ለሁለት አገራት በውትድርና የተሰለፉት እህትማማቾች

የፎቶው ባለመብት, MOIWO FAMILY
ሁለቱ እህትማማቾች ትውልዳቸው በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ሴራሊዮን ሲሆን፤ አንደኛዋ ወጣት የትውልድ አገሯን ለመጠበቅ ወታደራዊ ስልጣና ወስዳ የሴራሊዮን ወታደራዊ ምሩቅ ሆናለች።
ትልቅ እህቷ ደግሞ የትውልድ አገሯ የቀድሞ ቅኝ ገዢ የሆነችው ብሪታኒያን በውትድርና እያገለገለች ነው።
ትንሿ እህት መቶ አለቃ ማቲልዳ ማቱ ሞይዎ ወታደር መሆኗን ትልቅ እህቷ ያወቀችው ስልጠናዋን አጠናቃ የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ሲካሄድ ነው።
ትልቋ እህት ኮርፖራል ሉሲ ሞይዎ ወደ ብሪታኒያ ሄዳ ሥራ በምታፈላልግበት ወቅት የጋራ ብልጽግና አገራት (የቀድሞ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት አገራት) ዜጎች የብሪታኒያ የመከላከያ ሠራዊት አባል መሆን ይችላሉ የሚል ማስታወቂያ በማየቷ ነበር የእንግሊዝ ወታደር ለመሆን የወሰነችው።
ታናሽ እህት ጂኦሎጂስት ነበረች። ነገር ግን በፈረንጆቹ 2017 በሴራሊዮን የደረሰውን ከፍተኛ የመሬት መንሸራተት ተከትሎ ትልቅ እህቷ ሌላ ሥራ በማፈላለግ እንድትረዳት ትንሽ አህት ጠይቃት ነበር።
የሰጣቻት ምላሽ ግን 'እኔን ምሰይ' የሚል ነበር። በእህቷ ምክር የተስማማችው ጂኦሎጂስት ውሳኔዋን ለእህቷ ባታሳውቃትም ምክሩን ተቀብላ ወደ ውትድርናው ዓለም ገባች።
በመጀመሪያዎቹ የስልጠናዋ ቀናት ጥይት ስትተኩስ በመፍራቷ አይኗን ጨፍና በመተኮስ እራሷን እንዳለማመደች ትናገራለች።
የፍርሃቷ ምክንያትም በ1990ዎቹ የሴራሊዮን የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት፤ የአባታቸው ስም አማጽያኑ ሊገድሏቸው ከሚፈልጓቸው ሰዎች ስም ዝርዝር ውስጥ በመገኘቱ አገር እንዲለቁ መገደዳቸው ነበር።
"ምናልባትም ይህ ነገር ለቤተሰቤ መጥፋት ምክንያት ሊሆን ይችላል እያልኩ እስጋ ስለነበረ ነው" ብላለች መቶ አለቃዋ።
አሁን ሁለቱ እህትማማቾች ታላቅ የብሪታኒያ፣ ታንሽ ደግሞ የአገሯ የሴራሊዮን ወታደር በመሆን እያገለገሉ ነው።
አይበለውና ሁለቱ አገራት ጦርነት ውስጥ ቢገቡ ማን ወደ ማን ቃታ ይስብ ይሆን?












