የኮሮናቫይረስ ክትባትን ለመውሰድ ማመንታት በኢትዮጵያ - የአንዳንዶች ፈተና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኮሮና የፈጠረውን ስጋት ያህል ክትባቱ ያስገኘው ተስፋ እና ደስታ አሁን ድረስ ዘልቋል። ብዙዎች ክትባቱ መቼ በተገኘ እና ከዚህ በሽታ በተገላገልን እንዳላሉ አሁን አሁን ደግሞ አንከተበም የሚሉም ቁጥራቸው የትየለሌ ነው።
የጤና ባለሙያዎች ክትባቱ ሰዎች እንዲከተቡ እያበረታቱ ነው። የጤና ባለሙያዎችን ምክር ተቀብለው ግን ሁሉም ለመከተብ ፈቃደኛ አልሆነም።
ክትባቱን አንፈልግም ከሚሉ ጀምሮ አምርረው እስከሚቃወሙ ድረስ ዓለም እያስተናገደች ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ክትባቱን ተቃውመው ሰልፍ የወጡ ባይኖሩም 'አንከተብም' የሚሉት ግን ጥቂት አይደሉም።

ቃልኪዳን ዓለሙ የአዲስ አበባ ነዋሪ ናት።
የ ኮሮናቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ ገባ ሲባል እሷም እንደ ብዙዎቹ ደንግጣለች።
"እኔስ? ቤተሰቦቼስ እንዴት እንሆናለን?" ብላለች።
ከቤት መውጣት እና ሥራ መሄድ ያስፈራት የነበረበት ጊዜም ሩቅ አይደለም።
ጊዜው እየገፋ ሲሄድ ግን መላመድ መጣ።
የክትባቱ መገኘት ደግሞ ለመላው ዓለም ተስፋን ፈነጠቀ።
ቃልኪዳን ግን ክትባቱን ከመውሰድ ጥንቃቄ ማድረግን መርጣለች።
"የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሁሌም አደርጋለሁ። ሁሌም እጅ መታጠቡን ግን እንደቀድሞው አይደለም. . . ከበፊቱ [ኮሮና ከመከሰቱ በፊት] የተለየ እጅ የመታጠብ ነገር የለኝም" ትላለች ቃልኪዳን።
በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ስድስት ሺህ ማለፉን የጤና ሚኒስትር ካስታወቀ ቀናት ተቆጠሩ።
ባለፉት ጥቂት ወራት በወረርሽኙ ሳቢያ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በአሳሳቢ ሁኔታ መጨመሩን በየዕለቱ የሚወጣው መረጃ ያመለክታል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ እንደተናገሩት በኮሮናቫይረስ ተይዘው ለሞት ከተዳረጉት ሰዎች መካከል ሁሉም በሚባል ደረጃ ያልተከተቡ ናቸው።
በአገሪቱ ውስጥ ከሰኔ ወር አጋማሽ ጀምሮ እሰከ ነሐሴ ወር አጋማሽ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ በወረርሽኙ ከሞቱ ሰዎች መካከል አንድ ግለሰብ ብቻ የመጀመሪያውን የኮቪድ መከላከያ ክትባት የወሰደ ሲሆን ሌሎቹ በሙሉ ያልተከተቡ መሆናቸው ተገልጿል።
በተለይም ደግሞ የዴልታ ዝርያ በኢትዮጵያ መገኘቱና ህብረተሰቡ ቫይረሱን ለመከላከል የሚያደርገው ጥንቃቄ መላላት ለወረርሽኙ መስፋፋት ምክንያት ሆኗል ብለዋል።
ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስችለውን ክትባት አለመውሰድና ከቫይረሱ ጋር የሚሰራጩ ሃሰተኛ መረጃዎችም ለቫይረሱ ስርጭት ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን ጤና ሚኒስቴሯ ዶ/ር ሊያ ተናግረዋል።
ዶ/ር ሊያ የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል (ሲዲሲ) ጥናትን መነሻ አድርገው እንዳሉት፣ ያልተከተቡ ሰዎች ለበሽታው በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ ናቸው። በዚህም በቫይረሱ የመያዝ ዕድላቸው ከ4.5 እጥፍ በላይ፣ ሆስፒታል የመግባት ዕድላቸው ከ10 እጥፍ በላይ ሲሆን ታመው የመሞት ዕድላቸው ደግሞ ከ11 እጥፍ በላይ ነው ብለዋል።
ይህ አሃዝ ግን ቃልኪዳንን የሚያስበረግግ አልሆነም።
የኮሮናቫይረስ ክትባት እና ሐሰተኛ ወሬዎች
ከኮቪድ-19 ክትባት ጋር በተያያዘ በርካታ የሐሰት ትርክቶች በተለያዩ የማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ ሲሰራጩ ይታያል።
በኢትዮጵያ የተለያዩ ቤተ እምነት አገልጋይ የሆኑ አንዳንድ ግለሰቦች በበኩላቸው ስለ መድሃኒቱ የተለያዩ ሐሰተኛ መልዕክቶችን ሲያሰራጩ ተደምጠዋል።
መልዕክቶቹ ከክትባቱ የሚያርቁ ብቻ ሳይሆን የግለሰቦችን እምነት የሚፈትን ጭምር መሆኑ፣ እንዲሁም ሠፊው አማኝ በተሰበሰበበት አደባባይ ላይ የተነገረ መሆኑ ተጽዕኖውን ብርቱ አድርጎታል።
ምንም እንኳ ቃልኪዳን እነዚህን ስብከቶች ስለመስማት አለመስማቷ ባትናገርም "ምክንያቴ ሃይማኖታዊ ነው። ፈጣሪዬ እንደሚጠብቀኝ አምናለሁ። ስለዚህ ክትባቱን አልወስድም" ትላለች።
ቢቢሲ፡ ሌላም መድኃኒት አትወስጂም?
ቃልኪዳን፡ እወስዳለሁ። አሁንም እየወሰድኩት ያለሁት መድኃኒት አለ [ሳቅ]።
ቢቢሲ፡ የኮሮናው ክትባት ታዲያ በምን ይለያል?
ቃል ኪዳን፡ (ከረዥም ዝምታ በኋላ) ተከትበው የሚታመሙ ግፋ ሲልም የሚሞቱ እንዳሉ ሰምቻለሁ።
ክትባቱን የመጠራጠር እና ላለመከተብ ዳተኛ መሆን የቃል ኪዳን አቋም ብቻ አይደለም።
በአንድ ስሙ እንዳይገለጽ በተጠየቀ የመንግሥት መስሪያ ቤት ክትባት እንዲወስዱ ጥያቄ ከቀረበላቸው 250 ሠራተኞች መካከል 30ዎቹ ብቻ ናቸው ፈቃደኛ ሆነው የተከተቡት።
ቫይረሱ ጉዳት ማድረሱን የማትክደው ቃልኪዳን "ችግሩ አፍጥጦ እየታየና ወገኖቻችንን አያጣን ነው። እውነቱን እንቀበል። ራስን ከቫይረሱ ለመከላከል አለመቻል ግራ የሚያጋባ ነው። የሚሠጠው መመሪያ እንዲፈፀም እንተባበር። የማይተባበሩትን እናስተምር" ትላለች።
"አሁን በበሽታው የሚያዙ እና ህይወታቸው የሚያልፍ ሰዎችን ቁጥር መጨመርን ስመለከት እንኳንም ተከተብኩ እላለሁ"
አስቴር ሞገስ ክትባቱን ቀድመው ከወሰዱት መካከል አንዷ ናት።
ክትባቱን ለመውሰዷ ምክንያት የሆናት ችግሩ በሯን አንኳክቶ መምጣቱ ነው።
ከወራት በፊት የቅርብ ቤተሰቧ ይታመማል።
ትንሽ የሚመስለው ህመም ከዕለት ወደ ዕለት እያደገ "ሳንዘጋጅበት ህይወቱ አለፈ" ትላለች።
ይህ ክስተት ቤተሰቡ ውስጥ ድንጋጤን ፈጥሯል።
ሌላኛው የድንጋጤው ምክንያት ደግሞ ኮሮና ነው መባሉ ነው።
"ለቅሶው፣ ቀብሩ ሁሉም ነገር ሐኪሞች ባሉት መሠረት ነው የተከናወነው" ትላለች አስቴር።
ቤተሰቡ ከመደናገጡ የተነሳ "ማስክ ደርቦ ነበር የለቅሶው ሰሞን የሚጠቀመው" ትላለች።
ከለቅሶው በኋላ ሁሉም ባይባልም ብዙዎቹ የቤተሰቡ አባላት በፍጥነት ነበር ክትባት የተከተቡት።
ቅድሚያ ተጓዳኝ በሽታ ያለባቸው ወሰዱ።
"አናቴ፣ አጎቶቼ፣ ወንድም እና እህቶቼ በፍጥነት ነበር የተከተብነው።"
"መጀመሪያ ላይ 'ተጓዳኝ በሽታ ላለባቸው ብቻ ነው ክትባቱ የሚሰጠው' ሲባል እኛም ተጓዳኝ በሽታ እንዳለብን በመናገር ነው የተከተብነው" ስትል ታስታውሳለች።
የመጀመሪያውን ክትባት አግኝተው ሁለተኛውን ዙር ለማግኘት ጊዜ ቢፈጅባቸው "ተከታትለን ተከትበናል" ስትል ለቢቢሲ ገልጻለች።
አንድ የቤተሰቡ አባል ላይ መጠነኛ ከሚባል የጎንዮሽ ህመም ውጭ ሁሉም የቤተሰቡ አባላት ምንም የገጠማቸው ነገር እንደሌለ ትናገራለች።
"የዘመዳችን ሳናስበው በኮሮና ህይወቱ ማለፍ ዋነኛው ምክንያት ቢሆንም ዶክተር እህታችን እሷም ተከትባ እኛም እንድንከተብ ስላበረታታችን ነው ለመከተብ የቻልነው" ትላለች።
"ሰው ቅድሚያ ለህይወቱ ዋጋ መስጠት አለበት። ትምህርት መውሠድ አለበት። የተከተቡ ላልተከተቡ ሠዎች እናስተምራቸው። በርግጠኝነት ክትባቱ ጉዳት የለውም። ሁለቱንም ተከትበናል" ብላለች።
አስቴር በክትባት ብቻ አላቆመችም ከቤት ውጭ በሚደረገው እንቅስቃሴዋ ሁሉ የአፍና አፍንጫ ጭንብል ትጠቀማለች።
"አሁን በበሽታው የሚያዙ እና ህይወታቸው የሚያልፍ ሰዎችን ቁጥር መጨመርን ስመለከት እንኳንም ተከተብኩ እላለሁ" ብላለች።
ለምን ተከተብሽ የሚላት ባይኖርም አንከተብም የሚሉ ሰዎች እንደገጠሟት ትናገራለች
እሷ ግን "ከዚህ ቀደም እንደተከተበቻቸው ክትባቶች" እንደምትመለከተው ትገልጻለች።
የኮሮናቫይረስ ክትባት አቅርቦት
መጀመሪያ ላይ ክትባት ማግኘት አስቸጋሪ ነበር። ለመከተብ ፈልገው ያጡ ሰዎች ቁጥር ቀላል አልነበረም።
በአንዳንድ አካባቢዎች አሁንም ክትባት ስለመኖሩም መረጃ ያላገኙ እና ክትባት አለመኖሩንም የሚገልጹ ሰዎችም አሉ።
በአዲስ አበባ ግን ከዚህ የተለየ ነው። የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በሚኖርበት አካባቢ የጤና ባለሙያዎች እየዞሩ ከ18 ዓመት በላይ የሆናቸው ሰዎች እንዲከተቡ ሲያበረታቱ በተደጋጋሚ ሰምቷል።
በዘንድሮው የመስቀል ደመራ በዓል ዕለትም ፈጣን የኮቪድ-19 ምርመራ እና ለክትባት ፈላጊዎች አገልግሎት እንደሚሰጥ ጤና ሚኒስቴር ሲገልጽ ነበር።
እንደ ደመራ፣ ኢሬቻ እና ሌሎችም ሕዝብ በሚበዛባቸው በዓላት እና ስፍራዎች የምርመራ እና ክትባት አገልግሎቶች የሚሰጡ መሆኑ ተጠቅሶ ነበር።
ሰዎች ወደ መስቀል አደባባይ ሲሄዱ በሁሉም መዳረሻዎች ላይ ፈጣን የኮቪድ-19 ምርመራ ከመስጠት ባለፈ፣ በስቴዲየም መግቢያ ክትባቱ የሚሰጥ በመሆኑ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል አገልግሎቱን ማግኘት ይችላል ሲል አስታውቆ ነበር።
እንደዚህ ዓይነት አጋጣሚዎችን በመጠቀምም የሃገሪቱ የተከታቢዎች ቁጥር በየዕለቱ እያደገ ነው።
ጤና ጥበቃ በሚሰጠው ዕለታዊ መረጃ መሠረት ኢትዮጵያ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎቿ ክትባቱን ሰጥታለች።
ከትባቱን በስፋት ለማዳረስ ትምህርት መስጠት እና ክትባቱን ተደራሽ ማድረግ በብዙዎች ተመራጭ ዘዴ ሆኗል።
አንዳንዶች ደግሞ ክትባቱን አስገዳጅ ማድረግ ጀምረዋል።
ቢቢሲ ለቃልኪዳንም ለአስቴርም ክትባቱ ግዴታ ቢሆንስ ሲል ጥያቄ አቀረቦ ነበር።
ቃልኪዳን "ግዴታ የሚለው ትክክል አይደለም። በፈጣሪ እና በጥንቃቄ እናልፈዋለን። መቼም እስካሁንም የደረስነው በክትባት አይደለም" ስትል አስቴር ደግሞ "ክትባቱን የፈጠሩት ፈጣሪ በሰጣቸው ጥበብ አይደል? ስለዚህ ግዴታ ቢሆን ጥሩ ነው። እንደኛ ሁሉም ችግር ሲደርስበት አይደለም ሊማር የሚገባው [እንደመቆዘም አለች]። እንደሌሎቹ መድኃኒቶች ክትባቱንም ፈጣሪ ነው የሰጠን" ስትል ትሞግታለች።















