እሌኒ ገብረመድህን፡ ዋና የደስታ አስፈፃሚ ሥራቸው ምንድን ነው?

የብሉ ሙን ዋና የደስታ አስፈፃሚ ዶ/ር እሌኒ ገብረመድህን

የፎቶው ባለመብት, ELENI GABREMADHIN

የምስሉ መግለጫ, የብሉ ሙን ዋና የደስታ አስፈፃሚ ዶ/ር እሌኒ ገብረመድህን

ዋና የደስታ አስፈፃሚ የተሰየመውን የሥራ መደብ ፈጥረው እራሳቸው ባቋቋሙት ድርጅት ውስጥ እራሳቸውን የመደቡት ዶ/ር እሌኒ ገብረመድህን ይህ ሃላፊነታቸው ምን እንደሆነና ምንስ ውጤት እንዳለው ይናገራሉ።

ዶ/ር እሌኒ ገብረመድህን በብዙ ሰዎች ዘንድ የሚታወቁት በሥራ ፈጠራቸው ወይም ለሥራ ፈጣሪዎች ዕድል በመስጠታቸው አሊያም ደግሞ የኢትዮጵያን የምርት ገበያን በማስጀመራቸው ነው። ሆኖም ግን ብዙ ሰው ላያውቀው የሚችለው በአሁኑ ሰዓት ዶ/ር እሌኒ ገብረመድህን ዋና የደስታ አስፈፃሚ ወይም በእንግሊዘኛ 'ቺፍ ሃፒነስ ኦፊሰር' መሆናቸውን ነው።

ለመሆኑ የደስታ አስፈፃሚ ሥራ ምንድን ነው? ምንስ ማለት ነው?

ብሉ ሙን

የብሉ ሙን ዋና ዓላማ "ወጣ ያሉ፤ ለየት ያሉ የፈጠራ ሃሳቦችን ለመገፋፋት ታስቦ" የጅማሮ ሥራ ፈጠራንና በፈጠራ ሃሳቦች ላይ የተመሠሩቱ ሥራዎችን በገንዘብና በተለያየ መልኩ ድጋፍ ለማበርከት የተቋቋመ እንደሆነ ያስረዳሉ።

በዚህ ዓይነት የሥራ አካባቢ ደግሞ "አንድ ሥራ አስኪያጅ ለየት ባለ መልኩ ነገሮችን ማየት ይኖረበታል" የሚሉት ዶ/ር እሌኒ የብሉ ሙን ሥራ አስኪያጅ መሆን ማለት ደስታ አስፈፃሚ ከመሆን ጋር ትርጉሙ ተመሳሳይ ሆኖ ሊታሰብ እንደሚችል ይጠቁማሉ።

"እራሴን ዋና የደስታ አስፈፃሚ ብዬ የሰየምኩትም ከድሮም ጀምሬ የምንሠራው በሙሉ መጨረሻው ደስታ መሆን አለበት ብዬ ስለማምን ነው" ይላሉ።

"አንድ ሰው የማያስደስተውን ነገር መሥራት የለበትም። የሚያስደስተውን ደግሞ መሥራት አለበት" ብለው አንድ ሥራ አስኪያጅ ሥራው ወረቀት ማገላበጥ ወይም ለሰው ትዕዛዝ መስጠት ብቻ ሊሆን አይችልም ይላሉ።

የዋና ደስታ አስፈፃሚ ሥራ ደግሞ የሁሉንም ሰው ደስታ ከእሳቤ አስገብቶ ጥሩ ውጤት ለማምጣት መነሳት ማለት እንደሆነ ይናገራሉ። የሥራ ድርሻቸው በሦስት የመሥሪያ ቤቱ ዘርፍ ውስጥ እንደሚንፀባረቅ ዶ/ር እሌኒ ይናገራሉ።

በድርጅት ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩት ሠራተኞች በሙሉ ደስታ የሚሰጥ ሥራ በመሥራትና በስሜት እንዲሠሩ ማመቻቸት ጠቀሜታው ከሠራተኛው በተጨማሪ ተገልጋዩ እራሱ 'በሚሰጠው አገልግሎት ድስተኛ ሆኖ እንዲሄድ ያስፈልጋል' በማለት የሥራ ድርሻቸውን ያስረዳሉ።

ከተጠቃሚዎቹ ባሻገር ደግሞ ኢንቬስተሮቹ ገንዘባቸውን በሚለግሱበት ወቅት 'አምነውበት ብቻ ሳይሆን ደስተኛ ሆነው እንዲሰጡ' ማድረግም በአጠቃላይ የደስታን አስፈላጊነት ያስረዳሉ። "በጥልቀት አስቤበት ሳይሆን የሚሰማኝንና የማምንበት ስለሆነ የአንድ መሪ ዋና ዓላማ በሁሉም አቅጣጫ ደስታ መፍጠር ይመስለኛል" ይላሉ።

ደስተኛ መሥሪያ ቤት

ሃሳብን ማመንጨት፣ መፍጠር፣ ሃሳብን ማጋራትና በሙሉ የእራስ መተማመን ሃሳብን መግለፅ ለብዙ የማህበረሰቡ አባላት ከባድ እንደሆነ የሚያስረዱት ዶ/ር እሌኒ እነዚህን የሚያበረታቱ አካባቢዎች አስፈላጊ መሆናቸውን ይገላፃሉ።

"ያለንብት ማህበረሰብ ለየት ያሉ ሃሳቦችን ብዙ ጊዜ በንቀት 'ከየት አመጣሽው? ከየት አመጣኸው?' የሚል ስለሆነ እኛ ለእንደዚህ ዓይነት ሃሳቦች ቦታ መፍጠር ነበረብን።"

"ሁሌም ጠዋት ጠዋት ወደ ብሉ ሙን የፈጠራ ሃሳባቸውን ይዘው የመጡትን አባላት ምን እንደሚያስደስታቸው የመጠየቅ ልማድ አለኝ" የሚሉት ዶ/ር እሌኒ፤ እርሳቸውም የእራሳቸውን ስሜትና የሚያስደስቷቸውን ነገሮች እንደሚያካፍሏቸውም አጫውተውናል።

ከሚሰሟቸው ምላሾች መካከል አልፎ አልፎ የሚሳፈሩበትን ታክሲ በሰዓቱ ማግኘታቸው የሚያስደስታቸው እና የተመገቡት ምግብ እንዳስደሰታቸው የሚነግሯቸው እንዳሉና እሳቸውም በዚያን ዕለት የለበሱት ልብስ እንዳስደሰታቸው እንደሚነግሯቸው ይጠቅሳሉ።

የደስታ የሚያስደስቱ ውጤቶች

"እኛ የሰው ማንነት ላይ ነው የምናተኩረው። ሲያወሩ ሳቅ ብለው እንዲያወሩ፣ በእራሳቸው መተማመን እንዲያዳብሩና ደስተኛ እንዲሆኑ ነው የምንተጋው" በማለት በሥራ ቦታ ደስታ እንዲኖር ማድረግ ውጤታማ እንደሚያደርግ ያስረዳሉ።

ከብሉ ሙን የሚወጡት ግለሰቦች ውጤታማ መሆናቸውን በደስታ የሚናገሩት ዶ/ር እሌኒ፤ በቅርብ ጊዜ ቶታል ያዘጋጀውን ውድድር ጠቅሰው "በተለያዩ ውድድሮችም ላይ ሲሳተፉ አሸናፊዎች ናቸው። በሥራቸው ብቻ ሳይሆን መንፈሳቸው እራሱ አሸናፊ ነው። በዚህ ዓመት አንደኛም፣ ሁለተኛም፣ ሦስተኛም የወጡት የብሉ ሙን ወጣቶች ናቸው። የረዳቸው ደግሞ በሥራቸው ደስተኛ መሆናቸው ይመስለኛል" በማለት ይናገራሉ።