የቀድሞ የሴራሊዮን አማፂ አመራር አባል ፊንላንድ ውስጥ ተያዙ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የቀድሞ የሴራሊዮን አማፂ አመራር አባል የነበሩት ጂብሪል ማሳኮይ ፊንላንድ ውስጥ በቁጥጥር ስር ዋሉ።
የሴራሊዮን አማፅያን ቡድን ቃል አቀባይ የነበሩት ጂብሪል ማሳኮይ ለአስር አመታት በኖሩባት ፊንላንድ በቁጥጥር ስር የዋሉት እንደ አውሮፓውያኑ ከ1999 እስከ 2003 የሴራሊዮን ጎረቤት በሆነችው ላይቤሪያ ውስጥ የጦር ወንጀሎችን በመፈፀም ተጠርጥረው ሲፈለጉ ስለነበር ነው።
ፍትህ ማስፈን ላይ የሚሰራው የስዊዘርላንድ ድርጅት ሲቪታስ ማክሲማ እንዳስታወቀው የቀድሞው አማፂ ከተጠረጠሩባቸው ወንጀሎች መካከል ዘር በማጥፋት፣ ፆታዊ ጥቃትና ህፃናትን በውትድርና ማሰማራት ይገኙበታል።
ለዓመታት በዘለቀው የላይቤሪያ ሁለት የእርስ በእርስ ጦርነት እጃቸው ያለ ሰዎችን ተጠያቂ በማድረግ ረገድ የግለሰቡ በቁጥጥር ስር መዋል ትልቅ እርምጃ እንደሆነ የላይቤሪያ ዓለም አቀፍ ፍትህ እና ጥናት ተቋም ተወካይ የሆኑት ፋያ ዊሊያምስ ተናግረዋል።
"በእርስ በእርስ ጦርነቶቹ ለተጎዱ ሰዎች ተስፋ ይሰጣል፤ ፍትህ ዜግነትን መሰረት አድርጎ ልዩነት እንደማያደርግም ማሳያ ነው" ብለዋል።
ላይቤሪያ ከ1989-1996 እና 1999-2003 ሁለት አሰቃቂ የእርስ በእርስ ጦርነት ተካሂዶባታል።
በሁለቱም ጦርነቶች በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ህይወታቸውን አጥተዋል።
ጂብሪል ማሳኮይ ከሌሎች ጋር ሆነው ሲመሩት የነበረው የሴራሊዮን አብዮታዊ አንድነት ግነባር ውጊያ የጀመረው በ1991 ነበር።
የውጭ ሰላም አስከባሪ ሃይሎች ትጥቅ እስኪያስፈቱት ድረስ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቹን ይዞ እስከ 2002 ሲዋጋ ነበር ።













