በኢትዮጵያ ሥራን ለመፍጠር ሥራ ፈጣሪዎችን መፍጠር አስፈላጊ ነው - ቤርናር ሎራንዶ

የፎቶው ባለመብት, Bernard
ቤርናር ሎራንዶ ከኢትዮጵያዊት እናቱና ከፈረንሳዊ አባቱ ተወልዶ ያደገው ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሆን፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አዲስ አበባ እንደጨረሰ ትምህርቱን ለመቀጠል በመጀመሪያ ወደ ፈረንሳይ ቀጥሎም ወደ አሜሪካ አቅንቷል።
ረዘም ላሉ ዓመታት የአሜሪካንን የሥራ ዓለም በመቀላቀል ከሠራ በኋላ 'አገሬን ላገልግል' በማለት ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ።
ከዚያም 'ሎራንዶ ኤንድ አሶስዬትስ' በሚል በቤተሰቡ ስም የሰየመውን ድርጅት በማቋቋም የሥራ አጥነትን ለመቅረፍ የበኩሉን ማበርከት ጀመረ።
ይህ ድርጅት በስሩ የተለያዩ ተቋማትን የሚያስተዳድር ሲሆን ከእነዚህም መካከል 'እንቆጳ' አንዱ ነው።
ዋና ሕልሙ በኢትዮጵያ ያለውን ሥራ አጥነት መቅረፍ መሆኑን የሚናገረው ቤርናር፣ ይህ ደግሞ እንዲሁ በጭፍን የሚሠራ ሥራ አለመሆኑን ያስረዳል።
ለቤርናር ሎራንዶ ሥራ ፈጣሪ መሆን ማለት ሥራ ላጡ ሰዎች ሥራን መስጠት ብቻ አይደለም።
ቤርናር በድርጅቱ በኩል ከሚሠራው በተጨማሪ፣ ሕልሙን ለማሳካትና የብዙ ኢትዮጵያውያንን ፍላጎት ለማሟላት ቤርናር ለኢትዮጵያ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር አማካሪ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
ቤርናር ተቋሙን የሚያማክረው 'ዲጂታል' የሆኑ ሥራዎችንና 'ዲጂታል ስታርት አፕ ኢኮ ሲስተምን' [በዲጂታል መስክ ለጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች አመቺ ሁኔታን] አብዝቶ መፍጠር ላይ እንደሆነ ይናገራል።
የቤርናር እንቆጳ
እንቆጳ የሥራ ዕድል ፈጠራው እንቅስቃሴ በተደራጀ መልኩ እንዲጓዝ ታስቦ የተቋቋመ መሆኑን የሚገልፀው ቤርናር "እንቆጳ በግዕዝ ንፁህ ወርቅ ነው። ማለትም ወርቅ ገና በሰው እጅ ሳይቀየር የሚገኝበት ሁኔታ ነው" ይላል።
ይህንን ብሔራዊ እንቅስቃሴ 'እንቆጳ' ብዬሎ የሰየመበት ብዙ ምክንያቶች እንዳሉት በመግለጽ "በመጀምሪያ ስሙ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በብዙ አፍሪካውያን ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል። በዋነኛነት ደግሞ 'ወርቅ' ማለት ስለሆነ ነው። ሁላችንም ወርቅ መፍጠር እንደምንችል እተማመናለሁ" ይላል።
ቤርናር የኢትዮጵያውያንን የሥራ አጥነት በቀላሉ መቅረፍ የሚቻለው "ሥራ ፈላጊ አጦችን ከሥራ ፈላጊነት ወደ ሥራ ፈጣሪ በምንቀይርበት ጊዜ ነው" ሲል ይጠቅሳል።
ለቤርናር ይህ የሥራ ዕድል ፈጠራ 'ዲጂታል' በሆኑ ዘርፎች ላይ ያተኮረ ካልሆነ ዓለም የእድገት ደረጃ ላይ እንደ አገር ለመድረስ በጣም ከባድ እንደሚሆን የመለክታል። ካልሆነ ግን የእነዚህ ሥራዎች ዘላቂነትም ሆነ በጊዜ ሂደት የሚመጡትን ምጣኔ ሀብታዊ ለውጦች የመቋቋም ጉልበት እንደማይኖራቸው ይናገራል።
"ሥራ መፍጠር ደግሞ ብዙ ሳይንስ የሚጠይቅ አይደለም። ቀላል የሆኑና በዓለም ዙሪያ እንደሚሠሩ የተመሰከረላቸው መንገዶችን መከተል ነው የሚጠበቅብን።"
ቤርናር በኢትዮጵያ ያለውን የሥራ ፈጠራ እንቅስቃሴን ሲያስረዳ ". . .የሥራ ፈጠራ 'ኤንተርፕረነርሺፕ' ፍላጎት ያላቸውን በሁሉም መንገድ መደገፍና ማበረታታት፣ በፖሊሲ ዙሪያ ያሉ ሥራዎችን ማስተዋወቅና ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር እንዲሁም ከሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽኑ ጋር በመተባበር 'ስታርት አፕ አክት' የተሰኘውን ረቂቅ አዋጅ መደገፍን ያካታትል" በማለት ያብራራል።
'ስታርት አፕ አክት' የተሰኘውን ረቂቅ አዋጅ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከሥራ ፈጠራ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ያወጣው አዋጅ ሲሆን የተፈለገበትም ምክንያት ጀማሪ 'ስታርት አፕ' ድርጅቶችን ብቻ ለመደገፍ ሳይሆን በአገሪቱ እድገት ላይ ትልቅ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉ ዘርፎች ላይ ቴክኖሎጂን በመጠቀም መሥራት የሚፈለጉ ፕሮጄክቶችን በሙሉ ለመደገፍ ታስቦ መሆኑን ቤርናር ያስረዳል።
እርዳታ መስጠት ሲባል እንዴት ነው?
እንቆጳ ሥራ ፈጣሪዎችን ይረዳል ወይም አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙ ያደርጋል ሲባል እንደ እርዳታ ድርጅት ስለተቋቋመ አለመሆኑን ቤርናር ይናገራል።
እንቆጳ ሥራ ፈጣሪ የሆኑ ሰዎችን በሕግ፣ በፋይናንስ እና በሌሎችም ጉዳዮች መረጃን በመስጠትና አስፈላጊ ሥልጠናና ድጋፍ በማቅረብ ይሰራል።
"ሥራን ለመፍጠር ሥራ ፈጣሪዎችን መፍጠር አስፈላጊ ነው" የሚለው ቤርናር ይህን ግብ ለመምታት ብቻውን በእንቆጳ ብቸኛ እንቅስቃሴ እንደማይወጣውም ተገንዝቧል።
"አገር አቀፍ ችግር በመሆኑና በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሥራ አጥ በመሆናቸው በአንድ ሰው ወይም በአንድ ድርጅት አቅም ችግሩ የሚቀረፍ አይደለም። የግል ድርጅቶች፣ መንግሥት በተለይም ደግሞ ግለሰቦች ማለትም ማኅብረሰቡ ሊሳተፍበት የሚገባና የሁሉንም አስተዋጽኦ የሚጠይቅ ነው" ይላል።
እንቆጳ በሥራ ኮሚሽን በኩል ባገኘው ፈቃድ መሠረት ከሌሎች ብዙ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እና ድርጅቶች በጋር ለመሥራት አስችሎታል።
የሥራ ፈጠራን ከመደገፍ ውጪ እንቆጳ ኮሚሽኑንና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን ለዲጂታሉ ዓለም ጠቃሚ ይሆናሉ ተብለው የሚታሰቡ ፖሊሲዎችን በመንደፍም ያግዛል።
ይህም 'ስታርት አፕ አክት'ን ጨምሮ 'ፐርሰናል ዳታ ፕሮቴክሽን ፕሮክላሜሽን' እና 'ዲጂታል ስትራቴጂ 2025'ን የመሳሰሉ ይካተቱበታል።
"የምንረዳቸው እንደ አስፈላጊነቱ 'ኤኮ ሲስተም ቢልደርስ' [ለሥራ ፈጠራ አመቺ ሁኔታን የሚፈጥሩ] የምንላቸውንም ጭምር ነው። እነርሱም ኢንቬስተሮች፣ ባንኮችና የመሳሰሉትን ያካትታል።"
አክሎ "ዋናው ችግር ሃሳብ ማምንጨቱ ሳይሆን ሥራውን ለማስጀመር የሚያስፈልገውን ገንዘብ ማግኘቱ ስለሆነ በዋነኛነት ትኩረታችንን ሰጥተን ድጋፍ የምሰጠው የፋይናንስ አቅርቦትን ማመቻቸት ላይ ነው" ይላል።
ቤርናር በዘርፉ ስላሉ ክፍተቶች ሲያስረዳም "ዋናው ክፍተት ያለው ለሥራ ፈጠራ ታስበው የሚጠነሰሱ ፕሮጄክቶችን መጀመሩ ላይ ሳይሆን፣ ሥራውን ለማስጀመር የሚያስፈልገውን ገንዘብ ራሱ ሥራ ፈጣሪው እንዲያገኝ መጠበቁ ላይ ነው" በማለት በዋነኝነት ለመሸፈን የሚታሰበው ክፍተትም የፋይናንስ እንደሆነ ይናገራል።














