ኮሮናቫይረስ፡ ብዙ ያልተነገረለት ኮቪድ-19 በአንጎላችን ላይ ሊያደርስ የሚችለው ጉዳት ምንድን ነው?

ስትሮክ፣ ቅዠት፣ ጭንቀት፣ ግራ መጋባት፣ ድካም ፣ እያለ ይቀጥላል። ኮቪድ-19 የመተንፈሻ አካላት ላይ ብቻ ጉዳት የሚያደርስ ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል።
እያንዳንዱ ሳምንት ባለፈ ቁጥር ኮሮናቫይረስ ዘርፈ ብዙ አእምሯዊና አካላዊ ጉዳቶችን ማስከተል ይጀምራል።
ቫይረሱ እንደተገኘባቸው የተረጋገጡ በርካታ ሰዎች በመጀመሪያ አካባቢ ብዙም የሚሰጋ ህመም የማይሰማቸው ሲሆን፤ ቀስ በቀስ ግን ማስታወስ አለመቻልና ድካምን የመሳሰሉ ጠንከር ያሉ ምልክቶች ማሳየት ይጀምራሉ።
ፖል ማይልሪያ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሁለት ከባድ የሚባሉ ስትሮኮች [የአንጎል ውስጥ ደም መፍሰስ] አጋጥመውታል።
የ64 ዓመቱ ፖል በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የኮምዩኒኬሽንስ ኃላፊ ሲሆን እምብዛም ስጋት ውስጥ ሊከተው ሚችል የጤና እክል አልነበረበትም።
በለንደኑ የአንጎልና የአንጎል ቀዶ ህክምና ብሔራዊ ሆስፒታል ውስጥ እጅግ ከፍተኛ የጤና መሻሻል ያሳየ የኮሮረናቫይረስ ታማሚ ሆኗል። ካጋጠመው ስትሮክ በኋላም ፖል ጥሩ የሚባል መሻሻል ታይቶበታል።
የመጀመሪያው ስትሮክ ያጋጠመው በሆስፒታል የጽኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ እያለ ነበር። በዚህ ምክንያት ሕይወቱ ልታልፍበት የምትችለበት እድልም ከፍተኛ ነበር። ለዚህም ሲባል ደም የሚያቀጥን መድኃኒት እንዲወስድ ተደርጎ ነበር።
ከጥቂት ቀናት በኋላ ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ስትሮክ አጋጠመው። ሁለተኛው ግን በጣም የከፋና ሕይወቱን ትልቅ አደጋ ውስጥ የከተተ ነበር።
አማካሪ የአንጎል ሐኪም ሆኑት ዶክተር አርቪንድ ቻንድራቴቫ፤ ፖል በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታሉ ሲመጣ ሥራቸውን ጨርሰው እየወጡ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
''ፖል ፊቱ ላይ ግራ መጋባት ይስተዋልበት ነበር። መመልከት የሚችለው በአንድ አቅጣጫ በኩል ብቻ ነበር፤ ተንቀሳቃሽ ስልኩን ለመጠቀምም ሲቸገርና የይለፍ ቃሉን ማስታወስ አቅቶት ግራ ሲጋባ ነበር'' ብለዋል ዶክተሩ።
ዶክተር አርቪንድ እንደሚሉት በፖል ጭንቅላት ውስጥ አጋጥሞ የነበረው የደም መርጋት ከዚህ በፊት አይተውት የማያውቁት አይነት እንደሆነ ይናገራሉ።
ፖል በተደረገለት ምርመራ የደም መርጋት ምልክቶች ታይተውበታል። በምርመራው የተገኘው ውጤትም አጋትሟቸው በማያውቁት ሁኔታ እጅግ የተለየና አሳሳቢ ነበር።
"በሕይወቴ እንዲህ ያለ ውስብስብና ከፍተኛ ከፍተኛ ደም መርጋት ሁኔታ ተመልክቼ አላውቅም" የሚሉት ዶክተር አርቪንድ ኮሮረናቫይረስ የፖል ደም በእጅጉ የተጣበቀ እንዲሆን እንዳደረግ ይገልጻሉ።
በእንቅስቃሴ ገደቡ ጊዜ ስትሮክ አጋጥሟቸው ድንገተኛ ክፍል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር ቀንሶ ነበር። ነገር ግን በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ የአንጎል ህክምና ባለሙያዎች በኮቪድ-19 ምክንያት ስትሮክ ያጋጠማቸው ስድስት ሕመምተኞችን አክመዋል።
ለአደጋው መንስኤ የነበረው በሰውነት እና በአንጎል ውስጥ እብጠት የሚያስከትሉ የሰውነት በሽታ ተከላካይ ሕዋሳት በጣም ከመጠን በላይ መበራከት ነው።
ዶክተር አርቪንድ የፖልን አንጎል የውስጥ ክፍልን የሚያሳዩ ምስሎችን ሲመለከቱ በቫይረሱ ምክንያት የማየት አቅሙ መዳከሙን፣ ማስታወስ እንደሚቸግረው፣ መናገር እንደሚከብደውና ነገሮችን ማስተዋል ከባድ እንደሚሆንበት አስተውለዋል።
ያጋጠመው ስትሮክ በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ሐኪሞች በሕይወት አይተርፍም ወይም የአካል ጉዳተኛ ይሆናል ብለዋ ገምተው ነበር።
ፖልም ቢሆን "ከሁለተኛው ስትሮክ በኋላ ባለቤቴ እና ሴት ልጆቼ አበቃለት ብለው እንደገና ደግመው እንደማያዩኝም ገምተው ነበር'' ሲል ተናግሯል።
''ዶክተሮቹ ምንም ማድረግ የሚችሉት ነገር እንደሌለና ያለው አማራጭ መጠበቅ ብቻ እንደሆነ ነገሯቸው። ነገር ግን እኔ በሆነ መንገድ ተረፍኩኝ፤ ጤናዬም ቀስ በቀስ መስተካከል ጀመረ።''

ፖል እየተሻለው መሆኑን ካሳዩ ነገሮች መካከል ከነርሶቹ ጋር በእንግሊዝኛ የጀመረውን ንግግር በፖርቹጊዝ መጨረስ መጀመሩ ነበር።
ፖል ስድስት ቋንቋዎችን የሚናገር ሲሆን ከስትሮኩ በኋላ ጭንቅላቱ ቀድሞ የተማራቸውን ነገሮችና በዚህ ሁኔታ ውስጥ ቋንቋዎችን ማስታወስ መጀመሩ ለዶክተሩ አበረታች ውጤት ነበር።
ፖል እንደሚለው ከስትሮኩ በኋላ እንደቀድሞው በፍጥነት ማንበብ ያቃተው ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ነገሮችን ይዘነጋል። ነገር ግን ካጋጠሙት ሁለት ስትሮኮች አንጻር በጭንቅላቱ ላይ የደረሰው ጉዳት ከታሰበው በታች ትንሽ ነው።
አካላዊ የማገገም ሂደቱም ቢሆን ተስፋ ሰጪ ነበር። ዶክተሮች ለዚህ በምክንያትነት ያስቀመጡት ደግሞ ከዚህ በፊት የነበረው አካላዊ ብቃት ጥሩ መሆኑን ነው።
"በየቀኑ ለአንድ ሰዓት ያህል ብስክሌት እነዳለሁ፣ በሳምንት ውስጥ የስፖርት ማዘውተሪያ እሄዳለሁ፣ በአቅራቢያ ባለ ወንዝ ውስጥም እዋኛለሁ። ከዚህ በኋላ ግን ሳይክል መንዳት የምችል አይመስለኝም። ነገር ግን መዋኘት መቀጠል የምችል ይመስለኛል'' ብሏል ፖል።
በላንሴት የሥነ አእምሮ ክፍል ባደረገው ጥናት መሰረት በዩናይትድ ኪንግደም ሆስፒታሎች ውስጥ 125 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ምክንያት የአንጎል ውስጥ ችግር አጋጥሟቸዋል።
ግማሽ የሚሆኑት ደግሞ ስትሮክ ያጋጠማቸው ሲሆን የደም መርጋት ችግርና የአንጎል እብጠት እንዲሁም እብደት መሰል ሁኔታ ተስተውሎባቸዋል።
ካናዳዊው የአንጎል ህክምና ተመራማሪው ፕሮፌሰር አድሪያን ኦዊን እንደሚሉት በኮሮረናቫይረስ ምክንያት ከባድ የጤና እክል ካጋጠማቸው በኋላ ሲሻላቸው ወደቤታቸው የሚላኩ ሰዎች ድነዋል ማለት አይደለም።
ታማሚዎቹ ወደቤታቸው ከተመለሱ በኋላ ለበርካታ ሳምንታት ሊቆይ የሚችል የማገገም ሂደት ይጠብቃቸዋል ብለዋል።
በዚህም ምክንያት የኮቪድ-19 ታማሚዎች የሚያሳዩት ምልክቶችና አንጎላቸው ላይ የሚስተዋለውን የአጭርና የረጅም ጊዜ ጉዳት በአግባቡ መመርመር ወደፊት ለሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል ፕሮፌሰር አድሪያን ያሳስባሉ።














