ኮሮናቫይረስ፡ አሜሪካ በቫይረሱ ምክንያት የመጀመሪያው ሰው ሞተባት

የፎቶው ባለመብት, EPA
በአሜሪካ በዋሽንግተን ግዛት ለመጀመሪያ ጊዜ በኮሮናቫይረስ አንድ ሰው መሞቱ ይፋ ተደረገ።
ባለሥልጣናት ሟቹ በ50ዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኝና ሌሎች በሽታዎች ያሉበት ሰው ነው ብለዋል።
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው ሌሎች የኮሮናቫይረስ ተጠቂዎች ሊኖሯት እንደሚችሉ ተናግረው ነገር ግን ለቫይረሱ ከማንም በላይ ዝግጁ ነን ሲሉ አስረግጠዋል።
አውረስትራሊያም ለመጀመሪያ ጊዜ በኮሮና ምክንያት ሰው እምደሞተባት አሳውቃለች። ግለሰቡ በዳይመንድ ፕሪንሰስ መርከብ ውስጥ የነበረ የ78 ዓመት አዛውንት ነው ተብሏል።
እስካሁን በ57 አገራት ከ85 ሺህ በላይ የኮሮናቫይረስ ተጠቂዎች መኖራቸው ተዘግቧል። 3 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ሞተዋል ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አሳውቋል። ብዙዎች የቫይረሱ ተጠቂዎችና ሟቾች ቫይረሱ ከመነጨባት ቻይና ናቸው።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት ሟቹ የቫይረሱ ስጋት ወዳለበት አካባቢ አልተጓዘም ሲሉ ተናግረዋል። ይህን ተከትሎ የዋሽንግተን አገረ-ገዥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀዋል።
ካሊፎርኒያ፣ ኦሬጎን እና ዋሽንግተን ግዛቶች ውስጥ የቫይረሱ ስጋት ያለባቸው ቦታዎች ያልሄዱ ሰዎች የበሽታውን ምልክት ማሳየታቸውን ተከትሎ ስጋት አድሯል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዋሽንግተን ውስጥ በሚገኝ አንድ የአዛውንቶች መንከባከቢያ ክበብ ሁለት ሰዎች የቫይረሱን ምልክት አሳይተው ወደ ጤና ጣብያ ተወስደዋል። ሌሎች በርካታ የክበቡ አባላት ምርመራ እየተደረገላቸው ነው።
የዓለም ጤና ድርጅት አሜሪካ ውስጥ እስካሁን 62 ሰዎች የቫይረሱ ተጠቂዎች መኖራቸው ተረጋግጧል ይላል። አንድ አሜሪካዊ በቅርቡ ቫይረሱ በመነጨባት ዉሃን መሞቱ አይዘነጋም።
ትራምፕ፤ ምንም እንኳ ቫይረሱ አገራቸው ቢገባም 'የሚያስደነግጥ ነገር የለም' የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።
ምክትል ፕሬዝደንት ማይክ ፔንስ ደግሞ ኢራን ላይ ተጥሎ የነበረው የጉዞ እግድ እንደሚቀጥልና ባለፉት 14 ቀናት ኢራንን የጎበኘ ማንኛውም የውጭ ዜጋ ወደ አገራቸው እንደማይገባ አሳውቀዋል።
ኢራን ከቻይና ውጭ ብዙ ሰው በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሞተባት አገር ናት።













