንድ የዳሰሳ ጥናት ላይ ከተሳተፉ 800 ሴት የማክዶናልድስ ሠራተኞች መካከል ሦስት አራተኛ የሚሆኑት በሥራ ገበታቸው ላይ ጾታዊ ትንኮሳ እንደሚደርስባቸው ገልጸው ነበር።

በዚሁ ተመሳሳይ የዳሰሳ ጥናት ላይ ጾታዊ ትንኮሳ እንደደረሰባቸው ለድርጅቱ ካስታወቁ ሴቶች መካከል 71 በመቶ የሚሆኑት ከድርጅቱ በኩል ቅጣት የሚመስል እርምጃ እንደገጠማቸው ገልጸዋል።

የሥራ ማቆም አድማዎቹን እና ተቃውሞዎቹን ተከትሎ ማክዶናልድስ በሁሉም ሬስቶራንቶች ውስጥ ለሚሰሩ ሠራተኞች ከሚቀጥለው ጥር ወር ጀምሮ ጾታዊ ትንኮሳና በተመለከተ ሥልጠና እንደሚሰጥ አስታውቋል።

ነገር ግን የተቃውሞው አዘጋጆች ድርጅቱ ያወጣው መግለጫ በትክከል ችግሮቹ ላይ ተገቢውን እርምጃ እንደማይወስድ ማሳያ ነው ብለዋል።

ድርጅቱ ግን የሚቀርቡ ጾታዊ ትንኮሳን የተመለከቱ ቅሬታዎችን በተገቢው መንገድ እንደሚመረምርና መመሪያዎችን ተግባራዊ ለመድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጿል።