ጆ ባይደን በመጪው ምርጫ የትራምፕ ተቀናቀኝ ሆነው ሊቀርቡ ይችላሉ

ጆ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በቀጣዩ የአሜሪካ ምርጫ ላይ የቀድሞ ምክትል ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ዲሞክራቶችን በመወከል የትራምፕ ተቀናቃኝ ሆነው ሊቀርቡ ይችላሉ ተባለ።

መራጮች ዲሞክራቶችን ወክሎ ሪፓብሊካኑን ዶናልድ ትራምፕን የሚገዳደር እጩ እየመረጡ ይገኛሉ።

በደቡብ ካሮላይና በተደረገው ምርጫ ጆ ባይደን ማሸነፍ ችለዋል። ይህም በቀጣይ ምርጫ ዲሞክራቶችን ወክለው እንዲወዳደሩ ሊያስችላቸው ይችላል ተብሏል።

ግራ ዘመሙ በርኒ ሳንደርስ፤ በደቡብ ካሮላይና በተደረገው ምርጫ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

የፊታችን ማክሰኞ ዲሞክራቶችን ወክሎ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ላይ የሚሳተፈው እጩ ይለያል።

ለሶስተኛ ጊዜ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ላይ የሚሳተፉት ጆ ባይደን፤ በአፍሪካ አሜሪካውያን ዘንድ ድጋፍ እንዳላቸው ይታመናል። በደቡብ ካሮላይና እንዲያሸነፉ ያስቻላቸው ከጥቁሩ የኮንግረስ አባል ጄምስ ክላይበርን ይሁንታ በማግኘታቸው ነው የሚሉም በርካቶች ናቸው።

በቀጣይ ምን ይፈጠራል?

'ሱፐር ቲዩስደይ' የሚል ስያሜ የተሰጠው የፊታችን ማክሰኞ የዲሞክራቶች እጩ ማን ሊሆን እንደሚችል የሚቀበት ቀን ነው።

በ14 ግዛቶች የሚገኙ ዲሞክራቶች ድምጽ ይሰጣሉ። ከእነዚህም መካከል በርካታ የህዝብ ቁጥር ያላቸው ካሊፎርኒያ እና ቴክሳስ ይገኙበታል።

በርኒ ሳንደርስም ሆኑ የኒው ዮርኩ ቢሊየነር ማይክል ብሎምበርግ ዲሞራቶችን በመወከል የትራምፕ ተቀናቃኝ ሆነው ሊቀርቡ የሚችሉበት እድል አለ።

የ78 ዓመቱ አዛውንት በርኒ ሳንደርስ ድጋፋቸው በዋናነት የሚመነጨው ከወጣቶች ነው። ባለፈው ምርጫ በሂላሪ ክሊንተን ተሸንፈው ከዲሞክራት እጩነት መውጣታቸው ይታወሳል።

በዘንድሮ ምርጫም ከጆ ባይደን በተጨማሪ ዲሞክራቶችን ወክሎ የትራምፕ ተቀናቃኝ የመሆን ስፊ እድል ያላቸው ሴናተር ናቸው።