ትራምፕ ከአውሮፓ ወደ አሜሪካ የሚደረጉ በረራዎችን አገዱ

የፎቶው ባለመብት, AFP/GETTY IMAGES
የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እየጨመረ ያለባት አሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከአውሮፓ ወደ አገራቸው የሚደረጉ በረራዎችን በሙሉ ማገዳቸውን አስታወቁ።
በቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭት በተላለፈው ንግግራቸው ትራምፕ ከማንኛውም አውሮፓ አገር የሚደረግ በረራ ለቀጣዩቹ 30 ቀናት መታገዱን ገልፀዋል።
ነገር ግን ይህ ጥብቅ እና አስፈላጊ እግድ 460 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ባረጋገጠቸው እንግሊዝ ላይ ተግባራዊ እንደማይሆን አስታውቀዋል።
በመላ አሜሪካ 1135 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 38 የሚሆኑ ደግሞ ሞተዋል።
"አዳዲስ ኬዞች እንዳይገቡ ከአውሮፓ የሚደረጉ በረራዎችን በሙሉ አግደናል" ብለዋል ትራምፕ ትናንት ከዋይት ሃውስ በተላለፈው ንግግራቸው።
ይህ እገዳ ከነገ አርብ እኩለ ሌሊት ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።
አውሮፓ ህብረት አስፈላጊውን ጥንቃቄ አላደረገም ሲሉም ትራምፕ ጣታቸውን ህብረቱ ላይ ቀስረዋል።
እገዳው አሜሪካ ከመግባታቸው በፊት ለ14 ቀናት በአውሮፓ ህብረት በየትኛውም የሸንገን ነፃ ዝውውር አካባቢ በነበሩ ሰዎች ላይም ተግባራዊ እንደሚሆን ታውቋል።
ይህ ማለት ከ26 የሸንገን ነፃ ዝውውር ሃገራት መካከል ያልሆነችው አየርላንድ ከእግዱ ነፃ ትሆናለች ማለት ነው።
እንደ ቡልጋሪያ፣ ክሮሺያ እና ሮማኒያ ያሉ የአውሮፓ ህብረት አገራት የሸንገን ነፃ ዝውውር አካባቢዎች አይደለሙ።
ትራምፕ እንደገለፁት እግዱ ከአውሮፓ የሚመጡ ትልልቅ የንግድ ካርጎዎች ላይም ተፈፃሚ ይሆናል።
ኮሮናቫይረስ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ ለአነስተኛ ንግድ ተቋማት የብድር ድጋፍ እንደሚደረግ፤ የታክስ እፎይታዎች እንዲደረጉ የሚያስችል ውሳኔ ኮንግረሱ እንዲያሳልፍ እንደሚደረግም ተናግረዋል ትራምፕ።
"የአሜሪካን ህዝብ ለመከላከል የፌደራልና የግል ዘርፉን ሙሉ አቅም አቀናጅተን እየሰራን ነው" ብለዋል።















